በዲ/ን ዓላማየሁ ሀብቴ
ሚያዚያ ፬ ቀን ፳፻፱
ዓ/ም
ዐቢይ ጾም ከሆሳዕና በኋላ ከትንሣኤ በፊት ያሉት አምስቱ ቀናት በቤተክርስቲያናችን ቋንቋ ሰሙነ ሕማማት ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ይህም ከክርስቶስ ልደት በፊት ሰው በምድረ ፋይዲ ወድቆ የኖረበት የዐመተ ፍዳ ዐመተ ኩነኔ ምሳሌ ነው፡፡ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ያ ዘመን የጥፋት የጨለማ ዘመን ተብሎ ይታወቃል፡፡ አዳም በሠራው በደል ከአምላኩ ተጣልቶ፣ ከእግዚአብሔር የተሰጠው ስልጣን፣ ጸጋና ሲሳይ ተነፍጎት፣ ልጅነትን አጥቶ፣ ባሕርይው አድፎ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ተለይቶ፣ ከደስታ ሀገሩ ከገነት ተባርሮ፣ በምድረ ፋይድ ወድቀቆ ከነልጅ ልጆቹ ለአምስት ሺ አምስት መቶ ዘመናት በእግረ አጋንት ሲረገጥ ኖሯል፡፡ ይህ የአዳም በደል ጥንተ አብሶ፣ አበሳ ዘትካት፣ ኃጢአተ አዳም፣ ስህተተ አዳም፣ ድቀተ አዳም (የቀደመው በደል፣ የትንቱ አበሳ፣ የአዳም ኃጢአት፣ የአዳም ስህተት፣ የአዳም ውድቀት) ይባላል፡፡
ክርስቶስ በአጭር ቁመት በጠባብ
ደረት ተወስኖ በለቢሰ ሥጋ በኩነተ ሰብእ ወደዚህ ዓለም የመጣው አዳምን ከሴጣን ግዞት ነፃ አውጥቶ ከዘላላም ሞት ለማዳን ነው፡፡ የአዳም በደል ደምስሶ አዳምን ከወደቀበት
አንስቶ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ ነው፡፡ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ የሰው ፍቅር አገብሮት ሰውን ለማዳን ሰው ሆነ፡፡ ከኃጢአት
በቀር የሰውን ሥራ ሁሉ ሠራ፡፡ ወፈጸመ ኩሉ ግብረ ሰብእ ዘእንበለ ኃጢአት በህቲታ፡፡ በሰውነቱ የአዳምን መከራ ሁሉ በመስቀል ላይ
ተቀበለ፡፡ ስለአዳም ተገረፈ፣ መከራ መስቀልን ተሸከመ፤ ስለሰው ተራበ፣ ተጠማ፣ ታመመ፣ ቆሰለ፣ በመስቀል ላይ ሞቶ ሞትን አጠፋ፡፡
አዳም አምላክነትን ሽቶ ሰው መሆን ቢያቅተው አምላክ ሰው ሆኖ ሰውን አምላክ አደረገው፡፡ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በፈጸመው የማዳን
ሥራ የአዳም በደል ተደመሰሰ፣ የሴይጣን ስልጣን ተሸረ፣ ኃጢአት ተሸነፈት፣ ሞት ጠፋ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ. ፭÷ ፲፪-
፳፩ ድረስ እንደሚከተለው ያስረዳናል፡-ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን
ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤ ሕግ እስከ መጣ ድረስ ኃጢአት በዓለም ነበረና ነገር ግን ሕግ በሌለበት ጊዜ ኃጢአት
አይቈጠርም፤
ነገር
ግን በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ፥ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው
ለእርሱ አምሳሉ ነውና። ነገር
ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን እንደዚያው አይደለም፤ በአንድ ሰው በደል ብዙዎቹ ሞተዋልና፥ ነገር ግን የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ
ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የሆነው ስጦታ ከዚያ ይልቅ ለብዙዎች በዛ። አንድ ሰውም ኃጢአትን በማድረጉ እንደ ሆነው መጠን
እንደዚያው ስጦታው አይደለም፤ ፍርድ ከአንድ ሰው ለኵነኔ መጥቶአልና፥ ስጦታው ግን በብዙ በደል ለማጽደቅ መጣ። በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል
ከነገሠ፥ ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ። እንግዲህ በአንድ
በደል ምክንያት ፍርድ ለኵነኔ ወደ ሰው ሁሉ እንደ መጣ፥ እንዲሁም በአንድ ጽድቅ ምክንያት ስጦታው ሕይወትን ለማጽደቅ ወደ ሰው
ሁሉ መጣ። በደልም እንዲበዛ ሕግ ጭምር ገባ፤ ዳሩ ግን ኃጢአት በበዛበት፥ ኃጢአት በሞት እንደ ነገሠ፥ እንዲሁ ደግሞ ጸጋ
ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣ በጽድቅ ምክንያት ለዘላለም ሕይወት ይነግሥ ዘንድ፥ ጸጋ ከመጠን ይልቅ በለጠ።
ሰሙነ ሕማማት ከዘመነ ፍዳ ዘመነ
ኩነኔ ምሳሌነት ባሻገር የሰው ልጅ የመዳን ሥራ ጋር የተገናዘቡ ብዙ ሥራዎች ተሠርተውባቸዋል፡፡ የየራሳቸው የሆነ ስያሜም
አላቸው፡፡
ሀ. ሰኞ፡- መርገመ በለስ ትባላለች፡፡ ክርስቶስ ተርቦ ከበለስ ፍሬ ለመብላት ወደደ፡፡ ነገር ግን ከቅጠል
በቀር ፍሬ ስላጣባት ለዘላለም ፍሬ አይገኝብሽ ብሎ በለሷን ረገማት፡፡
በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ።
በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርስዋ መጣ፤ ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትምና። ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ አላት።
በለሲቱም ያንጊዜውን ደረቀች። ማቴ. ፳፩፥ ፲፰ -፲፱፡፡
ይህም መሳሌ ነው፡፡ በለስ የኃጢአት
ምሳሌ ናት፡፡ በአንፃረ በለስ ረገማ ለኃጢአት አንዲል፡፡ ለአምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን በሰው ላይ እንደ በለስ ጥላ ተንሰራፍታ
የነበረችውን ኃጢአት ረገመ፡፡ ወዲያውኑ ደረቀች ማለት ጥንተ አብሶ ተፋቀ ተደመሰሰ ማለት ነው፡፡
አንድም በለስ ቤተአስራአል ናት፡፡
በነቢያት በካህናት አድሮ በትንቢት በምሳሌ ወደአስተማራቸው አስራኤል ሀይማኖት ምግባር ፍሬ ባገኝባቸው ብሎ ወደ አነርሱ ቢመጣ ሀይማኖት
ምግባር ፍሬ አጣባቸው፡፡ ሀይማኖት ምግባር ካልያዘችሁ ልጅነት አትሰጣችሁም መንግሥቴን አትወርሱም ብሎ ከልጅነት ከመንግሥተ ሰማያት
አፍኣ አደረጋቸው፡፡ አንድም በቤተ እስራኤል ሰፍና የኖረቸውን ኃጢአት ረግሞ አደረቀላቸው፡፡
ዛሬም ከበለስ ኃጢአት ስር ሆነው
በእርግማን የሚኖሩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ማመስገን የማያውቁ የሚያማርሩ፤ የሚያሙ፣ ምርቃት የማያውቁ የሚራገሙ፤ ያልተመረቁ በክፉ ሥራቸው
የተረገሙ ብዙዎች ናቸው፡፡ እንግዲህ ክርስቶስ ኢየሱስ ከእርግማን ነፃ አውጥቶ በደሙ ቀድሶናልና ከኃጢአት ርቀን በቅድስና እንኑር፡፡
ለ. ማክሰኞ፡- የጥያቄ እለት ትባላለች፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰዎችን
ኃጢአት ይቅር ሲል፣ ድውያንን ሲፈውስ፣ ሙት ሲያስነሳ አይተው የካህናት አለቆች ቀኑበት፡፡ ሰው እኛን ትቶ ዓለሙ ሁሉ እርሱን ተከተለው
ብለው በምቀኝነት ተነሳስተው ኃጢአትን ይቅር እንድትል፣ ድውያንን ልትፈውስ፣ ሙት ልታስነሳ ይህን ስልጣን የሰጠህ ማን ነው ይህን
ስልጣን ከወዴት አገኘኸው ብለው ጠቁት፡፡ እርሱም ሹመት ሽልማት የማያስፈልገው ዘላላማዊ ንጉሥ የባሕርይ አምላክ ነውና ይህን እንድነግራችሁ
የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ናት ንገሩኝ አላቸው፡፡ በተንኮል እንደጠየቁት ያውቃልና፡፡ አነርሱም ከሰማይ ነው ብንል እንግዲያው ለምን
አላመናችሁበትም ይለናል ከምድር ነው ብንል ሕዝቡ በድንጋይ ይወግረናል ብለው የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት እንደሆነች አነውቅም አሉት፡፡
ጌታ ኢየሱስም ይህን ካላወቃችሁ ስልጣኔ ከወዴት እንደሆነች አልነግራችሁም አላቸው፡፡
ወደ መቅደስም ገብቶ ሲያስተምር
የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሎች ወደ እርሱ ቀረቡና። በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት።
ኢየሱስም መልሶ፦ እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተም ያችን ብትነግሩኝ እኔ ደግሞ እነዚህን በምን ሥልጣን እንዳደርግ
እነግራችኋለሁ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይን ወይስ ከሰው? አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ። ከሰማይ
ብንል። እንኪያስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ ከሰው ግን ብንል፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራለን
አሉ። ለኢየሱስም መልሰው። አናውቅም አሉት። እርሱም ደግሞ። እኔም
በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው። ማቴ ፳፩÷ ፳፫- ፳፰፡፡
ስልጣኑ የማይመረመር ምጡቅ፣ በሕርይው
የማይደረስበት ረቂቅ ነገር ግን በሕግ በአምልኮ ለሚቀርቡት ክሱት መሆኑን ሲያጠይቅ በማን ስልጣን ይህን እንደማደርግ አልነግራችሁም
አላቸው፡፡
ዛሬም በዓለማችን በሕይወታችንም
ብዙ ጥያቄዎች ብዙ ጠያቂዎችም አሉ፡፡ ሳይመለከታቸውም ሆነ ተመልክቶአቸው ስለምንሠራው ሥራ (ምን ቢሆን ነው ከእኔ ተሸሎ የተገኘው)፣
ስለማንባለው ምግብ (ምን ቢበላ ነው እንዲህ ያማረበት)፣ ስለምንጠጣው፣ ስለምንለብሰው (ከየት አምጥቶ ነው)፣ ስለምንኖርበት ቤት፣
ስለምናመልከው፤ ስለምንሰጠው አገልግሌት ወዘተ ለክፋትም ሆነ ለበጎ ጠያቂዎች አሉ፡፡ ለመመለስ የተዘጋጀን እንሁን፡፡
ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ
በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና
በፍርሃት ይሁን። ፩ጴጥ. ፫፥ ፲፭፡፡
