በቀሲስ ስንታየሁ አባተ
በኢሳይያስ ዘመን የነበሩ እስራኤላውያን የተናገሩት ቃል ነው። እስራኤላውያን የሚጾሟቸው ብዙ አጽዋማት ነበሯቸው። ለምሳሌ ያህልም ብናይ በሳምንት ሁለት ጊዜ በሳምንት ሁለት ቀን ይጾሙ እንደነበር በሉቃ. ፲፰፥፲፪ ላይ ያለው ቃል ያስረዳል። ማክሰኞና ሐሙስ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ወደ ደብረ ሲና የወጣበትና ከዚያ የወረደበት ዕለት ለማሰብ እስራኤላውያን በሳምንት ሁለት ቀኖች ይጾሙ ነበር። በነቢዩ በዘካርያስ ትንቢትም ላይ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን እንዲህ ብሎ አዝዟቸዋል «የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአራተኛው ወር ጾም የአምስተኛውም የሰባተኛውም የአሥረኛውም ወር ጾም ለይሁዳ ቤት ደስታና ተድላ የሀሤትም በዓላት ይሆናል ስለዚህም እውነትንና ሰላምን ወደዱ።» ተብሎ ለእስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ዘንድ በነብዩ በኩል በተነገራቸው መሠረት የተጠቀሱትን ይጾሙ ነበር። /ዘካ. ፰፥፲፰-፲፱/።