Monday, January 18, 2016

ተጠምቀ በማይ ከመይትቀደስ ማይ

ጥምቀት ‹‹አጥመቀ›› አጠመቀ ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሳቢ ዘር ነው፡፡ ፍቺውም በገቢር መንከር፣ መድፈቅ፣ መዝፈቅ፤ በተገብሮ መነከር፣ መደፈቅ፣ መዘፈቅ፣ መላ አካልን በውሃ ውስጥ ማስገባት ማለት ነው፡፡
ጥምቀት ከአዳም የወረስነውን ኃጢአትና እኛም የፈጸምነውን በደል ሁሉ ደምስሳ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማሕጸነ ዮርዳኖስ እንደገና ከእግዚአብሔር የምንወለድባት የክርስትና በር ናት፡፡ ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊ*ያይ አይችልም አለው። ኒቆዲሞስም ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው። ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው። ዮሐ. ፫፥፫-፮፡፡