Showing posts with label በዓላት ወአጽዋማት. Show all posts
Showing posts with label በዓላት ወአጽዋማት. Show all posts

Thursday, April 13, 2017

ዕለታተ ሰሙነ ሕማማት

በመምህር ቸሬ አበበ

 (ከማሕበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ የተወሰደ)

ሚያዝያ ፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
የእግዚአብሔር ቸርነት 
ከአባታችን አዳም በደል ወይም ስሕተት በኋላ በሕማማት፣ በደዌያት፣ በመቅሠፍታት፣ ወዘተ. በብዙ መከራ የሰው ልጅ ሊኖርባቸው ግድ የኾነባቸው ዘመናት ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ ጥሮ ግሮ ወጥቶ ወርዶ ለፍቶ ማስኖ የዕለት ጉርስ፣ የቀን ልብስ ማግኘት እጅግ አዳጋች ነበር፡፡ ዅልጊዜ የሰው ልጅ ቢያጠፋ ቢበድል ከሕገ እግዚአብሔር ቢወጣ እንኳ የዋህ፣ ታጋሽ፣ ቸር፣ አዛኝ የኾነ አምላክ የጠፋውን ሊፈለግ፣ የተራበውን ሊያጠግብ የታረዘውን ሊያለብስ፣ ፍቅር ያጣውን ፍጹም ፍቅር ሊለግስ፣ ሰላም ለሌለው ፍጹም ሰላምን ሊሰጥ፣ ተስፋ ለሌለው ተስፋን ሊያጐናጽፍ ከሰማይ ወረደ፤ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፤ በገዳመ ቆሮንቶስ ዐርባ ቀንና ሌሊት ጾመ፡፡ በጾሙም የኃጢአት ሥሮች ወይም ራሶች የተባሉትን ስስትን፣ ትዕቢትንና ፍቅረ ንዋይን ድል አደረገልን፡፡ እኛ እርሱ የጾመውን ጾም እንድናከብር እንድንጾም፤ ዲያብሎስን ድል አድርጐ እኛም ዲያሎስን ድል እንድንነሣው ኃይልና ምሳሌ ኾነን፡፡
ሰሙነ ሕማማት 
ሰሙን ‹ሰመነ – ስምንት አደረገ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ቃል ሲኾን ትርጕሙም ሳምንት፣ ስምንት ማለት ነው፡፡ ‹ሕማማት› ቃሉ ‹ሐመ – ታመመ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም ብዙ ሕማምን ያመላክታል፡፡ ‹ሰሙነ ሕማማት› ስንልም ‹የሕማም ሳምንት› ማለታችን ነው፡፡ ይኸውም ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር ዅሉ ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ ለማውጣት ሲል የተቀበለውን መከራ የምናስብበት ወቅት ነው፡፡ ሰሙነ ሕማማት ከዕለተ ሆሣዕና ሠርክ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ያለውን ጊዜ ያጠቃልላል፡፡ ዕለታቱ የዓመተ ኵነኔ ወይም የዓመተ ፍዳ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ውለታ እያሰቡ እጅግ የሚያዝኑበት፤ የሚያለቅሱበት፤ የሚሰግዱበት ቤት ንብረታቸውን ትተው ከሌላው ቀናትና ጊዜያት በተለየ መልኩ በቤተ ክርስቲያን ተሰባስበው እግዚአብሔርን የሚማጸኑበት፤ ጧት ማታ ደጅ የሚጠኑበት፤ ኃጢአታቸውን ለካህን የሚናዘዙበት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ልዩ ሳምንት ነው፡፡

Thursday, March 24, 2016

ዐቢይ ጾምና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ



ክፍል አንድ
 በመምህር ሙሴ ኃይሉ
በተለያዩ መጻሕፍት እንደተጻፈውና በተለያዩ የቤተክርስቲያናችን መምህራን ሊቃውንት በየዓውደ ምሕረቱ ዘወትር እንደሚተነተነው ጾም ማለት በታወቀ፣ በተወሰነ፣ በተቀመረ... ጊዜ ከመብል ከመጠጥ መከልከል፣ መቆጠብ፣ መወሰን... ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን "ጾም" ከክርስቲያናዊ ምግባርና ትሩፋት የሚመደብ ኣስተምህሮ ነው፡፡ ጾም የተመሠረተውም ሆነ የታዘዘው ከፈጣሬ ሰማያት ወምድር ከእግዚአብሔር ነው፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ምዕመን ጾምን በመከተል ለሠራዔ ጾም (ጾም ለሠራለት) አምላክ እየተገዛ፣ እያመለከ፣ እያከበረ፣ እየታዘዘ... በበጎ ሕሊና ተሞልቶ ፈቃደ ሥጋውን (ትዕቢት፣ ስስት፣ ዝሙት፣ ቅንዓት...) ለፈቃደ ነፍሱ (የዋህነት፣ በጎነት፣ ርህሩህነት...) በማስገዛት በፈጣሪ መመሪያ፣ ትእዛዝ እና ፈቃድ መኖር ማለት ነው፡፡

