ሰባተኛው እሑድ ኒቆዲሞስ ይባላል፡፡
በሌሊት ወደ ጌታ መጥቶ ይማር የነበረው የኒቆዲሞስን ታሪክ የሚያወሳ ስብከት ይሰበካል፤ መዝሙር ይዘመራል፡፡
ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊና የአይሁድ አለቃ
ነው፡፡ ፈርሳውያን የጌታ ተቀዋሚዎች ናቸው፡፡ ኒቆዲሞስ በዘመኑ ከነበሩት ተላላቅ የአይሁድ ምሑራን አንዱ ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ የሕግ
አዋቂ፤ የሕግ ምሑር ነው፡፡
የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነትና አደራ በትጋት የሚወጣ ትጉህ ዜጋ ነውና ቀን በዕውቀቱ ሕዝቡን ሲያገለግል፣
ሲያስተምር፣ ሲመክር፣ ሲገስጽ ውሎ ሌሊት ሌሊት በድብቅ ወደ ጌታ እየመጠ ከእውነተኛው መምህር ቀለ ሕይወትን ይማር ነበር፡፡ የዮሓንስ
ወንጌል ምዕራፍ ሶስትን ይመልከቱ፡፡ ነቆዲሞስ ብልህ ምሑር ነው፡፡
የሚያስተምራቸው ወገኖቹ አይሁድ
(ፈርሳውያን) የጌታ ተቀዋሚዎች ስለነበሩ እንዳይቃወሙት ቀን እነርሱን ሲያስተምር ውሎ ሌሊት በድብቅ ወደ ጌታው ሄዶ ይማር ነበር፡፡
ሰው ፈጣሪውን ከፈለገ ከአምላኩ የሚለይ ማገጃ አጥር፣ መወሰኛ ድንበር፣ መገደቢያ በር የለም፡፡ ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል?
መከራ፣ ወይስ ጭንቀት፣ ስደት፣ ወይስ ረሃብ፣ ወይስ ራቆትነት፣ ወይስ ፍርሃት፣ ወይስ ሴይፍ? ሮሜ. ፰፥ ፴፭
የኢየሩሳሌም ሸንጎ ጌታችን መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስን በምቀኝነት ሊከሰው ሲፈልግ በሙያው ይከላከል ነበር፡፡ ዮሓ. ፯፥ ፵፭- ፶፪፡፡ ኒቆዲሞስ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል
ላይ ተሰቅሎ ከሞተ በኋለ ለመግነዙ የሚሆን ንጥር ከርቤና የእሬት ቅልቅል (ልዩ ቅመም) አዘገጅቶ እንደ አይሁድ ልማድ የክርስቶስን
ቅዱስ ሥጋ ከአርማቲያሱ ዮሴፍ ጋር በመሆን ገንዘው በአዲስ መቃብር ቀብረዋል፡፡ ዮሓ. ፲፱፥ ፴፷- ፴፱ ፡፡
ውድ ወገኖቼ፡-ከኒቆዲሞስ ሕይወት
ምን እንማራለን? አንደ ኒቆዲሞስ ያምላካችን ፍቀር በልባችን ነዶ፣ እንቅልፍ ነስቶን ዘውትር እንተጋለን?
አባቶቻችን ፍቅሩ አገብሮአቸው ሌሊት
በሰአታት፣ ነግህ በኪዳን በቅዳሴ አምላካቸውን ያገለግላሉ፡፡ እንደ ቅዱሳን መላእክት ለእግዚአብሔር ሲዘምሩ ስሙን ሲቀድሱ ይኖራሉ፡፡
እኛ ግን ደከሞችን ነን፡፡ ድካማችን
ያመለካከት ችግር፣ የምግባር ጉድለት ነው፡፡ ብዙዎቻችን ትምክህተኞች ነን፡፡ ምንም ሳንይዝ በባዶ እንታበያለን፡፡ ሳንማር አዋቂዎች
ነን እንላለን፡፡ ክብር ሳይኖረን የከበሬታ ወንበር እንፈልጋለን፡፡ እኛ በባዶ ስንኩራራ ወደ ኋለ ቀርተናል፡፡ ብዙዎች ኋለኞች ቀድመውናል፡፡
ዘመኑን መዋጀት አልተቻለንም፡፡ የካህን ዘር ነኝ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪ ነኝ፣ የእገሌ ማሕበር አገልጋይ ነኝ፣ የጽዋ አባል
ነኝ፣ ሰባኬ ወንጌል ነኝ፣ ዘማሪ ነኝ፣ ዲያቆን ነኝ፣ ቄስ ነኝ፣ መለኩሴ ነኝ እንላለን፡፡ ነገር ግን የአገልጎሎት ፍቅር፣ የዘማሪ
ሥርዓት፣ የሰባኪ ሕይወት፣ የካህን ምግባር የለንም፡፡ አገልጎሎታችን ሁሉ ገንዘብን፣ ዝናን ያማከለ ነው፡፡ የውዳሴ ክንቱ አባዜ
