ስድስተኛው እሑድ ገብር ሔር ይባላል፡፡
ገብር ሔር ማለት መልከም ባርያ ታማኝ አገልጋይ ማለት ነው፡፡ በዚህ ሳምንት የተጣለባቸውን አደራ ተቀብለው በታማኝነት ኃለፊነታቸውን
የተወጡ መልካም አገልጋዮች በጌታቸው ፊት መወደሳቸውና መሸለማቸው ይወሳል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የተሰጠውን አደራ ቸል ብሎ ኃላፊነቱን
ያልተወጣ እኩይ ሎሌ በጌታው መወቀሱና መቀጣቱ የሚነገርበት የሚወሳበት ሳምንት ነው፡፡
ይህ ታሪክ በማቴዎስ ወንጌል በሰፊው
ተብራርቶ ተነግሯል፡፡ አስመ ከመ ብእሲ ዘይነግድ ወጸውኣ አግብርቲሁ ወወሀቦሙ ንዋዮ ይትገብሩ ቦቱ …፡፡ ማቴ. ፳፭ ÷ ፲፬ -
፴ ፡፡
በዚህ ገጸ ንባብ ላይ እንደተብራራው
ለረጅም ጊዜ ወደ ሌላ ሀገር የሚሄድ ሰው አገልጋዮቹን ጠርቶ ከሄደበት እስኪመለስ ድረስ በንዘቡ ነግደው፣ አትርፈው፣ ሀብቱን አበርክተረው
እንዲቆዩት እንደየአቅማቸው ለአንዱ አንድ፣ ለአንዱ ሁለት፤ ለአንዱም አምስት መክሊት በአደራ ሰጣቸው፡፡ ከብዙ ዘመናት በኋላ ከሄደበት
ተለምሶ ገንዘቡን ከነትርፉ እንዲመልሱለት ሲቆጣጠራቸው ታማኝነት ከጎደለው ከአንዱ ሀኬተኛ ባርያ በስተቀር፤ ሁለቱ አገልጋዮች በትጋት፣
በታማኝነት፣ ወጥተው፣ ወርደው፣ እጥፍ አትርፈው ለጌታቸው በማስረከብ ተሸልመዋል፡፡
የዚህ ምሳሌ ትልቁ ምስጢር በአጭሩ
እንደሚከተለው ነው፡፡
Ø ወደ
ሌላ ሀገር የሚሄድ በለፀጋ የተባለው ጌታችን መድጋኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
Ø ሌላ
ሀገር የተባለው ወደ ሰማይ ማረጉን መናገር ነው፡፡
Ø መመለሱ
ዳግም ለፍርድ መምጣቱን ያጠይቃል፡፡
Ø መክሊት ትምህርት (እውቀት) ነው፡፡
Ø አምስትና ሁለት መክሊት ተሰጥቶአቸው
ያተረፉት ፍጹም ትምህርት ተምረው፣ መክረው፣ አስተምረው፤ ራሳቸውን አስመስለው ያወጡ ደቀ መዛሙርት ያበዙ መምህራን ናቸው፡፡ አንድም
በማንኛውም የሙያ ዘርፍ ሀገር ወገን እንዲያገለግል የተጣለበትን አደራ በታማኝነት በትጋት የተወጣ ተማኝ አገልጋይ ነው፡፡
Ø በለአንድ ፍጹም ትምህርት ተምሮ
አላውያን ስለት እሳት አሳይተው ቢያስቱኝ፣ መናፍቃን ተከራክረው ምላሽ ቢያሳጡኝ ብሎ ፈርቶ ሳያስተምር ሀይማኖቱን
በልቡ የያዘ ሰነፍና ፈሪ ሰው ነው፡፡
እኛም ዐረፍተ ዘመን እስከሚገታን ድረስ ነግደን ልናተርፍ፣ መክሊት ልናበረክት
ከጌታችን ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሠርቶ የማትረፍ ኃላፊነት የተቀበልን በለአደራዎች ነን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ፩ኛ
ቆሮ. ፯፥ ፯ ላይ እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ለራሱ የጸጋ ስጦታ አለው እንዳለ ሳይሰስት በልግስና ከሚሰጥ ከእግዚአብሔር እንደየአቅማችን
