Friday, November 27, 2015

ጦምህን በሥራ ተግብረህ አሳየኝ፡፡



ሕዳር ፲፯ ቀን ፳፻፰ ዓ/ም


“በጦም ወቅት አንድ ክርስቲያን  በፈቃደኝነት አንድ በጎ ሥራን  ጎን ለጎን ቢፈጽም መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ከሰዎች ምስጋናን ወይም አንዳችን ነገር ሽቶ የሚጦም ከሆነ ግን ጦሙ በእግዚአብሔር ዘንድ የማይወደድ ጦም ይሆንበታል፡፡ ማንኛውም በጎ ሥራ ስንሠራ ለእግዚአብሔር አምላካችን ካለን ፍቅር የመነጨ ይሁን፡፡ እንዲያ ካልሆነ ግን እግዚአብሔርን ደስ ልናሰኝ አይቻለንም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስን ጌታችን በመንጎቹ ላይ ሲሾመው ለእርሱ ያለውን ፍቅር ተመልከቶ ነበር፡፡ እግዚአብሔን የሚያፈቅር ሰው የሚፈጽማቸው የትኞቹም በጎ ሥራዎች በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደዱለት ይሆኑለታል፡፡ ፍጹማንም ናቸው፡፡ ስለዚህም ማንኛውንም በጎ ሥራዎቻችንን ስነሠራ እርሱን በማፍቀር ላይ የተመሠረቱ ይሁኑ፡፡”


“አንድ ሰው ምንም እንኳ መላ የሕይወት ዘመኑን በትኅርምት ሕይወት መምራት ያለበት ቢሆንም በዚህ በዐቢይ ጦም ግን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ኀጢአቱን  ለካህን ተናዝዞ ለድሆች ምጽዋትን በማድረግ በአግባቡ ሊጦም ይገባዋል፡፡ እነዚህን ዐርባ የጦም ቀናት በአግባቡ በጎ ሥራዎች አክለንባቸው የጦምናቸው እንደሆነ ቸሩ ፈጣሪያችን ዓመት ሙሉ ባለማወቅ የፈጸምናቸውን ኀጢአቶቻችንን ይደመስስልናል፡፡ (ዮሐንስ አፈወርቅ )

IMG_0715ነገር ግን ብዙዎቻችን በጦም ራስን መግዛትን ከምንለማመድ ይልቅ ለሥጋ ምቾቶቻችን መትጋታችን የሚያስገርም ነው፡፡ እኛ ለራሳችን የተጠነቀቅን መስሎን ደስታን ይፈጥሩልናል የምንላቸውን ምግቦችንና መጠጦችን አብዝተን እንበላለን እንጠጣለን፡፡ … ነገር ግን መጨረሻችን ሕማምና ስቃይ ይሆንብናል፡፡ የሥጋን ምቾት የናቁና በጦም በጸሎት እንዲሁም በትኅርምት ሕይወት መንፈሳዊ ሕይወታቸውን የሚመሩ ቅዱሳን ግን ሥጋና ነፍሳቸውን ሕያዋን አድርገው በመልካም ጤንነት ያኖሯቸዋል፡፡ በተድላና በምቾት ይኖር የነበረው ሰውነታችን በሞት ሲያንቀላፋ ከውስጡ ከሚወጣው ክፉ ጠረን የተነሣ ሽቶ በራሱ ላይ እናርከፈክፍበታለን፡፡ ነገር ግን የቅዱሳን ሰውነት በሕይወት ሳሉም ቢሆን በሞት ከሥጋቸው መልካም መዓዛ ይመነጫል፡፡ ይህ እጅግ ድንቅ የሆነ ነገር ነው ፡፡ እኛ ለሥጋችን ምቾት በመጠንቀቅ ራሳችንን ስናጠፋ እነርሱ ግን ሥጋቸውን ለነፍሳቸው በጦምና በጸሎት በማስገዛታቸው ሥጋቸውን ይቀድሷታል፡፡ የነፍሳቸውን በጎ መዓዛ በመጠበቃቸውም ሥጋቸው መልካም መዓዛን እንድታፈልቅ ሆነች፡፡