ሐ. ረቡዕ፡- ምክረ አይሁድ ይባላል፡፡ ጸሓፍት ፋርሳውያንና የአይሁድ ሊቃነ ካህናት
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድው ሲፋውስ ሙት ሲያስነሳ ኦሪት እንዳለፈች ስልጣናቸው እንደ ቀረች እንደ ተሸረች አውቀው በምቀኝነት
ተነሳስተው የሀሳት ምስክር አቁመው በሀሳት ከሰሱት፡፡ ክሱም ፖለቲካዊና ሀይማኖታዊ ይዘት
ነበረው፡፡
Ø እራሱን ፈጣሪ አድርጎ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ይላል፣
Ø ሰንበትን ይሽራል፤
Ø ራሱን ንጉሥ አድርጎ ለቄሳር ግብር
እንዳይሰጥ ይከላክላል የሚል ነበር፡፡
አይሁድ ረቡዕ እለት ፕራቶሪዮን
በሚባል በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰብስበው ምንም በደል የሌለበትን ንፁሐ በሕርይ ክርስቶስን የሞት ፍርድ ፈረዱበት፡፡ ወታደሮችም ፕራይቶሪዮን
ወደሚባል ግቢ ውስጥ ወሰዱት፥ ጭፍራውንም ሁሉ በአንድነት ጠሩ። ማር. ፲፭÷ ፲፮፡፡
ሞቱ በፈቃዱ ቢሆንም አይሁድ በክፋት
ተነሳስተው ወንበዴ ተለቆ ክርስቶስ እንዲሞት ይሙት በቃ ፈረዱበት፡፡
ዛሬም በዓለማችን ለሰዎች ክፋትን
የሚመክሩ ተረፈ አይሁድ አሉ፡፡ ለሰው ክፉ ክፉውን ብቻ የሚመኙ፣ መልካም ምክር የማያውቁ፣ ሰው ሲስማማ የሚከፋቸው ዲያብሎሳውያን፣
የሀገርን ሰላም የማይወዱ፣ የሰዎች ፍቅር የሚያበሳጫቸው ጎጠኞች፣ በሰው ጥፋት የሚደሰቱ በርካቶች ናቸው፡፡
ክርስትና አምባ ክርስቲያንም የሰላም
ሐዋርያ ነውና ለሰው ሁሉ ፍቅር ይኑረን ሰላምንም እንመኝ፡፡
ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን
አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ሮሜ. ፲፪፥
፲፯- ፲፰፡፡
መ. ሐሙስ፡- ጸሎተ ሐሙስ ይባላል፡፡ ይህች ቀን ሕጽበተ እግር፣ እለተ ምስጢር፣ እለተ
ቁርባን ተብላም ትጠራለች፡፡ በዚህች ቀን ጌታ ሁለት ዐበይት ሥራዎችን ሠርቷል፡፡
፩ኛ. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ የሐዋርያትን እግር አጥቦ ትህትና አስተምሯል፡፡ መምህር ሆኖ ሳለ የተማሪዎቹን እግር አጠበ፡፡ የሰማይና የምድር ጌታ ሆኖ
ሳለ ወገቡን ታጥቆ ሎሌዎቹን አገለገለ፡፡
ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት፥
ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ
ወደዳቸው። እራትም ሲበሉ ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ ልብ አሳልፎ እንዲሰጠው አሳብ ካገባ በኋላ፥ ኢየሱስ አብ
ሁሉን በልጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ፥ ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፥
ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ
ሊያብስ ጀመረ። ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ፤ እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ፦
እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፥ በኋላ ግን ታስተውለዋለህ አለው። ጴጥሮስም፦ የእኔን እግር ለዘላለም አታጥብም አለው።
ኢየሱስም፦ ካላጠብሁህ፥ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም ብሎ መለሰለት።ስምዖን ጴጥሮስም፦ ጌታ ሆይ፥ እጄንና ራሴን ደግሞ እንጂ
እግሬን ብቻ አይደለም አለው። ኢየሱስም፦ የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፥ ሁለንተናው ግን ንጹሕ ነው፤
እናንተም ንጹሐን ናችሁ፥ ነገር ግን ሁላችሁ አይደላችሁም አለው። አሳልፎ የሚሰጠውን ያውቅ ነበርና፤ ስለዚህ፦ ሁላችሁ ንጹሐን
አይደላችሁም አለው። እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፥ እንዲህም አላቸው፦ ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን?
እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ። እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥
እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ
ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም። መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም። ዮሐ. ፲፫÷ ፩- ፲፮፡፡
፪ኛ. መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህች ቀን
