Wednesday, April 26, 2017

ሰሙነ ትንሣኤ (የትንሣኤ ሳምንት)/በዓለ ኀምሳ


በዲ/ን ዓለማየሁ ሀብቴ
ሚያዚያ ፲፯ ቀን ፳፻፱ ዓ/ም
ከትንሣኤ እሑድ ቀጥለው ያሉት ዕለታትሰሙነ ፋሲካወይምትንሣኤእየተባሉ የሚጠሩ ሲሆን፣ የየራሳቸው ምሥጢራዊ ስያሜም አላቸው፡፡
በዓለ ኀምሳ የሚባለው ከትንሣኤ እስከ በዓለ ጰንጠቆስጤ (በዓለ ጰራቅሊጦስ) ድረስ ያሉት ኀምሳ ዕለታት ናቸው በዚህ ወቅት ቤተክርስቲያን የክርስቶስን ትንሣኤ ታከብራለች በክርስቶም ያገኘችውን ዕረፍተ ነፍስ በምልዓት ትሰብካለች ፡፡ ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትን ታስባለች ፡፡ በነዚህ ዕለታት ዓርብ ረቡዕ አይጾሙም ቀኖና ለተነሳሕያን አይሰጥም ከበደልና ከመበደል ነጻ ሁነን፣ ከበደለኛ አእምሮ ወቀሳ ድነን የምንኖርባት መንግሥቱ በትንሣኤ ትሰጠናለች ፣ በትንሣኤውም በደላችን ሁሉ ሽሯል እንዲሁም በስግደት በድካም በትህርምት የሚኖሩ ሁሉ በዕረፍት በዐለ ኀምሣውን ያሳልፋታል በዚህ ወቅት ቅዳሴ መዝሙር ድካም የማያስከትል ሥርዓተ አምልኮት ይፈጸማል ይህ ሁሉ የሚሆነው በክርስቶስ ዕረፍተ ነፍስ አግኝተናል ጌታ የትንሣኤያችን በኩር ነው እኛም ከተነሣን በኋላ እግዚአብሔር ረኃብ ጥም ድካም ሕማም ፈተና ሞት ፈታኝ መቃብር ብልየት ልደት ልህቀት ኃይለ ዘርዕ ኃይለ ንባብ ኃይለ እንሰሳ የሌለበትን ሥርዓተ ምድር አልፎ በአዲስ ሥርዓተ ሕይወት የምትመራውን ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን ለማለት ሲሆን ቀኖና የማይሰጠው በሥጋም ሆነ በነፍስ ከመበደል ጌታ ነጻ ያወጣናል ባለመበደል በአፋችን ምስጋና መልቶ ሕይወታችን ከበደል ተለይቶ የምንኖርበት ዘመን ይመጣል በትንሣኤው በዕርገቱ ጽድቅና ጸጋ ሕይወት ተሰጥቶናል ከተዋርዶ ነፍስ ድነናል ለማለት ነው በአጠቃላይ ድኅነተ ነፍስ ድኅነተ ሥጋ በኢየሱስ ክርስቶስ ተሰጥቶናል ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያት የዘለዓለም ሕይወት ተዘጋጅቶልናል ማለት ነው
የአንደኛው ሳምንት እሑድ
እሑድ በዓለ ትንሣኤ ነው ፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ሦስት ሌሊት ሦስት መዓልት በከርሠ መቃብር አድሮ የተነሳበት ፣ ሙስና መቃብር የተሻረበት ትንሣኤያችን በትንሣኤው የታወጀበት ዕለት ነው ። ጌታችን ከሙታን ተለይቶ መነሣቱን ፣ ሞትን በሞቱ ድል መንሣቱን ሙስና መቃብርን (በመቃብር ፈርሶ በስብሶ መቅረትን) ማጥፋቱን በሞቱ በመስቀሉ ያዳናቸውን በትንሣኤው ማጽደቁን በዝግ ቤት ገብቶ በፍርሃት ለነበሩት ሐዋርያት ሰላምን እርቅን መስበኩን ቤተክርስቲያን ታስባለች