ነፍሳችን ንጽሕናዋን በጦም ካልጠበቀች በቀር ቅድስናዋን በኀጢአት ምክንያት ማጣቱዋ የማይቀር ነው፡፡ ያለጦም የነፍስን ንጽሕና ጠብቆ መቆየት የማይሞከር ነው፡፡ ሥጋም መንፈስ ለሆነችው ነፍሳችን መገዛትና መታዘዝ አይቻላትም፡፡ አእምሮአችንም በምድራዊ ምቾቶቻችን ስለሚያዝብን ከልብ የሚፈልቅ ጸሎትን ማቅረብ አይቻለንም፡፡ ስለዚህ ሥጋችን ነፍሳችንን በስሜት ስለሚነዳት ነፍስ እውር ድንብሯ በፍርሃት ወደ ማትፈቅደው ትሔዳለች፡፡ በአእምሮአችን ውስጥ ክፉ ዐሳቦች ተቀስቅሰው ኅሊናችንን ያሳድፉታል፡፡ ስለዚህም የእግዚአብሔር ጸጋ ከእኛ ትወሰዳለች፡፡ ስለዚህም በግልጥ አጋንንት እንደ ፈቀዱት ነፍሳችንን ተሳፍረው ወደ ኀጢአት ይመሩዋታል፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ከጦመ በኋላ ተራበ፡፡ ሰይጣንም ወደ እርሱ ይቀርብ ዘንድ መራቡን ገለጠለት፡፡ እንዲህ በማድረግም ጠላታችንን እንዴት ድል እንደምንነሳው በእርሱ ጦም አስተማረን፡፡ ይህ አንድ ጦረኛ ላይ የሚታይ የአሰለጣጠን ስልት ነው፡፡ ለተማሪዎቹ ጠላትን እንዴት ድል መንሳት እንደሚቻል ሊያስተምር ሲፈልግ ለጠላቱ ደካማ መስሎ ይታየዋል፡፡ ጠላቱም የተዳከመ መስሎት ሊፋለመው ወደ እርሱ ይቀርባል፡፡ እርሱም በተማሪዎቹ ፊት ከጠላቱ ጋር ውጊያን ይገጥማል፡፡ ጠላትን በምን ድል መንሳት እንደሚችል በእውነተኛ ፍልሚያ ጊዜ በተግባር ያስተምራቸዋል፡፡ በጌታ ጦም የሆነውም ይህ ነው፡፡ ጠላት ሰይጣንን ወደ እርሱ ለማቅረብ መራቡን ገለጠ፡፡ ወደ እርሱም በቀረበ ጊዜ የእርሱ በሆነ ጥበብ በመጀመሪያውም፣ በሁለተኛውም፣ በሦስተኛው፣ ፍልሚያ በመሬት ላይ ጥሎ ድል ነሳው፡፡

እየጦምህ ነውን? ጦምህን በሥራ ተግብረህ አሳየኝ፡፡ ድሀ አይተህ እንደሆነ ራራለት፡፡ ወዳጅህ ከብሮ እንደሆነ ቅናት አይሰማህ፡፡ አፋችን ብቻ አይጡም፤ ዐይናችንም፣ ጆሮአችንም፣ እግራችንም፣ እጃችንም፣ የሰውነት ክፍሎቻችንም ሁሉ ክፉ ከመሥራት ይጡሙ፡፡ እጆቻችን ከስስት ይጡሙ፤ እግሮቻችን ኀጢአትን ለመሥራት ከመፋጠን ይጡሙ፡፡ ዐይናችም የኀጢአት ሥራዎችን ከመመልከት ይጡሙ፡፡  ጆሮዎቻችንም ከንቱ ንግግሮችንና ሐሜት ከመስማት ይከልከሉ፡፡ አንደበቶቻችንም የስንፍና ንግግርንና የማይገቡ ትችቶችን ከመሰንዘር ይቆጠቡ፡፡ ወንድማችንን እያማን ከዓሣና ከእንስሳት ተዋጽኦዎች መከልከላችም ምን ይረባናል? (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)

 የካቲት 9/2004 ዓ.ም. በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ -ማሕበረ ቅዱሳን

No comments:

Post a Comment