የተሰጠን መክሊት በሁላችን ዘንድ አለ፡፡
በለጸጋው የተትረፈረፈ ሀብት የተሰጠው
እንደነዌ በንፉግነት ወጥመድ ተይዞ ሲቆናቆን በገንዘቡ ምንም ሳይሠራ፣ አዱኛውን ሳይጠቀምበት፣ ንብረቱን ትቶ እርቃኑን ወደ መቃብር እንዲወርድ ሳይሆን እንደ ደጉ አበት እንደ አብርሃም
ለተራባ አጉርሶ፣ ለታረዘ አልብሶ፣ እንዲያገለግልበት ነው፡፡ ለክፉ ቀን ስንቅ እንዲሆነው ወርቁ ሳይበልዝ፣ ብሩ ሳይዝግ ገዝገቡን
በሰማያዊ መዝገብ በከርሠ ነደያን እንዲያከማች ነው፡፡ ይህ ጸጋ የተሰጠው ከሀብቱ ከፍሎ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲያሠንፅበት፣
መንፈሳዊ ተግባራትን እንዲያከናውንበት፣ ሀገሩን አልምቶ ወገኑን እንዲጠቅምበት ነው፡፡ በረከት ብድር የተሠጠው፣ አዝመራው የሆነለት፣
በረቱ የሞላለት ገበሬ፣ ወረቱ የተመለሰለት ነጋዴ እግዚአብሔር በበረከት የጎበኛቸው ገበሬው አሥራት በኩራቱን አውጥቶ፣ ቀዳሚያቱ
ሰጥቶ፤ ነጋዴው ከወረቱ አሥራቱን አውጥቶ፣ ለችግረኞች ራርተው የተቀበሉትን መክሊት እንዲያትርፉ ነው፡፡
ስልጣን የተሰጣቸው ሹማምንት የተሸሙት በስልጣናቸው እንዲመጻደቁ አይደለም፡፡
ሹመት ስልጣናቸው የጌትነት ሳይሆን የእረኝነት የአገልጋይነት ሹመት ነው፡፡ ነገሥታትም እግዚአብሔር ያስነሳቸው በሕዝብ ላይ የሚነግሡ
አይደሉም፡፡ ዳዊት ነግሠ ለእስራኤል እንዲል ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ፡፡ ለሕዝብ የሚነግሡ የሀገር ጠባቂዎች የሕዝብ እረኞች ናቸው፡፡
እረኝነት፣ ጠባቂነት፣ አገልጋይነት ነግደው ሊያተርፉ፣ ሊያበዙ፣ ሊያበረክቱ ከልዑል እግዚአብሔር የተሰጣቸው በኋላ ከነትርፉ የሚመልሱት
መክሊታቸው ነው፡፡ ደኞች በፍርድ ዙፋን ላይ የተሰየሙት ፍርድ እንዳይጓደል ደሃ እንዳይበደል ነው፡፡ ፊት አይተው የሚያዳሉ፣ ትክክለኛ
ሚዛን የሌላቸው በዘመድ አዝማድ የሚፈርዱ፣ ጉቦ የሚበሉ ፍርደ ገምድል ከሆኑ በተሰጣቸው በክሊት ነግደው አላተረፉምና ነገ ካባቸውን
አውልቀው በእውነተኛው ዳኛ በክርስቶስ የፍርድ ዙፋን ፊት ሲቀርቡ ከበርተ ሀከይ ተብለው ይፈረድባቸዋል፡፡
ጉልበት ያላቸው ወጣቶች አባረው
መያዝ፣ ሮጠው ማምለጥ እንዲችሉ ብርታት የተሰጣቸው በጉልበታቸው ደካሞችን እንዲያግዙ፣ አረጋውያንን እንዲጦሩበት ነው፡፡ ጉልበታቸው
በጉብዝና ወራት ፈጣሪያቸውን እንዲያገለግሉበት የተሰጣቸው ጸጋ ትርፍ የሚፈለግበት በክሊት ነው፡፡ ጤነኞች መልካም ጤንነት የተሰጣቸው
ሕሙማንን እንዲያስታምሙ፣ አጉራሽ አልባሽ የሌላቸውን እንዲጎበኙ ነው፡፡ ጤናችን ነግደን እንድናተርፍ ከእግዚአብሔር የተሰጠን መክሊታችን
ነው፡፡
እውቀት ያላቸው ምሁራን አስተዋይ
