Friday, October 24, 2025

ከቤተልሔም እስከ ግብፅ

በመ/ር ዓለማየሁ ሀብቴ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ክቡራንና ክቡራት የእግዚአብሔር ቤተሰቦች፣ እንደምን ከረማችሁ? ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ ለዚህች ሰዓት ስላደረሰን ስሙ ከዘላለም እስከ ዘላለም የተመሰገነ ይሁን።

ዛሬ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 2 ከቁጥር 1 እስከ 18 ያለውን ታላቅ ታሪክ መሠረት በማድረግ "ከቤተልሔም እስከ ግብፅ" በሚል ርዕስ እንማማራለን። ይህ ታሪክ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት ምሥጢር ብቻ ሳይሆን፣ በውስጡ እጅግ ጥልቅ የሆኑ መንፈሳዊ ትምህርቶችን የያዘ ነው። የሰው ልጅ ሕይወትም እኮ አንድ ጉዞ ነው፤ ልክ እንደ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ እንደ ጻድቁ ዮሴፍ እና እንደ ሰብአ ሰገል የየራሳችን የሆነ ከቤተልሔም እስከ ግብፅ የሚመ ጉዞ አለን። በዚህ ጉዞ ውስጥ ፈተና አለ፣ መከራ አለ፣ ግን ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔር ጥበቃና መዳን አለ።

በዚህ ትምህርት አራት ቁም ነግሮችን እንመለከታለን

1. የሰብአ ሰገል ጉዞ - የእምነትና የፍለጋ ጉዞ

የተወደዳችሁ ምዕመናን፣ ወንጌሉ የሚጀምረው "ኢየሱስም በይሁዳ ቤተልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ" በማለት ነው። እስኪ ለአንድ አፍታ ቆም ብለን እናስብ።

እነዚህ ሰብአ ሰገል ነገሥታት ናቸው፣ ጥበበኞች ናቸው። የኖሩበት ዘመን የዛሬን ያህል ቴክኖሎጂ የለም፣ መንገድ የለም፣ ግን አንድ ምልክት አይተዋል - ኮከብ! ይህ ኮከብ የአይሁድ ንጉሥ መወለዱን ያመለክታቸው ነበር። እነሱ ይህንን ኮከብ በዕውቀታቸው ብቻ ሳይሆን በእምነት ተከትለው ተነሱ። ጉዟቸው ረጅም ነበር፣ አድካሚ ነበር፣ ግን ግልጽ ዓላማ ነበራቸው "የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና።"

እዚህ ላይ ያለው ትልቁ ትምህርት ፈልጎ የማግኘት ምሥጢር ነው። እግዚአብሔርን በንጹሕ ልብ የሚፈልጉት ያገኙታል። ሰብአ ሰገል ሀብት፣ እውቀት፣ ስልጣን ነበራቸው፤ ግን ከዚህ ሁሉ በላይ የሆነውን የሰላም ንጉሥ፣ የነገሥታት ንጉሥ የሆነውን ክርስቶስን ፈለጉ። ስጦታ ይዘውለት ቀረቡ፦

  • ወርቅ፡ ለንጉሥነቱ ክብር የሚገባ ስጦታ።
  • ዕጣን፡ ለመለኮታዊ ክብሩና ለሊቀ ካህንነቱ የሚቀርብ መዓዛ።
  • ከርቤ፡ ለሰውነቱ መከራና ሞት መታሰቢያ የሚያሳይ።

ወገኖቼ፣ እኛስ ዛሬ ለጌታችን ምን ይዘን እንቀርባለን? ወርቅ የሆነ ንጹሕ ልባችንን፣ ዕጣን የሆነ ጸሎታችንን፣ ከርቤ የሆነ ከኃጢአት በመለየት የምንኖረውን ንስሐ ይዘን ቀርበናልን?

