Wednesday, February 18, 2015

፩. ዘወረደ

አንደኛው እሑድ ዘወረደ ይባላል፡፡ኃያል አምላክ የሰው ፍቅር አገብሮት ከሰማየ ሰማያት መውረዱ ፤ ሰው ሆኖ መወለዱ ፤ መሰቀሉ የሚወሳበት ሳምንት ነው ፡፡ ከፈጣሪው ተጣልቶ የነበረ አዳም መታረቁ የሚነገርበት በመሆኑ ዘወረደ ስብከተ ተፋቅሮ ነው ፡፡
የአዳም ስህተት የልጆቹም ተባባሪነት በሰውና በእግዚአብሄር መካከል ያለውን ልዩነት በመስፋቱ ሰባት መስተፃርራን ተከሰቱ  (ሰውና እግዚአብሔር ፤ ሰውና መላእክት ፤ ነፍስና ሥጋ ፤ ሰማይና ምድር) ፡፡ ሰው ከፈጣሪው በመለየቱ ምክንያት ፍጡራን ሁሉ ተለያዩ ፡፡ ጥፋተኛው አዳም በምድረ ፈይድ ተጣለ ፡፡ ዘመኑም ዘመነ ፍዳ ዘመነ ኩነኔ ሆነ ፡፡ ሩህሩሁ አምላክ ፈጽሞ ከሰው መለየት ፈቃዱ ስላልሆነ በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ “ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅየ አድንኃለሁ” ብሎ ለአዳም ቃል ገባለት ፡፡ ዘፍ. ፫ ፲፭ $ ይህ ኪዳነ አዳም ይባላል ፡፡ የቃል ኪዳን ሁሉ መሠረት ነው ፡፡ ሁለቱን ኪዳናት (ብሉይ ወሐዲስ) በፅኑዕ ተስፋ ያስተሳሰረ የረጅም ዘመናት የድኅነት ሰንሰለት ነው ፡፡ ዘወረደ እርቀ አዳም  ፤ ተስፋ አበው ፤ ትንቢተ ነቢያት ፤ ሱባኤ ካህናት መፈፀሙ ፤ ኪዳነ አዳም መሲህ መወለዱ የሚነገርበት የፍቅር አዋጅ ነው ፡፡ ዘወረደ የምስጢረ ሥጋዌ ትምህርት ነው ፡፡ ዘወረደ ስንል አምላክ መጣ ፤ ወረደ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ ፤ በፍጹም ተዋሕዶ ሰው ሆነ ማለታችን ነው ፡፡ ዘወረደ በአምላክ ትህትና ክብረ አዳም የሚነገርበት ነው ፡፡ አምላክ ሰው በመሆኑ ሰው አምላክ ሆነ ፤ ከበረ ፤ ገነነ ፤ ነገሠ ፡፡ ሕያው አምላክ ክርስቶስ በቅድስት ሞቱ ሟቹን አዳም ዘላለማዊ ሕያው አደረገው ፡፡ አምላክ ወልደ አምላክ በመስቀል ላይ በፈቃዱ ሞቶ ለአዳም ያለውን ታላቅ ፍቅር ገለጸ ፡፡ የተጣላውን አዳምን በፈቃዱ ታረቀው ፡፡ ጠላቶቹ ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን ፥ ይልቁንም ከታረቅን በኃላ በሕይወቱ እንድናለን ፡፡ ሮሜ. 5 ፥ ፲ ፡፡ በዚህም ትህትናን ፍቅርን አስተማረን ፡፡
ስለዚህ ወገኖቼ ፡- ቸሩ አምላክ በደላችንን ሁሉ ሳይቆጥር የዋለልንን ውለታ አስበን ለሰው ሁሉ መልካም በማሰብ ብንበድል ማሩኝታ ፤ ብንበደልም ይቅርታ አድርገን ፈለጉን እንከተል ፡፡
የእለቱ መዝሙር ፡- ተቀነዩ ለእግዚአብሔር
ምስባክ ፡- ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሐት ወተሀሰዩ ሎቱ በረዓድ አጽንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመዐዕ እግዚአብሔር ፡፡ መዝ. ፪፥ ፲፩-፲፪
ወንጌል ፡- ዮሐ. ፫ ፥ ፲ - ፳፩



ወስብሐት ለእግዚእብሔር

No comments:

Post a Comment