ልቡና፣ ብሩህ አእምሮ፣ ጥበብ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ የተሰጣቸው በእውቀት ማጣት በሥጋ የደከሙ በመንፋስ የደሃዩ ነደያነ ሥጋ ወመንፈስ
አሕዛብን እንዲያስተምሩ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው እውቀት አላዋቂዎችን ወደ እውቀት እንዲጠሩ፣ ባላቸው ጥበብ በድቅድቅ አለማወቅ
ጨለማ ያሉትን ወደ ሕይወት ብርሀን እንዲያደርሱ፣ ድኩማነ ሥጋ ወመንፈስ ኃጢአንን ወደ ንሥኀ ጠርተው ጠቢባን እንዲያደርጉአቸው የተጠሩ
ሹማምንተ አእምሮ ናቸው፡፡ ምሁራን ፈጣሪ ጥበቡን የሰጣቸው በለጋስነት ስለሆነ ዘነሰእክሙ በከንቱ ሀቡ በከንቱ (በከንቱ የተቀበላችሁትን
በከንቱ ስጡ) ብሎ ብዙ እንዲያተርፉ አዞአቸዋል፡፡ የማያስተምር ምሑር የማይጠቅም የጋን ውስጥ ማብራት ነው፡፡ በተሰጠው መክሊት
ባለመሥራቱ፣ የሚጠበቅበትን ትርፍ ባለማትረፉ በሊቀ አእምሮ በጥበብ ባለቤት በእግዚአብሔር ዘንድ ይጠየቃል፡፡
ካህናት በቤተ ክርስቲያን የተሸሙት
ሕዝብን ለማገልገል ነው፡፡ ያለወቀውን ለማስተማር፣ ለደከመው ለመጸለይ፣ ያጠፋውን ለመገሰጽ፣ የባዘነውን ለፈለግ፣ የተበተኑትን ለመሰበሰብ፣ የተጣሉትን ከሰውም ከእግዚአብሔር ለማስታርቅ፣ ከተበደሉ ጎን ቆም ፍትህ ለማስገኘት፣ ለሰው ሁሉ አባታዊ ፍቅር ሰጥቶ በመልካም እረኝነት አባግአ ክርስቶስን ለማሰማራት ነው፡፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፕሮጀክቱ በሰው ልብ ላይ ነው፡፡ ልማቱ፣ ግንባታው በሰው አእምሮ ውስጥ ነው፡፡ ካህናት
ከጌታ የተቀበሉት መክሊታቸው ይህ በመሆኑ አትርፎ ለመገኘት፣ በክርስቶስ ፊት ቀርቦ ለመሸለም መትጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሰባክያነ ወንጌል በተቀደሰ አደባባይ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ የሚቆሙት ዝና ለመናኘት፣ ሀብት ለማካበት፣
ንግድ ለማስፋፋት አይደለም፡፡ ያለምንም ክፍያ ከእግዚአብሔር በከንቱ የተቀበሉትን ቅዱስ ወንጌል በከንቱ ሰጥተው አሕዛብን ከአምልኮተ
ጠኦት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፤ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ለመመለስ ነው፡፡ በተቀበሉት መክሊተ ወንጌል ሰላሳ፣ ስልሳ፣
መቶ የጽድቅ ፍሬ አፍርተው በእግዚአብሔር ዘንድ መልካም ታማኝ ባርያ/አገልጋይ ተብለው ለመሸለም ነው፡፡
ዘማርያን በቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ ቃለ እግዚአብሔርን አሰምተው፣ ስመ እግዚአብሔርን ጠርተው የሚዘምሩት ከሴት ለመሸጥ፣
