Saturday, March 14, 2015

፭. ደብረ ዘይት



 አምስተኛው እሑድ ደብረ ዘይት ይባላል፡፡ ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ተራራ ማለት ነው፡፡ ደብረ ዘይት ብዙ የወይራ ዛፍ ያለበት ተራራ ሲሆን ስያሜውንም ያገኘው ከዚሁ ነው፡፡ ጌታ በደብረ ዘይት ተራራ ተቀምጦ ስለዳግም ምጽዓት ወይም የዓለም መጨረሻ ለቅዱሳን ሓዋርያቱ አስተምሯል፡፡ ጌታችን ቅዱሳን ሐዋርያቱን አስከትሎ ከመቅደስ ወጥቶ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሲሄደ ሐዋርያት የሰሎሞንን ቤተ መቅደስ ውበት የድንጋዩን አጠራረብ፣ ንድፈ ሕንፃውን፣ የወርቅ ዝምዝሙን፣ የሓር ጭምጭማቱን አይተው ተደነቁ፡፡ ግታም መልሶ፡- ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው። ይህን ውብ ሕንፃ የነደፉ እጆች በሞት ይታሰራሉ፣ ይሁን ድንቅ ንድፍ ያፈለቀ አእምሮ ይያዛል፤ በድንጋይ የተመሰለ ሕንፃ ሰውነታችሁ ይፈርሳ፣ በሞት ይለወጣል፡፡ ይህች በጨረቃ ደምቃ፣ በከዋክብት አሸብርቃ፣ በፀሓይ ሙቃ በውበቷ ምታማልላቸው ዓለም ታልፋለች አላቸው፡፡

ጌታ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፡- ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ የዓለም መጨረሻው ምልክቱ ይህ ነው፡- ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ ብለው በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ፣ ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፣ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳልና፣ ረብም፣ ቸነፈር፣ የምድርም መናወጥ በልዩልዩ ስፍራ ይሆናል፤ በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፣ ይገድሉአችሁማል፣ ስለስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ ብዙዎች ይሰናከላሉ፣ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጠሉ፣ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፣ ብዙ ሓሰተኞች ነቢያትም ይነሳሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ፣ ከዓመጻም ብዛት የተነሳ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች፡፡ እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን እርሱ ይድናል፡፡ ማቴ. ፳፬ ፥ ፩ - ፲፬፡፡
ምልክቱን ነገረን መምጫውስ መቼ ነው? ስለኝ እንደሆነ፡- ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዳስተማሩን የጌታችን መምጫ ወሩ ወርኃ መገቢት፣ እለቱ እለተ ሰንበት፣ ሰዓቱ እኩለ ሌሊት ነው፡፡ ይህ ዓለም የሚያልፈው በተፈጠረበት በውርኃ መጋቢት ነው፡፡ መጋቢት ፳፱ እለተ ሰንበት እንደተፈጠረ በዚሁ እለት፣ በዚሁ ሰዓት በወርኃ መጋቢት ያልፋል፣ ይጠቀለላል፣ ይፈጸማል፡፡ በወርኃ ጳጉሜም መምጫው ነው የሚሉ ሊቃውንት አሉ፡፡ ነገር ግን በወንጌል እንደ ተናገረው የትኛው ወርኃ መጋቢት፣ የትኛይቱ እለተ ሰንበት፣ ትኛይቱስ እኩለ ሌሊት፣ የትኛዋ ጳጉሜ እንደሆነ ከእርሱ ከእግዚአብሔር በቀር የሚያውቅ ማንም ፍጡር የለም፡፡ ማቴ. ፳፬፥ ፴፰ ልብ ይለዋል፡፡
በዓለ ደብረ ዘይት ከጌታችን አባይት በዓለት አንዱ ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያንም ታላቅ በዓሏ ነው፡፡ ለዓለምም መገኛ፣ መፈጸሚያዋ፣ የእድሜ መለኪያዋ ትልቅ አዝመራዋ በዓሏ ነው፡፡ ወርኃ መጋቢት ከአውርኃ ዓመት ሁሉ የተለየ ነው፡፡
መጋቢት ፳፱ እለተ ሰንበት፡-