Monday, March 7, 2016

የጾም ዋጋ



ጾም ዋጋ የሚያሰጠው ከምግብ በመከልከል ብቻ ሳይሆን ከኃጢአት ሥራዎችም መራቅ ነው፡፡ ሥጋ በለመብላቱ ብቻ የጾመ የሚመስለው ቢኖር በዚህ አንዳች ነገር አያገኝም፤ ጾሙ ብላሽ ወይም ከንቱ ናት፡፡ ትጾማለህ? በሥራህ ግለጠህ አሳየኝ፡፡ በምን ዓይነት ሥራ ይገለጣል ትለኝ እንደሆነ ለደሃ ራራለት እዘንለት፡፡ የተጣለህን ታረቀው፣ በባልጄራህ ክብር አትቅና፡፡ መልከ መልካም ሴት ስታይ ውበቷ ሳይማርክህ እለፋት፡፡ ጾም አፍህ ብቻ ሳይሆን ዐይንህ፣ ጆሮህ፣ አፍንጫህ፣ እግርህ፣ እጅ፣ በአጠቃላይ መላ ሕዋሳትህ መጾም አለባቸው፡፡

Wednesday, February 24, 2016

ኪዳነ ምሕረት





/ ኅብረት የሺጥላ



http://eotcmk.org/site/images/stories/KidaneMihret.JPG

'ኪዳን' የሚባለው ቃል "ቃል" ከሚለው ጋር እየተቀናጀ በብሉይ ኪዳን 280 ጊዜ ያህል ሲጠቀስ በአዲስ ኪዳን ደግሞ 33 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል፡፡ "ኪዳን" ቃሉ "ተካየደ" ተማማለ፣ ቃል ተገባባ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡
 "ምሕረት" የሚለው ቃል ደግሞ ማብራሪያ ሳያሻው ምሥጢሩ ከነዘይቤው ከግእዝ የተወረሰ ነው፡፡ ስለዚህ ኪዳነ ምሕረት ማለት የምሕረት፣ የይቅርታ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ ኪዳን ከተራ ውሎችና ስምምነቶች የበለጠ ጽኑና ቀዋሚ ነው፡፡ ከፍ ያለ ክብደትም አለው፡፡

Friday, November 27, 2015

ጦምህን በሥራ ተግብረህ አሳየኝ፡፡



ሕዳር ፲፯ ቀን ፳፻፰ ዓ/ም


“በጦም ወቅት አንድ ክርስቲያን  በፈቃደኝነት አንድ በጎ ሥራን  ጎን ለጎን ቢፈጽም መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ከሰዎች ምስጋናን ወይም አንዳችን ነገር ሽቶ የሚጦም ከሆነ ግን ጦሙ በእግዚአብሔር ዘንድ የማይወደድ ጦም ይሆንበታል፡፡ ማንኛውም በጎ ሥራ ስንሠራ ለእግዚአብሔር አምላካችን ካለን ፍቅር የመነጨ ይሁን፡፡ እንዲያ ካልሆነ ግን እግዚአብሔርን ደስ ልናሰኝ አይቻለንም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስን ጌታችን በመንጎቹ ላይ ሲሾመው ለእርሱ ያለውን ፍቅር ተመልከቶ ነበር፡፡ እግዚአብሔን የሚያፈቅር ሰው የሚፈጽማቸው የትኞቹም በጎ ሥራዎች በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደዱለት ይሆኑለታል፡፡ ፍጹማንም ናቸው፡፡ ስለዚህም ማንኛውንም በጎ ሥራዎቻችንን ስነሠራ እርሱን በማፍቀር ላይ የተመሠረቱ ይሁኑ፡፡”