ምስጢረ ቁርባንን መሥርቶልናል፡፡ የአይሁድ ፋሲካ (የቂጣ በዓል) በደረሰ ጊዜ ማዕመረ ኩሉ ህቡአት ጌታ የፋሲካን በዓል
እንዲያዘጋጁለት ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከ፡፡ በፊታችሁ ወደአላች ከተማ ሂዱ፡፡ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰውም ታገኛለችሁ፡፡
ተከተሉት፥ የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ፤ መምህሩ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው? ይላል በሉት። እርሱም በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ
ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን። ደቀ መዛሙርቱም
ወጡ ወደ ከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፥ ፋሲካንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ጋር መጣ። በዚያም ቤት (ቤተ ስምዖን)
ለማዕድ ተቀመጡ፡፡ ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ሰጣቸውና። እንካችሁ፤ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋንም አንሥቶ
አመስግኖም ሰጣቸው፥ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ። እርሱም፦ ይህ ስለ ብዙዎች ኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው ብሎ የዘላላም
ድኅነት የሚሆን ምስጢረ ቁርባንን ሠራልን። ጌታን ለሞት አሳልፎ የሚሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳም አሳልፎ የሚሰጥበት ሰላሳውን ዲናር
ለመቀበል ከአይሁድ ከተስማማ በኋላ በማዕዱ ታድሞ ነበር፡፡
በዚያን ጊዜ የአስቆሮቱ ይሁዳ
የሚባለው ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ። ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ? እነርሱም ሠላሳ
ብር መዘኑለት። ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ አሳልፎ ሊሰጠው ምቹ ጊዜ ይሻ ነበር። በቂጣው በዓል በመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ
ኢየሱስ ቀርበው። ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ልናሰናዳልህ ትወዳለህ አሉት። እርሱም፦ ወደ ከተማ ከእገሌ ዘንድ ሄዳችሁ።
መምህር። ጊዜዬ ቀርቦአል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ከአንተ ዘንድ ፋሲካን አደርጋለሁ ይላል በሉት አለ። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ
እንዳዘዛቸው አደረጉ ፋሲካንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ።ሲበሉም። እውነት
እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል አለ። እጅግም አዝነው እያንዳንዱ። ጌታ ሆይ፥ እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር። እርሱም
መልሶ፦ ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ያጠለቀ፥ እኔን አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፥
ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አለ። አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም
መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ እኔ እሆንን? አለ፤ አንተ አልህ አለው። ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ
ሰጠና። እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ፦ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ
ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። ማቴ. ፳፮÷ ፲፬- ፳፰፡፡
ፋሲካን በሚያርዱበት በቂጣ በዓል
መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ። ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ሄደን ልናሰናዳ ትወዳለህ? አሉት። ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ እንዲህም
