ውድ የማኅቶት ታዳሚያን እንደምን ከረማችሁ! ያልገባኝ ጥያቄ ለምንድ ነዉ እኩለ ፆም ሳማ ሰንበት በተለይ የሚከበረዉ? በማለት አንድ የማኅቶት ቤተሰብ ጥያቄ አቅርበዋል:: ውድ ጠያቂአችን ጥያቄዎን በወቅቱ ባለመመለሴ ይቅርታ ይደረግልኝ:: ኔትወርክ የሌለበት ስለነበርኩ ጥያቄውን አላየሁም ነበር:: መልሱን በአጭሩ እነሆ: ሰማ ሰንበት የሚከበረው በዓል ፅላቱ የሰንበት ፅላት ነው:: በምንጃር ወረዳ ሰማ ገዳም የሚከበረው ደግሞ የሰንበት ፅላት (ፅላተ እግዚአ ለሰንበት) የሚገኘው እዚያ ብቻ ስለሆነ ነው:: በእኩለ ጾም በደብረ ዘይት እለት መከበሩ እለቱ የህልፈተ ዓለም መታሰቢያ የምፅአተ ክርስቶስ መዘከርያ እለት ስለሆነ ነው:: ጌታችን ይህን ዓለም ለማሳለፍ ዳግም የሚመጣዉ በወርኃ መጋቢት በእለተ እሁድ በእኩለ ሌሊት ነው:: ይሁን እንጂ ጌታ በማቴዎስ ወንጌል 24: 36 ላይ " ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም።" እንደተናገረው የትኛው ወርኃ መጋቢት የትኛዋ እለተ ሰንበት የትኛይቱ እኩለ ሌሊት እንደሆነ ከእርሱ በቀር አንድም ፍጡር አያውቅም:: ይህ ጌታ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ የዳግም ምፅአቱን ያስተማረውን ትምህርት መሠረት አድርጋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በዓሉን በዓለ ደብረ ዘይት በዓለ ህልቀተ ዓለም በዓለ ሰንበት በዓለ ዳግም ምፅአት ነገረ ሕይወት ዘለዓለም በማለት ሥርዓት ሠርታ ጊዜ መድባ በዚህች እለት ታከብራለች::
No comments:
Post a Comment