2. የሄሮድስ ምላሽ - የምድራዊ ሥልጣን ፍርሃትና ክፋት

ታሪኩ ሲቀጥል ንጉሡ ሄሮድስ የሰብአ ሰገልን ጥያቄ ሲሰማ "ታወከ፥ ኢየሩሳሌምም ሁሉ ከእርሱ ጋር።" ይላል። ለምን ታወከ? ሄሮድስ ምድራዊ ንጉሥ ነው። ሥልጣኑን ከምንም በላይ ይወዳል፤ ስለዚህ "ሌላ ንጉሥ ተወለደ" የሚለው ዜና ለሥልጣኑ ስጋት ሆነበት።

የሄሮድስ ልብ በቅናትና በፍርሃት ተሞላ። ሰብአ ሰገል ንጉሡን ሊሰግዱለት ሲፈልጉ፣ ሄሮድስ ሊገድለው ፈለገ። ክፋቱ ግን በውሸት ተሸፍኖ ነበር። "ሄዳችሁ የሕፃኑን ነገር መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ" አላቸው። ልቡ ግን የግድያ ሴራ ነበረው።

ይህ የሚያሳየን የክፋትን ባህሪ ነው። ክፋት ሁልጊዜ በቅንነት ልብስ ተሰውሮ ይመጣል። ዓለም ዛሬም በሄሮድሶች ተሞልታለች። በውጪ መልካም መስለው በውስጣቸው ግን የክርስቶስን እውነትና ተከታዮቹን ለማጥፋት የሚፈልጉ ብዙዎች ናቸው። የሄሮድስ መንፈስ የሥልጣን፣ የገንዘብ፣ የክብር ፍቅር ነው። ይህ ፍቅር የእግዚአብሔርን ፍቅር ከልብ ያጠፋል።

3. ወደ ግብፅ መሰደድ - የእግዚአብሔር ጥበቃና መለኮታዊ ዕቅድ

ሰብአ ሰገል በሕልም "ወደ ሄሮድስ እንዳትመለሱ" የሚል አምላካ ትዕዛዝ ተቀብለው በሌላ መንገድ ወደ ሀገራቸው ሄዱ። የሄሮድስ ክፉ ዕቅድ ሲከሽፍ፣ የእግዚአብሔር የመዳን ዕቅድ ደግሞ ይገለጣል።

የጌታ መልአክ ለጻድቁ ዮሴፍ በሕልም ታይቶ "ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ" አለው። ዮሴፍም ያላንዳች ማመንታት፣ "ለምን? እንዴት?" ሳይል ወዲያውኑ ታዘዘ። ቅድስት ድንግል ማርያምንና ሕፃኑን ኢየሱስን ይዞ በሌሊት ወደ ግብፅ ተሰደደ።

እስኪ ይህንን ስደት በጥልቀት እናስበው።

  • የሰማይና የምድር ፈጣሪ፣ የነገሥታት ክርስቶስ ስደተኛ ሆነ! ይህ ንኛ ድንቅ ነው? እንደ ምንስ ያለ ትሕትና ነው? ለእኛ ሲል መከራን ተቀበለ።
  • ግብፅ ለምን ተመረጠች? በብሉይ ኪዳን እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ወጥተዋል። አሁን ደግሞ አዲስ ኪዳንን ሊመሠርት የመጣው ዓለም መድኃኒት ራሱ ወደ ግብፅ ሄደ። ይህም "ልጄን ከግብፅ ጠራሁት" የተባለው የነቢዩ ሆሴዕ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው። (ሆሴዕ 11:1)
  • የእግዚአብሔር ጥበቃ፡ ሄሮድስ በቤተልሔም ሰይፉን ሲመዝ፣ እግዚአብሔር ግን ቅዱሱን ቤተሰብ በመላእክቱ እየጠበቀ ወደ ግብፅ አሻገራቸው። ይህም የሚያስተምረን፣ በሕይወታችን የሄሮድስ ሰይፍ ሲመጣብን፣ እግዚአብሔር ምናመልጥበትን "የግብፅ" መንገድ ያዘጋጅልናል ማለት ነው። ያቺ "ግብፅ" ምናልባትም መከራ፣ ችግር ወይም ስደት ልትመስል ትችላለች፤ ግን በስተመጨረሻ የእግዚአብሔር የመዳን እጅ ያለባት ጉዞ ናት።

4. የቤተልሔም ሕፃናት ሰማዕትነት - የንጹሐን ደም ለክርስቶስ ምስክር ሆነ

ሄሮድስ በሰብአ ሰገል እንደተታለለ ሲያውቅ እጅግ ተቆጣ። ቁጣው ወደ አሰቃቂ ጭፍጨፋ መራው። በቤተልሔምና በአካባቢዋ የነበሩትን፣ ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑትን ወንድ ሕፃናት በሙሉ አስገደለ።