Saturday, August 8, 2015

ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር

እንኳን ለጾመ ፍልሰታ በሰላም አደረሳችሁ::
ሰላም ለፍልሰተ ሥጋኪ መካነ ፍሥሐ ምጡቀ በአእባነ ባህርይ ዘተነድቀ ማርያም ደብተራ እንተ ኢትትከደን ሠቀ፡፡ እመቤቴ ማርያም ሆይ ምጡቅና ሩቅ ወደሚሆን የደስታ ቦታ ላረገ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል ፡፡ ይኸውም ኅብሩ ሊመረምሩት በማይቻል ዕንቊ የታነፀ ሕንፃ ይገኝበታል (መልክአ ማርያም)፡፡

Thursday, April 2, 2015

፰. ሆሣዕና



ሆሣዕና ማለት መድኃኒት ማለት ነው ፡፡ ዕለቱ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ሆኖ ሆሣዕና በአርያም እየተባለ በምስጋና በይባቤ ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ የገባበት እለት ነው ፡፡
ቤዛ ዓለም ክርስቶስ በማዕከለ ምድር በቀራኒዮ አደባባይ ተሰቅሎ የአዳምን በደል በመደምሰስ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለህ  ብሎ የገባለትን ቃል ኪዳን ይፈጽምለት ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ ፡፡

Friday, March 27, 2015

፯. ኒቆዲሞስ



ሰባተኛው እሑድ ኒቆዲሞስ ይባላል፡፡ በሌሊት ወደ ጌታ መጥቶ ይማር የነበረው የኒቆዲሞስን ታሪክ የሚያወሳ ስብከት ይሰበካል፤ መዝሙር ይዘመራል፡፡
ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊና የአይሁድ አለቃ ነው፡፡ ፈርሳውያን የጌታ ተቀዋሚዎች ናቸው፡፡ ኒቆዲሞስ በዘመኑ ከነበሩት ተላላቅ የአይሁድ ምሑራን አንዱ ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ የሕግ አዋቂ፤ የሕግ ምሑር ነው፡፡

Friday, March 20, 2015

፮. ገብር ሔር



ስድስተኛው እሑድ ገብር ሔር ይባላል፡፡ ገብር ሔር ማለት መልከም ባርያ ታማኝ አገልጋይ ማለት ነው፡፡ በዚህ ሳምንት የተጣለባቸውን አደራ ተቀብለው በታማኝነት ኃለፊነታቸውን የተወጡ መልካም አገልጋዮች በጌታቸው ፊት መወደሳቸውና መሸለማቸው ይወሳል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የተሰጠውን አደራ ቸል ብሎ ኃላፊነቱን ያልተወጣ እኩይ ሎሌ በጌታው መወቀሱና መቀጣቱ የሚነገርበት የሚወሳበት ሳምንት ነው፡፡
ይህ ታሪክ በማቴዎስ ወንጌል በሰፊው ተብራርቶ ተነግሯል፡፡ አስመ ከመ ብእሲ ዘይነግድ ወጸውኣ አግብርቲሁ ወወሀቦሙ ንዋዮ ይትገብሩ ቦቱ …፡፡ ማቴ. ፳፭ ÷ ፲፬ - ፴ ፡፡

Saturday, March 14, 2015

፭. ደብረ ዘይት



 አምስተኛው እሑድ ደብረ ዘይት ይባላል፡፡ ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ተራራ ማለት ነው፡፡ ደብረ ዘይት ብዙ የወይራ ዛፍ ያለበት ተራራ ሲሆን ስያሜውንም ያገኘው ከዚሁ ነው፡፡ ጌታ በደብረ ዘይት ተራራ ተቀምጦ ስለዳግም ምጽዓት ወይም የዓለም መጨረሻ ለቅዱሳን ሓዋርያቱ አስተምሯል፡፡ ጌታችን ቅዱሳን ሐዋርያቱን አስከትሎ ከመቅደስ ወጥቶ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሲሄደ ሐዋርያት የሰሎሞንን ቤተ መቅደስ ውበት የድንጋዩን አጠራረብ፣ ንድፈ ሕንፃውን፣ የወርቅ ዝምዝሙን፣ የሓር ጭምጭማቱን አይተው ተደነቁ፡፡ ግታም መልሶ፡- ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው። ይህን ውብ ሕንፃ የነደፉ እጆች በሞት ይታሰራሉ፣ ይሁን ድንቅ ንድፍ ያፈለቀ አእምሮ ይያዛል፤ በድንጋይ የተመሰለ ሕንፃ ሰውነታችሁ ይፈርሳ፣ በሞት ይለወጣል፡፡ ይህች በጨረቃ ደምቃ፣ በከዋክብት አሸብርቃ፣ በፀሓይ ሙቃ በውበቷ ምታማልላቸው ዓለም ታልፋለች አላቸው፡፡