ተጠናውቶናል፡፡ ስማችን በድምፅ ማጉልያ በመድረክ ላይ ካፍ ብሎ ካልታወጀ አምስት ሣንቲም መስጠት አንፈልግም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ.፲፪፥
፲፮-፲፰ ላይ እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች
የሆናችሁ አይምሰላችሁ። ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። ቢቻላችሁስ በእናንተ
በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ ብሎ ትህትናን ያስተምረናል።
ክርስቲያን ነን፣ የክርስቶስ ነን
እንላለን፡፡ በምግባራችን ግን ከክርስቶስ ሕግ፣ ከክርስቶስ ፍቅር ውጭ ነን፡፡ ክርስቶስ የሞተለትን ሰው እናሳዝነዋለን፡፡ በሓሜት፣
በተንኮል፣ በሀሰት ምስክርነት እንገለዋለን፡፡ የታመመውን አንጠይቅም፣ የታሰረውን አናስፈታም፣ የተራበውን አናጎርስም፣ የታረዘውን
አናለብስም፣ ያዘነውን አናረጋጋም፣ የደከመውን አናበረታታም፣ የባዘነውን አንመልስም፣ የጠፋውን አንፈልግም፣ ደሃ አንታደግም፣ ፍትህ
አናደርግም፡፡ የክርስትና ስም እንጂ ግብር የለንም፡፡ የቤተ ክርስቲያን አባል ነን እንላለን፡፡ ሕይወታችን ግን ከቤተ ክርስቲያን
ሥርዓት ውጭ ነው፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ
ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ /፪ጴጥ.፩፥፲/ እንዳለን ለተጠራንበት ሕይወት በሰዓት ሳንወሰን፣ ችግር ሳይበግረን እንደ ኒቆዲሞስ
እንትጋ፡፡ የጠራን ትሁትና ቅዱስ ነው፡፡ የተጠራነው ደግሞ በትህትና ለሚገኝ ክብረ ቅድስና ነው፡፡ ጌታችን ኃያል ሆኖ ሳለ በትህትና
ዝቅ ብሎ የሐዋርያትን እግር አጥቧል፡፡ እርሱ ጌታ መምህረ ትህትና ነውና አትህቶ ርእስ አስተማረን፡፡
እኛ ቀረብን እንጂ እግዚአብሔር
ግን ሰው አላጣም፡፡ በስውር የሚያመልኩት ብዙ ኒቆዲሞሶች አሉት፡፡ እኛ ከአህዛብ የመደብናቸው ዓለማውያን የምንላቸው፣ በሕይወትም
በምግባርም ከኛ የተሸሉ ትሁታን አገልጋዮች አሉት ፡፡
በስም ብቻ ሳይሆን በእውነት ክርስቲያኖች
እንሁን፣ ራሳችንን ዝቅ አድርገን በትህትና እናገልግል፡፡ ለአግልግሎት ከመነሳታችን በፊት ጸጋችንን እንወቅ፣ ለማስተማር ከመቆማችን
በፊት እንማር፣ ሌላውን ከመምከራችን አስቀድመን እንመከር፡፡ በአንደበት ብቻ ሳይሆን ከልባችን እንደ ቅዱሳን አበው የማንጠቅም ባሮች
ነን እንባል የሳምንቱ የማኅቶት መልእክት ነው፡፡
የእለቱ መዝሙር፡-ሆረ ሀቤሁ
ምንባብ፡-ቆላ. ፫፥ ፱- ፲፯፣
፩ዮሓ. ፬፥ ፩- ፰፣ የሓዋ. ፭፥ ፳፩- ፳፮
ምስባክ፡-መንፈቀ ሌሊት እትነሣእ
ከመ እግነይ ለከ በእንተ ኩነኔ ጽድቅከ ከማሆሙ አነ ለኩሎሙ እለ ይፈርሁከ፡፡ ፩፻፲፺(፩፻፲፱)፥ ፷፪- ፷፫
ወይም
መዝ. ፲፮፥ ፫- ፬ ሐወጽከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ፡፡ አመከርከኒ ወኢረከብከ
ዓመፃ በላዕልየ፡፡ ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ እጓለ እመሕያው በእንተ ቃለ ከናፍርከ፡፡
ወንጌል፡-ዮሓ. ፫ ፥ ፩- ፲፯
ወስብሐት ለእግዚእብሔር
No comments:
Post a Comment