አላቸው፦ ወደ ከተማ ሂዱ፥ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰውምይ ገናኛችኋል፤ ተከተሉት፥ የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ። መምህሩ። ከደቀ መዛሙርቴ
ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው? ይላል በሉት። እርሱም በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ
ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን። ደቀ መዛሙርቱም ወጡ ወደ ከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፥ ፋሲካንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ከአሥራ
ሁለቱ ጋር መጣ። ተቀምጠውም ሲበሉ ኢየሱስ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ፥ እርሱም ከእኔ ጋር የሚበላው አሳልፎ ይሰጠኛል
አለ። እነርሱም ያዝኑ፥ እያንዳንዳቸውም። እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር። እርሱም መልሶ፦ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ከእኔ ጋር ወደ ወጭቱ
እጁን የሚያጠልቀው ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤
ያሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አላቸው። ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ሰጣቸውና። እንካችሁ፤ ይህ ሥጋዬ ነው
አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፥ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ።እርሱም፦ ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው። ማር.
፲፬÷ ፲፪- ፳፬፡፡
በዚህች ቀን በቤተክርስቲያናችን
ካህናት፣ ሊቃነ ካህናት፣ ጳጳሳት፣ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ ዝቅ ብለው የተናናሾቻቸውን (በማዕረግ) እግር ያጥባሉ፡፡ ይህ
ከመምህረ ትህትና ከጌታቸው ከኢየሱስ ክርስቶስ የተማሩት ነው፡፡
ሠ. አርብ፡- ስቅለት ይባላል፡፡ ጌታ የተሰቀለባት አርብ እለተ መድኃኒት፣ እለተ መስዋዕት፣
የካሳ ቀን ናት፡፡ በዚህች ቀን ጌታ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ለዓለም ቤዛ ሆኗል፡፡ የሰው ፍቅር አሸንፎት በመልእልተ መስቀል
ላይ ስለሰው ሞተ፡፡ የአዳምን ኃጢአት ያስወግድ ዘንድ ሕያው የእግዚአብሔር በግ በመስቀል ላይ ታረደ፤ ተሰዋ፡፡ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘየዓትት ኃጢአተ ዓለም (የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ እንሆ)፡፡ የዓለምን ኃጢአት ሊያስወግድ የሚችለው
ሰዎች የሚሠውት ተፈጥሮአዊ በግ ሳይሆን የእግዚአብሔር በግ ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሔር በግ ደሙ የዓለምን ኃጢአት የሚያጥብ፣ የተዘጋውን
የገነት በር የሚከፍት፣ የአዳምን በደል የሚደመስስ፣ ለዘመናት በሰው ላይ ሰፍኖ የነበረውን የሴይጣንን ግዛት የሚያፈርስ እውነተኛ
መድኃኒት ነው፡፡ የእግዚአብሔር በግ እግዚአብሔር ዓለሙን የወደደበትና ለሰው ያለውን አምላካዊ ፍቅሩን የገለጠበት፣ ችርነቱን፣ መግቦቱን፣
ርህራሄውን ያሳየበት ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና፡፡ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤ የመሥዋዕቱ በግ ልዑለ
ባሕርይ የእግዚአብሔር አንድያ ልጁ ነው፡፡ ዮሐ. ፫፥፲፮ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ
የእግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡ ሊቁ አባ ሕርያቆስም ይህን እግዚአብሔር ለሰው ያለውን
ፍቅር በማድነቅ ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሆ እስከ ለሞት (ኃያሉ እግዚአብሔር ወልድን የሰው ፍቅር ከልኡል መንበሩ
ሳበው ለሞትም አደረሰው) ብሏል(ቅዳሴ ማርያም)፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
በፈቃዱ ራሱን በመስቀል ላይ ሠውቶልናል፡፡ ሕመማችንን ታመመ፣ አበሳ በደላችንን ተሸከመ፣ መከራችንን ተቀበለ፣ ተናቀ፣ ተተፋበት፣
ስለእኛ ቆሰለ፣ ሞታችንን በመስቀል ላይ ሞቶ ሕይወቱን ሰጠን፡፡
የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል?
የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጧል? በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል፡ መልክና ውበት የለውም፣ ባየነውም
ጊዜ እንወደው ዘንድ ደም ግባት የለውም፡፡ የተናቀ ከሰውም የተጠላ፣ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፡ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት
የተናቀ ነው፣ እኛም አላከበርነውም፡፡ በአውነት ደዌአችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሟልና እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም
እንደ ተቀሰፈ እንደ ተቸገረም ቆጠርነው፡፡ እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቆሰለ፣ ስለበደላችንም ደቀቀ የደህንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ
ላይ ነበረ፣ በእርሱም ቁስል እና ተፈወስን፡፡ እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ
እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ፡፡ ተጨነቀ ተሰቃየም አፉንም አልከፈተም ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፣ በሸላቾቹም
ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡ በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ
ተወገደ ከትውልዱ ማን አስታዋለ? ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፣ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፣ በአፉም
ተንኮል አልተገኘበትም ነበር፡፡ ኢሳ. ፶፫፥፩-፱፡፡
ስለእኛ መከራ መስቀልን ተቀበለ፡፡
የሾህ አክሊል ደፍቶ ተንገላታ፣ አጥንቱ አስኪታይ ተገረፈ፣ ታመመ፣ ሞተ፡፡ በድካሙ አበረታን፣ በሕማሙ ፈወሰን፣ በሞቱ አዳነን፡፡
ወበሕማማቲሁ ቤዘወነ እንዲል ግብረ ሕማማት፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
የዓለምን ኃጢአት ሊደመስስ በመስቀል ላይ ሆኖ ክፉዎች አይሁድ መከራ ሲያበዙበት፣ ሲገርፉት፣ የሾህ አክሊል በራሱ ላይ ደፍተው ሲዘባበቱበት፣
በችንካር ሕማሙን ሲያበዙበት አልተቆጣም፡፡ ክፉም ቃልም አልተናገራቸው፡፡ በፈቃዱ መከራን በሥጋው የተቀበለ፤ መከራን ሁሉ የታገሠ እርሱ
ነው፤ እንደ
በግ ሊሠዋ
መጣ፤ በግ
በሚሸልተው ሰው
ፊት እንዳይናገር አልተናገረም፤
በነገሩም ሐሰት
አልተገኘበትም
እንዲል ሀይማኖተ አበው ዘጎርጎርዎስ፡፡
ይልቁንም የፍርሃት የትዕቢት አይደለ ለሰው መድኃኒት አብነት የሚሆኑ ሰበአቱ አጽርሓ
መስቀል (ሰባቱ የመስቀል ላይ ጩኸት) የተባሉትን ብቻ አሰምቶ ተናግሯል፡፡ ቃላተ ርኅራኄ ሰበአተ እንተ ዲበ መስቀል ነበበ እንዲል፡፡
እነዚህ ጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ የተናገራቸው ሰባቱ ቃለተ ርኅራኄ የሚከተሉት ናቸው፡፡
፩. ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ
(አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ) ማቴ. ፳፯፥፵፮፡- ስለ አዳም ተገብቶ ሲጸል፡፡
፪. አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና
ይቅር በላቸው፡፡ ሉቃ. ፳፫፥፴፬፡- ከባቴ አበሳ ነውና ይቅርታን ሲያስተምረን፡፡
፫. እውነት እልሃለሁ፣ ዛሬ ከእኔ
ጋር በገነት ትሆናለህ፡፡ ሉቃ. ፳፫፥፵፫፡- በመከራ ብንመስለው እንደሚታደገን ሲያጠይቅ፡፡
፬. አባት ሆይ ነፍሴ በእጅህ አደራ
እሰጣለሁ፡፡ ሉቃ. ፳፫፥፵፮፡- የነፍሳችን ጌታ እግዚአብሔር መሆኑን ሲያሰተምረን፡፡