Friday, March 6, 2015

፬. መጻጉዕ


                                                                     አልጋህን ተሸክመህ ሂድ፡:


አራተኛው እሁድ መጻጉዕ ይባላል፡፡ መጻጉዕ ማለት በሽተኛ ማለት ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕበራይስጥ ቤተ ሳይዳ ወደምትባል አንዲት መጠመቂያ ወርዶ በልዩልዩ ደዌያት የተያዙ ብዙ ሕሙማንን መፈወሱ የሚወሳበት፣ የሚዘመርበት ሳምንት ነው፡፡ በተለይም ለሰላሳ ስምንት ዓመታት በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዞ የነበረው አንድ ሕሙም በጌታ ቃል ተፈውሶ አልጋውን ተሸክሞ ወደ ቤቱ መሄዱ በቅዱስ መጽሓፍ በጉልህ ተመዝግቧል፡፡

Sunday, March 1, 2015

፫. ምኩራብ




ሶስተኛው እሁድ ምኩራብ ነው ፡፡ በዚህ ሰንበት ጌታ ወደ ምሁራብ ገብቶ ማስተማሩ ይነገራል ፤ ይወሳል ፡፡ ወደ ቅፍረናሆምም ገቡ ፤ ወዲያውም በሰንበት ወደ ምኩራብ ገብቶ አስተማረ ፡፡ ማር .፩ ፥ ፳፰፡፡

Saturday, February 21, 2015

፪. ቅድስት


ሁለተኛው እሁድ ቅድስት ይባላል ፡፡ በተለይ ስለ እለተ ሰንበት ቅድስና ስለሚያወሳ ቅድስት ተብሏል ፡፡ እለተ ሰንበት እለት ዕረፍት እለት ቅድስት ናት ፡፡ በመዝገበ ፍጥረት መጽሐፍ እንደተገለፀው አምላክ ገቢረ ፍጥረታትን አጠናቅቆ አርፎበታል ፡፡ ሰማይና ምድር ሠራዊቶቻቸውም ሁሉ ተፈፀሙ ፡፡ እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ ፤ በሰባተኛውም ቀን ከሥራው ሥራ ዐረፈ ፡፡ እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም ፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና ፡፡ ዘፍ. ፪ ፥ ፩ - ፫ ፡፡

Wednesday, February 18, 2015

፩. ዘወረደ

አንደኛው እሑድ ዘወረደ ይባላል፡፡ኃያል አምላክ የሰው ፍቅር አገብሮት ከሰማየ ሰማያት መውረዱ ፤ ሰው ሆኖ መወለዱ ፤ መሰቀሉ የሚወሳበት ሳምንት ነው ፡፡ ከፈጣሪው ተጣልቶ የነበረ አዳም መታረቁ የሚነገርበት በመሆኑ ዘወረደ ስብከተ ተፋቅሮ ነው ፡፡

Monday, February 16, 2015

ጾም


ጾም (ጦም) ማለት ለተወሰነ ጊዜ እህል ከመብላት ውሃ ከመጠጣት መታቀብ ወይም ለተወሰኑ ወራት ከጥሉላት ምግቦች መከልከል ማለት ነው ፡፡ የጾም ሀይማኖታዊ ትርጉም ሰውነት ከሚያስፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ መከልከል ፤ መወሰን ፤ ለሰውነት የሚያጎመዠውን ነገር ሁሉ መተው ፤ ለሰው ሁሉ መልካሙንና በጎውን ማድረግ ፤ ሰውንም ሆነ እግዚአብሔርን  ከሚያሳዝን ክፉ ሁሉ መራቅ ነው ፡፡ ጾም ፈጣሪን መለመኛ ከሐጢአት ቁራኝነት መላቀቂያ መሣሪያ ስለሆነ በጾም ወራት ሕዋሳት ሁሉ ከክፉ ሥራ መቆጠብ አለባቸው ፡፡ ይጹም ዓይን ፤ ይጹም ልሳን ፤ እዝንኒ ይጹም እምሰሚዓ ሕሱም በተፋቅሮ [1]፡፡ አንድ ክርስቲያን በጾም ወራት ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ ሕዋሳቱን ሰውንና እግዚአብሔርን ከሚያሳዝኑ ክፉ ሓሳቦችና ተግባራት መቆጠብና መከልከል  አለበት ፡፡