በዲ/ን ዓላማየሁ ሀብቴ
ሚያዚያ ፬ ቀን ፳፻፱
ዓ/ም
ዐቢይ ጾም ከሆሳዕና በኋላ ከትንሣኤ በፊት ያሉት አምስቱ ቀናት በቤተክርስቲያናችን ቋንቋ ሰሙነ ሕማማት ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ይህም ከክርስቶስ ልደት በፊት ሰው በምድረ ፋይዲ ወድቆ የኖረበት የዐመተ ፍዳ ዐመተ ኩነኔ ምሳሌ ነው፡፡ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ያ ዘመን የጥፋት የጨለማ ዘመን ተብሎ ይታወቃል፡፡ አዳም በሠራው በደል ከአምላኩ ተጣልቶ፣ ከእግዚአብሔር የተሰጠው ስልጣን፣ ጸጋና ሲሳይ ተነፍጎት፣ ልጅነትን አጥቶ፣ ባሕርይው አድፎ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ተለይቶ፣ ከደስታ ሀገሩ ከገነት ተባርሮ፣ በምድረ ፋይድ ወድቀቆ ከነልጅ ልጆቹ ለአምስት ሺ አምስት መቶ ዘመናት በእግረ አጋንት ሲረገጥ ኖሯል፡፡ ይህ የአዳም በደል ጥንተ አብሶ፣ አበሳ ዘትካት፣ ኃጢአተ አዳም፣ ስህተተ አዳም፣ ድቀተ አዳም (የቀደመው በደል፣ የትንቱ አበሳ፣ የአዳም ኃጢአት፣ የአዳም ስህተት፣ የአዳም ውድቀት) ይባላል፡፡