Friday, September 30, 2016

አንብር መስቀልየ ዲበ መስቀል፡፡

በዲ/ን ዓለማየሁ ሀብቴ
መስከረም ፳፩ ቀን ፳፻፱ ዓ/ም

መስቀል በዘመነ ብሉይ የወንጀለኛ መቅጫ መሣርያ የመረገም ምልክት ነበር፡፡ በጥንት ፋርሶችና ሮማውያን ዘንድ ከባድ ጥፋት የፈጸሙ ወንጀለኞች በመስቀል ላይ ተሰቅለው ይቀጡ ነበር፡፡  
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በሞቱ ሞትን ሽሮ፣ ኃጢአተ አዳምን ደምስሶ፣ እዳ በደሉን ክሶ በኃይሉ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ከተነሳ በኋላ ወንጀለኞች ይቀጡበት የነበረው መስቀል ዲያብሎስ የወደቀበት የድል አርማ፣ የክርስቲያኖች ምርኩዝ፣ የነፃነት ምልክት ሆኗል፡፡ ወወሀብኮሙ ትዕምርተ ለእለ ይፈርሁከ ከመ ያምስጡ እም ገጸ ቀስት ወይድኅኑ ፍቁራኒከ (ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ፥ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው። ወዳጆችህ እንዲድኑ መዝ.፶፱÷፬። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በገላ. ፫፥፲፫ ላይ በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን ብሎ አስተምሮናል፡፡
መስቀለ ክርስቶስ እንደ እንቁ እያበራ፤ ድው በመፈወስ ሙት በመስነሳት በሚሠራቸው ተአምራት እየተሳቡ ብዙ አሕዛብ ክርስቲያን መሆን ጀመሩ፡፡ ከአይሁድም እንዲሁ አንዳንዶች ክርስትናን ተቀበሉ፡፡ ይህ የብዙዎች ወደ ክርስትናው መቀላቀል ክርስቶስን በምቀኝነት ተነሳስተው በመስቀል ላይ ሰቅለው የገደሉትን አይሁድን አበሳጫቸው፡፡ እናንተ በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን የአባቶቻችን አምላክ አስነሣው እንዲል የሐዋ.፭፥፴::