፭. አንቺ ሴት እነሆ ልጅሽ… እነኋት
እናትህ፡፡ ዮሐ. ፲፱፥፳፮፤ ለድንግል እናቱ ልጆቿ እንድንሆን አደራ ሲሰጣት፡፡
፮. ተጠማሁ፡፡ ዮሐ. ፲፱፥፳፱፤
የአደምን የ፶፭፻ ዘመናት በሲኦል መጠማት እንደ ተጠማለትና በደሙ እንደረከው ለመግለጽ፡፡
፯. ተፈጸመ፡፡ ዮሐ. ፲፱፥፴፤
ኪዳነ አዳም ፣ ድህነተ ዓለም መፈጸሙን፣ ካሳ መከፈሉን ሲያጠይቅ ነው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ለቤዛ ዓለም በመሥዋዕትነት በቀረበ ጊዜ አዲስ የመሥዋዕት ሥርዓት ሠርቷል፡፡ በሐዲስ ኪዳን ዘለዓለማዊ የሆነ አዲስ የክህነት አገልግሎት
ፈጽሟል፡፡ በዘመነ ብሉይ የነበረ ፍጹም ድህነት የማይሰጠውን አሮጌ
የክህነት ሥርዓት ሽሮ በአዲስ ሥርዓት፣ በአዲስ አገልግሎት፣ በአዲስ ክህነት፣ በአዲስ መሥዋዕት፣ በአዲስ ሊቀ ካህናትነት ፈጽሞታል፡፡
የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት ፍጹም ባልሆነ የክህነት አገልግሎት ስለራሱና ስለሕዝቡ ኃጢአት ሥርየት የደም መሥዋዕት ይዞ በዓመት አንድ
ጊዜ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባ ነበር፡፡ የሐዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ንጹሓ ባሕርይ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለሙ ሁሉ ድህነት በፍጹም
የክህነት አገልግሎት ዘለዓለማዊ የድህነት መሥዋዕት አንድ ጊዜ ፈጽሟል፡፡
ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ
ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፣ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፣ የዘለዓለምን
ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም፡፡ የኮርማዎችና የፍየሎች
ደም በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ ሥጋን ለማንጻት የሚቀድሱ ከሆኑ፣ ነውር የሌለው ሆኖ በዘለዓለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሄር
ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን? ዕብ. ፱፥፲፩-፲፬፡፡
በሐዲስ ኪዳን የክህነት አገልግሎት መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ አዳም ራሱን መስዋዕት
አድርጎ በመስቀል ላይ ሲያቀርብ እራሱ መስዋዕት ሆኖ፣ እርሱ እራሱ መሥዋዕት አቅረቢ ሊቀ ካህን፣ መስዋዕት ተቀባይ አምላክም እራሱ
ነበር፡፡ የሚሰዋ በግ
እርሱ ነው፤
የሚሰዋ ካህን
እርሱ ነው፤
ከባሕርይ አባቱ
ከአብ፤ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ
ጋርም መሰዋዕት የሚቀበል እርሱ ነው እንዲል ሀይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ፡፡ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን
አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ፡፡ ፪ቆሮ. ፭፥፲፱፡፡
በዚህ በሓዲስ ኪዳን የክህነት አገልግሎት
ሥርዓት የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤ የመስዋዕቱ በግ በመስቀል ላይ በተሰዋበት ጊዜ ሰባት ተኣምራት ተፈጽመዋል፡፡
ማቴ. ፳፯፥፵፭-፶፬፡፡ በሰማይ ሶስት በምድር አራት ተአምራት ተፈጽመዋል፡፡
ይኸውም፡-
፩. ፀሐይ ጨለመች (ከስድስት እስከ
ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ላይ ጨለማ ሆነ)፣
፪. ጨረቃ ደም ሆነች፤
፫. ከዋክብት ረገፉ፣
፬. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ለሁለት