በቤተ ክርስቲያን ስም ለመነገድ፣ በዓም ሰልፍ ውስጥ አልሆን ያላቸውን ሥጋዊ ፍላጎት ለማሳካት አይደለም፡፡ በዝማሬ ባካበቱት ሀብት
ቤታቸው እንዲሞላ፣ዝናቸው እንዲናኝ፣ ስማቸው እንዲገን ሳይሆን እግዚአብሔር እንዲከብርበት፣ ምእመናን እንዲማሩበት፣ እንዲገሰጹበት፣
እንዲጸልዩበት ነው፡፡ የመዝሙሩ የመዘመሩም ዓላማ በዚህ መልክ ካልተቃኘ መክሊቱ
ባክኗል፣ ዘማሪው ከስሯል፡፡ መክሊቱን በሰጠው ጌታ ዘንድ ምስጋና ሳይሆን ወቀሳ፣ ሽልማት ሳይሆን ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡
ምሁር የሆነ እርሱ ጠቢብ እንደ
መዝሙረኛው ዳዊት ከመ እንግር ፈቃድከ መከርኩ አምላኪየ፡፡ ወሕገከኒ በማእከለ ከርስየ፡፡ ዜኖኩ ጽድቀከ በማሕበር ዐቢይ፡፡ (አምላኬ
ሆይ፥ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ፥ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው። በታላቅ ጉባኤ ጽድቅን አወራሁ መዝ. ፴፱፥፰- ፱ ብሎ መዘመርና ለድኩማነ
አእምሮ ብርሀን ሆኖ መገነት ያስፈልጋል፡፡ ብርሀነ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ. ፲፪፥፮- ፰ ላይ እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ
ስጦታ አለን፤ ትንቢት ቢሆን እንደ እምነታችን መጠን ትንቢት እንናገር፤ አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ፤ የሚያስተምርም ቢሆን
በማስተማሩ ይትጋ፤ የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛ በትጋት ይግዛ፤ የሚምር በደስታ ይማር
በማለት ይመክረናል።
ውድ ክርስቲያኖች፡- ይህን የተጣለብን
ታላቅ አምላካዊ አደራና ኃላፊነት በታማኝነትና በትጋት እየተወጣን ያለን ስንቶቻችን ነን?
ሁላችንም ከሁሉ አሰቀድመን ለሕሊናችን
በመታዘዝ ሙያዊ ሥነምግባራችንን በታማኝነት መወጣት ይጠበቅብናል፡፡ አብረን ለምንኖረው ቤተሰባችን፣ በመሥርያ ቤት በሙያ ወይም በጉልበት
ለምናገለግለው ማሕበረሰብና መንግሥት (ለወገን፤ ለሀገር)፣ ለሃይማኖታችን፣ ለቤተ ክርስቲያናችን፣ ለፈጣሪያችን እውነተኛ ታማኝ አገልጋዮች
መሆን ይጠበቅብናል፡፡
ሳምንቱ የሽልማትና የቅጣት ሳምንት
ስለሆነ ጌታችን ለፍርድ ሳይመጣ ለሽልማት እንትጋ የሳምንቱ የማኅቶት መልእክት ነው፡፡
እለቱ መዝሙር፡- መኑ ውእቱ ገብር
ሔር
ምንባብ፡-፩ቆሮ. ፬፥ ፩- ፮ ፤
፪ጴጥ. ፩ ፥ ፩– ፭፤ የሐዋ. ፭፥ ፩– ፲፮
ምስባክ፡- ይትሌቃህ ኃጥእ ወኢይፈዱ
ወፃድቅሰ ይምሕር ወይሁብ እለ ይባርክዎ ይወርስዋ ለምድር ፡፡ መዝ. ፴፮(፴፯) ፥ ፳፩- ፳፪
ወንጌል፡- ማቴ. ፳፭፥ ፲፬- ፴
|
No comments:
Post a Comment