ይህ ታሪክ ልብ ይሰብራል። ነገር ግን በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ፣ እነዚህ ሕፃናት የመጀመሪያዎቹ ሰማዕታት ናቸው። ስለ ክርስቶስ ስም ደማቸው የፈሰሰ ንጹሐን ናቸው። እነሱ በሞታቸው የክርስቶስን መከራ ተሳተፉ። "ድምፅ በራማ ተሰማ፥ ልቅሶና ብዙ ዋይታ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፥ መጽናናትም አልወደደችም፥ የሉምና" የተባለው የኤርምያስ ትንቢት ፍጻሜውን አገኘ።

ክርስቶስን መከተል ዋጋ ያስከፍላል። አንዳንድ ጊዜ የሄሮድስ ሰይፍ በሕይወታችን፣ በቤተሰባችን፣ በእምነታችን ላይ ይመዘዛል። ነገር ግን በእምነት የጸኑ፣ መከራውን የታገሡ፣ የሰማዕትነትን አክሊል ይቀበላሉ።

ማጠቃለያ 

ክቡራን ምዕመናን፣ ከቤተልሔም እስከ ግብፅ ያለው ጉዞ፣ የእኛም የክርስትና ሕይወት ጉዞ ነው።

  1. እንደ ሰብአ ሰገል፣ የዓለምን ነገር ወደ ጎን ትተን፣ የእምነትን ኮከብ ተከትለን ክርስቶስን እንፈልግ። ልንሰግድለትና ስጦታችንን ልናቀርብለት ዘወትር እንትጋ።
  2. እንደ ሄሮድስ ልብ፣ በልባችን ያለውን ቅናት፣ የሥልጣን ፍቅርና ምድራዊ ስጋትን እናስወግድ። የክርስቶስ መምጣት ለልባችን ሰላም ሊሆን ይገባል
  3. እንደ ጻድቁ ዮሴፍ፣ የእግዚአብሔርን ድምፅ ለመስማት ጆሮአችንን ክፍት እናድርግ፤ ትዕዛዙንም ያለማመንታት እንፈጽም። "ወደ ግብፅ ሽሽ" ሲለን ለመሄድ ዝግጁ እንሁን።
  4. ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ትህትና ትዕግስትን እንማርልጄ አምላክ ነው፤ ሰማያዊ ንጉሥ ነው ብላ ስደትን አልተሳቀቀችም፤ ከልጇ ጋር ረሃብና ጽሙን፣ ውርጭና ሃሩሩን ታግሳ መክራ ስደትን ተቀበለች እንጂ፡፡ እኛም በሀብታችን፣ በዕውቀታችን፣ በጉልበታችን፣ በዘመድ አዝማድ፣ በስልጣናችን ሳንመካ በእግዚአብሔር ማዳን ብቻ እንታመን፡፡
  5. ጌታችን ስደተኛ እንደሆነ እናስብ። በስደት፣ በችግር፣ በሀዘን ውስጥ ያሉትን ወገኖቻችንን ስናይ የክርስቶስን መከራ እናስብና እንራራላቸው።

በመከራ ውስጥ ስናልፍ "ጌታ ትቶኛል" አንበል። ጌታ ራሱ የመከራን ጽዋ ቀምሷል። በስደት ጎዳና ላይ ከቅድስት እናቱና ከጻድቁ ዮሴፍ ከቅድስት ሳሎሜ ጋር ተጉዟል። ለሰማዕታት ስደትን የባረክ እርሱ የእኛን ስቃይና መክራ ሁሉ ያውቃል፤እንባችንን ያብሳል።

ልዑል እግዚአብሔር የሰብአ ሰገልን እምነት፣ የጻድቁ ዮሴፍን ታዛዥነት፣ የቅድስት ድንግል ማርያምን ጽናት ለሁላችን ያድለን። ከሄሮድስ ክፋትና ሰይፍ ይጠብቀን። በሕይወት ጉዟችን ሁሉ ከቤተልሔም እስከ ግብፅ፣ ከግብፅም እስከ ገነት ድረስ እርሱ መሪና ጠባቂ ይሁነን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!