ሀ. ዓለም የተፈጠረበት (ፍጥረተ ዓለም)
ለ. ጌታችን የተፀነሰበት (ፅንሰተ እግዚእ)
ሐ. የጌታችን ትንሳኤ (ጥንተ ትንሳኤ)
መ. ዳግም ምጽዓት (ህልፈተ ዓለም) ነው፡፡      
ደበረ ዘይት ሁሉም የዘራውን የሚያጭድበት፤ የበተነውን የሚሰበስብበት የመኸር ጊዜ ነው፡፡ ደብረ ዘይት ምርቱ ከገለባ፤ ስንዴው ከእንክርዳድ (ፃድቁ ከኃጥኡ) የሚለይበት አውድማ ነው፡፡ ደብረ ዘይት ሁሉም የሥራውን ዋጋ የሚቀበልበት የፍርድ አደባባይ ነው፡፡ ደብረ ዘይት የምግባር መለኪያ፣ የዋጋ መቀበያ፣ የፍት ርትዕ መስጫ አውድ ናት፡፡ ደብረ ዘይት ለፃድቀን የሚፈረድላቸው በኃጥአን የሚፈረባቸው፤ ይግባኝ የማይጠየቅበት በዘለዓማዊ ንጉሥ በአምላካችን ዘለዓለማዊ ፍትህ የሚሰጥበት የፍርድ ቀን ናት፡፡ ደብረ ዘይት ፃድቀን በአምላካቸው በአደባባይ በክብር ደምቀው የሚመሰገኑበት ኃጥአን በሀፍረት ተሸማቀው የሚቀጡባት እለተ ሐሴት ወእለተ ደይን ናት፡፡
ደብረ ዘይት የእምነት ሚዛን፣ የምግባር መለኪያ፣ የዋጋ መቀበያ፣ የፍርድ አደባባይ፣ የፍትህ አውድ ናት፡፡ በዚያች ቀን ፈራጆች በፍርድ ዙፋን ፊትይቆማሉ፣ ደኞችም ይዳኛሉ፣ ሹማምንት ይሻራሉ፣ ነገሥታት በስልጣናቸው ከፍድ ኤድኑም፡፡ ይህ ዓለም በእለተ ምፅዓት በደብረ ዘይት አደባባይ ይዳኛል፡፡
 ይህች ፍትህ የማታውቅ፣ ፍርድ የተጓደለባት፣ ደሃ የተበደለባት ዓለም በእለተ ምፅዓት ይግባኝ የማይባልበት የመጨረሻ ውሳኔ ፍትህ ርትዕ በእግዚአብሔር ታገኛለች፡፡ እለተ ምፅዓት ከአምስቱ አእማደ ምሥጢራት እንዱ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ምስጢረ ትንሳኤ ሙታን ብለዋለች፡፡ ሥጋቸው አፈር ትቢያ ሆኖ፣ አጥንታቸው ተበታትኖ የነበሩ ምውታን ተነስተው እንደየ ሥራቸው ዘለዓለማዊ ፍርድ የሚቀበሉበት ምሥጢር ነው፡፡ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ነገረ ሕይወት ዘለዓለም ይባላል፡፡
ይህች እለት አስደሳችም አስጨናቂም ናት፡፡ ፃድቃን ሲደሰቱ ኃጢአን ያዝናሉ፣ ፃድቃን ሲሸለሙ ኃጢአን ለዘለዓለም ይቀጣሉ፡፡ ጌታችን የምጥ ጣር መጀመርያውን ሲያስረዳ፡- ‹‹በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና። እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ›› ይብሏል።
እለተ ምፅዓት ከአእማደ ምሥጢራት አንዱ ምሥጢር ቢሆንም በሕቡዕ የሚደረግ ስውር ምሥጢር አይደለም፡፡ ፍጡራን በሙሉ የሚያዩት የሚሳተፉበት ገሃዳዊ ምሥጢር ነው፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት በመዝሙር ፵፱፥፪-፫ ላይ እግዚአብሔርሰ ገሀደ ይመጽዕ ወአመላኪነሂ ኢያረምም እሳት ይነድድ ቅድሜሁ (እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል። አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም እሳት በፊት ይቃጠላል፥ በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ) ብሎ ዘምሯል፡፡ በአይሁድ የተናቀው የክብር በለቤት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የናቁት፣ የተፉበት፣ የገረፉት፣ የወጉት፣ በመስቀል ላይ ሰቅለው ቸነከሩት ሁሉ እያዩት በቅዱሳን መላእክት ታጅቦ በግርማ ይመጣል፡፡ እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ አንዲል ራዕ. ፩፥ ፯። ጌታችንም ይህ ምሥጢር ገሃዳዊ ምሥጢር መሆኑን ሲያስረዳ፡- እነሆ፥ በበረሀ ነው ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ እነሆ፥ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና ብሎናል፡፡ ክርስቶስ አየሱስ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንጂ ጩኸት በተሞሉ አደራሾች አይገኝም፡፡ ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያለው ምሥጢር በሚፈጸምባት፣ ሥጋ ወደሙ በሚፈተትባት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንጂ ጩኸትና ፉጨት በሚያውኩት አደራሽ አይገኝም፡፡
ያን ጊዜ ሁሉ ይሸበራል፣ የሰማያት ኃይልም ይናወጣሉ፡፡ ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ።
የፍርድ አሰጣቱም ሂደት ምን እንደሚመስል ከወዲሁ ነግሮናል፡፡ ሰው በምግባሩ እንደሚለይ፣ በሥራው እንደሚፈረድለት ወይም እንደሚፈረድበት አስተምሮናል፡፡ ሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያበት የሚገባ አይደለም። በዚያ ቀን ብዙዎች። ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም። ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ። ማቴ. ፯፥ ፳፩- ፳፫፡፡
ደብረ ዘይት ፃድቃን በፀናች ሃይማኖት በበጎ ምግባር ኣሸብርቀው በአምላካቸው ቀኝ ቆመው ኑ የአበቴ ብሩካን ወደ ተዘጋጀላቸው ዘለዓለማዊ እረፍት ግቡ ሲባሉ ኃጥኣን በክህደት ልቡናቸው በከፋ ሥራቸው አፍረው ከአምላከቸው ግራ በመሆን እናንተ ርጉማን አላውቃችሁም ለሴይጣንና ለሠራዊቱ ወደ ተዘጋጀ የዘለዓለም ፍደ ግቡ የሚባሉባት የሀዘንና የደስታ ቀን ናት፡፡
በእግዚአብሔር የፍርድ ዙፋን ፊት እንዳናፍር በሀይማኖት ፀንተን፣ በምግባር ታንፀን፣ በትሩፋት አጊጠን መኖር ይገባናል፡፡ የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጕብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ ፀሐይና ብርሃን ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ፥ ደመናትም ከዝናብ በኋላ ሳይመለሱ… መክ. ፲፪፥ ፩- ፪፡፡ በእርጅና፤ በበሽታ እግርና አጆችህ ሳይታሰሩ፣ ዐይኖችህ ሳይፈዙ፣ ጆሮዎችህ መስማት ሳይሳናቸው፣ እውቀት አእምሮህ ሳይደበዝዝ፣ ጉልበትህ ሳይደክም፣ ውበትህ ሳይጠወልግ አባረህ መያዝ፣ ሮጠህ ማምለጥ፣ አርቀህ ማየት በምትችልበት ጤና ሳለህ በጉብዝና ወራት ለፈጣሪህ ተገዛ፡፡ በሕግ በአምልኮ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቅረብ፡፡   

የሁላችን እለተ ምፅአታችን እለተ ሞታችን መሆኑን አውቀን በሃይማኖት ፀንተን በጎ ሥራ በመሥራት በቀኝ ለመቆም እንትጋ የማኅቶት የሳምንቱ መልእክት ነው፡፡
የእለቱ መዝሙር፡- እንዘ ይነብር እግዚእነ
ምንባብ፡-፩ተሰ. ፩ ፥ ፲፫ - ፲፰ ፤ ፪ጴጥ. ፫ ፥ ፯ - ፲፭ ፤ የሐዋ. ፳፫ ፥ ፩ – ፰
ምስባክ ፡- እግዚአብሔርሰ ገሀደ ይመጽዕ ወአመላኪነሂ ኢያረምም እሳት ይነድድ ቅድሜሁ ፡፡ መዝ. ፵፱፥፪-፫


ወንጌል ፡- ማቴ. ፳፬ ፥ ፩ - ፲፭
ወስብሐት ለእግዚእብሔር 

No comments:

Post a Comment