Saturday, February 21, 2015

፪. ቅድስት


ሁለተኛው እሁድ ቅድስት ይባላል ፡፡ በተለይ ስለ እለተ ሰንበት ቅድስና ስለሚያወሳ ቅድስት ተብሏል ፡፡ እለተ ሰንበት እለት ዕረፍት እለት ቅድስት ናት ፡፡ በመዝገበ ፍጥረት መጽሐፍ እንደተገለፀው አምላክ ገቢረ ፍጥረታትን አጠናቅቆ አርፎበታል ፡፡ ሰማይና ምድር ሠራዊቶቻቸውም ሁሉ ተፈፀሙ ፡፡ እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ ፤ በሰባተኛውም ቀን ከሥራው ሥራ ዐረፈ ፡፡ እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም ፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና ፡፡ ዘፍ. ፪ ፥ ፩ - ፫ ፡፡
በሐዲስ ኪዳንም እለተ ሰንበት ዕለት ቅድስት እለት ህሪት እለት እምርት ናት ፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ፤ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳባት ዕረፍተ ሥጋ ወነፍስ የተደረገባት ፤ በሲኦል በግዞት ለነበሩት ነፍሳት ነፃነት የተወጀባት እለተ ትንሳኤ እለተ ዕረፍት ናት ፡፡ ይህች ሰንበት ለሰው ሁሉ የድስታ ቀን ናት ፡፡ እረፍተ ሥጋ እረፍተ ነፍስ ተደርጎባታልና፡፡ እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት ሐሤትን እናድርግ፥ በእርስዋም ደስ ይበለን። መዝ. ፩፻፲፰ ፥ ፳፬
እለተ ሰንበት ከእለታት ሁሉ ልቃ እለት ቅድስት እለት ክብርት እለት እምርት ሆና ተከብራለች ፡፡ እለተ ሰንበት ለሰው ተፈጥራለች እንጂ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም ፡፡ የሰው ልጅ የሰንበት ጌታዋ ነው ፡፡ ሰንበት ስለሰው ተፈጥሮአል እንጂ ሰው ስለሰንበት አልተፈጠረም ፤ እንዲሁም የሰው ልጅ ለሰንበት እንኳ ጌታዋ ነው ፡፡ ማር. ፪ ፥ ፳፰
እለተ ሰንበት ሰንበተ አይሁድ ቀዳሚት ሰንበተ ክርስቲያን እሁድ ሁለት ሰንበታት ሳይሆኑ እንደ አንዲት ሰንበት ይከበራሉ ፡፡ እለተ ሰንበት እለተ እረፍት ናት ፡፡ ሰው ከአምስቱ ቀናት ግብረ ሥጋ ሁሉ ዐርፎ ግብረ ነፍስ የሚያከናውንባት እለት ናት ፡፡ ክርስቲያን እለተ ሰንበትን ሲያከብር እንደ አይሁድ በግብዝነት በሩን ዘግቶ ከዘረጋ ሳያጥፍ ከጠፈ ሳይዘረጋ ፤ ከቆመ ሳይቀመጥ ከተቀመጠ ሳይነሳ ሳይሆን በእለተ ሰንበት የሰንበትን ተግባራትን በመከወን ነው ፡፡ የሰንበት ተግባራት መንፈሳዊ ተግባራትን ማከናወን ፣ ሕሙማንን መጠየቅ ፣ የታሰሩትን ዋስ ሆኖ ማስፈታት ፣ የተቸገሩትን መጎብኘት ፣ የተጣሉትን ማስታረቅ … ወዘተ ናቸው ፡፡
እለተ ሰንበት ለእርፍተ መንግሥተ ሰማያት ምልክት ናት ፡፡ እለተ ሰንበት ከግብረ ሥጋ ውጣ ውረድ ስንብተ በኋላ የምትታረፍ እንደሆነ ሁሉ መንግሥተ ሰማያትም የምንወርሳት ከፍፃሜ ዓለም ከአፀደ ሥጋ ስንብት በኋለ ነው ፡፡
ስለዚህ ተግባራት ሰንበትን በመከወን እለተ ሰንበትን እናክብር ፡፡
የእለቱ መዝሙር ፡- ግነዩ ለእግዚአብሔር
ምንባብ ፡- ፩ተሰ. ፬ ፥ ፩ – ፯ ፤ ያዕ. ፪ ፥ ፲፰ - ፳፬ ፤ የሐዋ. ፬ ፥ ፴፬ - ፴፯
ምስባክ ፡- ግነዩ ለእግዚአብሔር ወፀውዑ ስሞ ወንግሮሙ ለአሕዛብ ምግባሮ ሰብሁ ወዘምሩ ሎቱ ፡፡ መዝ. ፩፻፬፩፻፭ ፥ ፩ -
ወንጌል ፡ ማቴ. ፮ ፥ ፲፮ - ፳፭



ወስብሐት ለእግዚእብሔር  

No comments:

Post a Comment