Thursday, September 10, 2020

ያለፈው ዘመን ይበቃል፡፡ 1ጴጥ. 4÷3

በዘመኑ ህልፈት በመንግሥቱ ሽረት የሌለበት አምጻኤ ዘመናት ልዑለ ባህርይ እግዚአብሔር እንኳን ከዘመነ ዮሓንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ በሰላም በጤና አሸጋገረን፡፡ 

ያለፈው ዘመን 2012 ዓ/ም ለሰው ልጆች በጎ ዘመን አልነበረም፡፡ የኮሮና ቫይረስ ዓለምን ያስጫነቀበት፣ የሰው ልጆችን ህልውና የተፈታተነበት፣ ሰውም አቅሙን (ልኩን) ያወቀበት ዘመን ነበር፡፡

ዛሬ አዲስ ዓመት ለመቀበል ዋዜማዋ ላይ ላለን ኢትዮጵያውያን ደግሞ ችግሩ በጆሮ ላይ ደግፍ ሆኖብን ነበር፡፡ ለሀገር ፍቅር፣ ለወገን ክብር የሌላቸው ክብራቸው በነውራቸው የሆነ ክፉ የክፉ ጥፋት ልጆች እነ ሆድ አምላኩ ከመቼውም የከፉበት፣ ንፁሓን የተገፉበት፣ ክርስቲያነኖች ከእንስሳ ባነሰ ክብር የተገደሉበት፣ የታረዱበት ዘመን ነበር፡፡ 

በአጠቃላይ 2012 ዓ/ም ሀገርና ቅድስት ቤተክርስቲያን የመከራ ቁና የተሸከሙበት የክፉዎች ዘመን ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን 2012 ዓ/ምን ዘመነ ሰማዕታት ብላ ልትሰይመው ይገባል፡፡ እርግጥ ነው መከራ ለክርስቲያን ጌጡ ነው፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ስንመታ እንደ ሚስማር የምንጠብቅ ስለንፅህት ሃይማኖታችን መከራ ስንቀበል ብንደሰት እንጂ በመከራ እንደማንሳቀቅ ጠላት ይወቅ ይረዳ፡፡

ዛሬ ያ ዘመን አርጅቷል፡፡ አዲስ ዘመን ልንቀበል ዋዜማው ላይ ነን፡፡ ያ ዘመን አልፎ አዲስ ዘመን 2013 ዓ/ም መጥቷል፡፡ 

ስለዚህ የአህዛብን ፈቃድ ያደረግንበት፣ የሴይጣንን ሥራ የሠራንበት ያለፈው ዘመን ይበቃል፡፡ 

ክፉዎች፡-ሀገር ያመሳችሁበት፣ ንብረት ያወደማችሁበት፣ ቤተክርስቲያን ያቃጠላችሁበት፣ ሰውን ያስለቀሳችሁበት፣ ሰውን ያፈናቀላችሁበት፣የሰውን ደም ያፈሰሳችሁበት፣ የገደላችሁበት ዘመን ይበቃልና በአዲስ አስተሳሰብ በአዲስ አእምሮ አዲስ ሰው ሆናችሁ አዲሱን ዘመን ተቀበሉ፡፡ 

ክርስቲያኖች፡-ቤተክርስቲያናችሁ የተቃጠላችበት፣ የተሰዳዳችሁበት፣ የተገረፋችሁበት፣ ያለቀሳችሁበት፣ የተገደላችሁበት ያ የመከራ ዘመን ያ ያለፈው ዘመን ይበቃልና እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጋችሁ በአዲስ መንፈስ፣ በአዲስ አእምሮ አዲሱን ዘመን ዘመነ ማቴዎስን ተቀበሉ፡፡

 ልዑል እግዚአብሔር አዲሱን ዘመን ፍቅር የነገሰበት ዘመነ ሰላም፣ ዘመነ ፍስሃ ያድርግልን ፡፡ አሜን                  

Thursday, April 9, 2020

የምኅላ ጸሎት

ዘበእንቲአሃ ለቤተክርስቲያን ተጸፋእከ በውስተ ዐውድ ከመ ትቀድሳ በደምከ ክቡር ዘበእንቲአሃ ዝግሐታተ መዋቅሕት ፆረ ወተዐገሰ ምራቀ ርኩሰ እንዘ አልቦ ዘአበሰ አምላክ ዲበ ዕፀ መስቀል ተሰቅለ