ተቀደደ፣
፭. ምድር ተናወጠች፣ ዓለቶች ተሰነጠቁ፣
፮. መቃብራት ተከፈቱ፣
፯. ሙታን ተነሱ፡፡
የመስዋዕቱ በግ በተሠዋ ጊዜ ተጣልተው
የነበሩ ሰባቱ መስተጻርራን ታርቀዋል፤ ተስማምተዋል፡፡ ሰው ሕገ እግዚአብሔርን ጥሶ ከፈጣሪው በመጣላቱ ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና
መላእክት፣ ሥጋና ነፍስ፣ ሰማይና ምድር ተጣልተው ነበር፡፡ ሰው ከአምላኩ ከተጣላ፣ ከፈጣሪው ከተለየ ፍጡራና ሁሉ ይጣሉታል፡፡ እነዚህ
ሰባቱ ማስተጻርራን የታረቁት ሰው ከፍጣሪው በታረቀ ጊዜ ነው፡፡ ሰው ከአምላኩ የታረቀው በመሥዋዕቱ በግ፤ በእግዚአብሔር በግ ነው፡፡
እግዚአብሔር ቀድሞ ለአዳም በገባለት ቃል ኪዳን (ኪደነ አዳም) መሠረት በመሥዋዕቱ በግ፣ በልጁ ደም ጠላቱ የነበረውን በደለኛውን
ሰው ታረቀው፡፡ ሮሜ. ፭፥፲ ጠላቶቹ ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቀን፣ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፡፡
በዚህ በመሥዋዕቱ በግ ጠላትነት ጠፋ፣ በሰማይና በምድር ዕርቅ፣ ሰላም ሆነ፡፡ ቆላ. ፩፥፲፱-፳ እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ
እንዲኖር፥ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና። እግዚአብሔር
አምላክ ለገዛ ልጁ ሳይራራ መሕያዊት ለምትሆን ሞት በመስቀል ላይ አሳልፎ የሰጠው፣ አጽመ አዳም ባለበት በቀራንዮ ተራራ ላይ የሠዋው፤
የሴይጣንን ግዛት አፍርሶ፣ በአዋጅ የተነገሩትን የሞት ትዕዛዛት ሽሮ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን የጥል ግድግዳ ለማስወገድ
ነው፡፡ ኤፌ. ፪፥፲፮ ጥልንም
በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።
እግዚአብሔር ወልድ ጠላቶቹ ሳለን በሞቱ ታረቀን፣ ደሙን አፍስሶ ሥጋውን ቆርሶ ከዘለዓለም
ሞት ዋጀን፣ በሞቱ ሞታችንን አጥፍቶ ሕይወትን ሰጠን፣ እርሱ ተዋርዶ እኛን አከበረን፣ ስለእኛ ሞቶ እኛን አዳነን፡፡ በጸሎተ ሃይማኖታችን
ኮነ ብእሴ በእንቲኣነ፣ ሓመ፣ ወሞተ፣ ወተቀብረ፣ ወተንሥአ እሙታን ብለን ቤዛነቱን እንመሰክራለን፡፡ የመሥዋዕቱን በግ፤ የዓለምን
ኃጢአት የሚያስወግደውን የእግዚአብሔር በግ ሥጋውን በልተን ደሙን ጠጥተን ዘለዓለማዊ ሕይወት እናገኛለን፡፡ ሥጋው ዘለዓለማዊ የሕይወት
ምግብ ደሙም ዘለዓለማዊ የሕይወት መጠጥ ነው፡፡ በዘመነ ብሉይ እስራኤላውያን በምድረ በዳ መና በልተው ሞቱ፡፡ ከሰማይ የወረደው
መና ከሞት ታድጎ ዘለዓለማዊ ሕይወት አልሰጣቸውም፡፡ እኛ በምሥጢራዊና መንፈሳዊ ልደት ከክርስቶስ የተወለድን የክርስቶስ ወገኖች፣
የመንግሥቱ ዜጎች የሆንን ክርስቲያኖች (እስራኤል ዘነፍስ) በመስቀል ላይ የተሠዋውን የመሥዋዕቱን የእግዚአብሔር በግ በልተን ዘለዓለማዊ
ሕይወት አግኝተናል፡፡ ከመስቀሉ ወደ
ሲኦል በመውረዱ አዳነን፤ በአባታቸው በአዳም በደል በሲኦል ተግዘው የነበሩ ጻድቃንን ፈታ
ከሙታን ተለይቶ አስቀድሞ በተነሣ በእውነተኛ ትንሣኤውም አስነሣን፤ የንስሐንም በር ከፈተልን፡፡ በአባታችን በአዳም በደል የተዘጋ የገነት ደጅን
የከፈተልን፤ ዕፀ
ሕይወትን የሚጠብቅ ኪሩብንም ያስወገደ፤ የእሳት ጦርን ከእጁ ያራቀ፤ ወደ ዕፀ ሕይወት ያደረሰን እርሱ ነው፤ ፍሬውንም (ሥጋውን ደሙን)
ተቀበልን
ሀይማኖተ እንዲል አበው ዘጎርጎርዎስ፡፡
በመስቀል ላይ በፈቃዱ የተሰዋልንን
የመሰዋዕቱን በግ ሥጋ በልተን ደሙን ጠጥተን ከደዌ ሥጋ ደዌ ነፍስ እንድናለን፡፡ በደሙ ፈሳሽነት ኃጢአታችንን ባጠበው የእግዚአብሔር
በግ እዳ በደላችን ተደምስሶ የቅድስና ማዕረግ አግኝተናል፡፡ ሥጋ ወደሙ ደምሳሴ አበሳ፣ መሥተሥርየ ኃጢአት ወሀቤ ሕይወት ነው፡፡
እንበለ ደዌ
ወሕማም እንበለ ፃማ ወድካም አመ ከመ
ዮም ያብጽሐና ያብጽሐክሙ እግዚአብሔር በሰላም፡፡
No comments:
Post a Comment