Wednesday, March 25, 2020

እግዚአብሔር ለምን መቅሰፍት ያመጣል? (አባ ገብረኪዳን)

በልብ መታሰቡ በቃል መነገሩ ስሙ ይክበርና ቸሩ አምላካችን እግዚአብሔር ፍጥረቱን ለመጥቀም ስለ ሦስት ነገር መቅሰፍትን ያመጣል።

Wednesday, November 14, 2018

እኔ እንዳደረግሁ እግዚአብሔር እንዲሁ መለሰልኝ ።

(መሳ 1 )
 1 እንዲህም ሆነ፤ ኢያሱ ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች፦ ከነዓናውያንን ለመውጋት ማን በፊት ይወጣልናል? ብለው እግዚአብሔርን ጠየቁ።

 2 እግዚአብሔርም፦ ይሁዳ ይውጣ፤ እነሆ፥ ምድሪቱን በእጁ አሳልፌ ሰጥቻለሁ አለ።

 3 ይሁዳም ወንድሙን ስምዖንን፦ ከነዓናውያንን እንወጋ ዘንድ ከእኔ ጋር ወደ ዕጣዬ ውጣ፥ እኔም ደግሞ ከአንተ ጋር ወደ ዕጣህ እሄዳለሁ አለው። ስምዖንም ከእርሱ ጋር ሄደ።

4 ይሁዳም ወጣ፤ እግዚአብሔርም ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንን በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፥ ከእነርሱም በቤዜቅ ውስጥ አሥር ሺህ ሰዎች ገደሉ።

 5 አዶኒቤዜቅንም በቤዜቅ አገኙትና ተዋጉት፤ ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንንም መቱአቸው።

 6 አዶኒቤዜቅም ሸሸ፤ አሳድደውም ያዙት፥ የእጁንና የእግሩንም አውራ ጣት ቈረጡ።

 7 አዶኒቤዜቅም፦ የእጃቸውና የእግራቸው አውራ ጣት የተቈረጡ ሰባ ነገሥታት ከገበታዬ በታች ፍርፋሪ ይለቅሙ ነበር፤ እኔ እንዳደረግሁ እግዚአብሔር እንዲሁ መለሰልኝ አለ። ወደ ኢየሩሳሌምም አመጡት፥ በዚያም ሞተ።

በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀር ይሉሃል ይህ ነዉ።

Tuesday, September 11, 2018

Time is precious


Time is precious and golden to man. Nothing is as worthy as time is for us. It is the most scarce resource that limited to our life period. It is not static. Rather, running too fast. Time is the greatest gift of the Almighty God to human being as an instrument of good deeds and acts. In time people win gold and loss gold depending on their usage of time. The golden medalist athlete is the one who use time properly.

Saturday, February 24, 2018

ልቡና (ጾም)

ለብሉይ ሰውነታችን ሕዋሳትን ሁሉ እየቃኘ በበጎ ሥራ የሚያውቸው እንደ ንጉሥ የሚያዝ ልቡና አለው፡፡ ያለ ልቡና መሪነት ሕዋሳት ሁሉ ምንም ለሠሩ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ልቡና የሌለው ሰው እብድ ዝንጉዕ ይባላል እንጂ ሕያው ሰው አይባልም፡፡
እንደዚሁም ለሐዲሱ ሰውነታችን ሥራዎቹን የሚያከናውንበት የሥራ መሪው ጾም ነው፡፡ ያለ ጾም መሪነት ምንም በጎ ሥራ ሊሠራ አይችልም፡፡ ይህንንም ወደ ሌላ ሳንሄድ በልተን ጠጥተን በጠገብን ጊዜ የሚሰማን ስሜትና በምንጾበት ወራት የሚሰማን ስሜት ብናመዛዝነው ልንረዳው እንችላለን፡፡

Saturday, October 21, 2017

እኔስ ሰው አማረኝ






እስኪ ቀስቅሷቸው አበው ይናገሩ
የምንኩስና ግብር ምን ነበር ምሥጢሩ
የክርስትና ሕይወት ምን ነበር ተግባሩ
መቃብሩን ክፈቱና አበው ይመስክሩ፡፡