ሰኞ
የትንሣኤው ማግሥት ሰኞ ጌታችን በትንሣኤው ነፍሳትን ከሲኦል አውጥቶ ወደ ገነት አሻግሮ ለማስገባቱ መታሰቢያ ሰትሆን፣ፀአተ ሲኦልወይምማዕዶትትባላለች ዮሐ. ፲፱ ፥ ፲፰ ፤ ሮሜ. ፭ ፥፲ - ፲፯ ፡፡ 
ይህች እለት ሁለት መጽሓፍ ቅዱሳዊ ታሪኮች አሉአት ፡፡
፩ኛ ማዕዶት ትባላለች ። ማዕዶት ማለት (መሻገሪያ፣ መሻገር) ማለት ነው ። ታሪክ ፡- ቀድሞ እስራኤላውያን ባሕረ ኤርትራን ተሻግረው ምድረ ርስት ገብተዋል ። ምሳሌው ፈርዖን የዲያብሎስ ፣ ሠራዊቱ የሠራዊተ ዲያብሎስ ፣ ግብፅ የሲኦል ፣ ባሕረ ኤርትራ የባሕረ ሲኦል ፣ እስራኤል የምእመናን ፣ ሙሴ የወልደ እግዚአብሔር ፣ በትረ ሙሴ የመስቀል ምሳሌ እስራኤላውያን በሙሴ መሪነት ተሻግረው ምድረ ርስት እንደገቡ ነፍሳትም በክርስቶስ መሪነት ባሕረ ሲኦልን ተሻግረው ገነት የመግባታቸው ምሳሌ ነው ። በዚህም ማዕዶት ተብላለች ።
፪ኛ ዕለተ አብርሃም (ዕለቱ ለአብርሃም) ፣ ማዕዶተ አብርሃም (ማዕዶቱ ለአብርሃም) ትባላለች ። አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ከነዓን ገብቷል ። በዚህም አንጻር ምእመናንም ባሕረ ሲኦልን ተሻግረው ገነት የመግባታቸው ምሳሌ ነው ። አንድም አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ቢሄድ መልከጼዴቅ ኅብስተ አኰቴት ጽዋዐ በረከት ይዞ ተቀብሎታል ። ነፍሳትም ባሕረ ሲኦልን ተሻግረው ቢሄዱ ኅብስተ በረከት ጽዋዐ አኰቴት ወልድን የማግኘታቸውና ወደ ቀድሞ የበረከት ርስት የመመለሳቸው ምሳሌ ነው ። ስለዚህ ትንቢቱ ምሳሌው መድረሱን ለማጠየቅ ዕለቷ ማዕዶት ትባላለች ።
በዚህች ቀን ቤተ ክርስቲያን ነፍሳት በክርስቶ ሞትና ትንሣኤ ከሞት ወደ ሕይወት ከሐሳር ወደ ክብር ከሲኦል ወደ ገነት መሻገራቸውን ፋሲካችን ክርስቶ መሆኑን ታስባለች ፣ ታከብራለች ፣ ታስተምራለች ። ቆሮ.
በዳግም ትንሣኤው ማግሥት ያለችው ሰኞ ደግሞ ገበሬው፡- ወንዶቹ እርሻ ቁፋሮውን፣ ንግዱን፣ ተግባረ እዱን ዅሉ፤ ሴቶቹ፡- ወፍጮውን፣ ፈትሉን፣ ስፌቱን የሚጀምሩባት ዕለት ስለ ኾነችእጅ ማሟሻ ሰኞትባላለች፡፡

ማክሰኞ
 ቶማስ ትባላለች ፡፡ የትንሣኤው ዕለት እሑድ ማታ ጌታችን በዝግ ቤት ገብቶ ለሐዋርያት ሲገለጽ ሐዋርያው ቶማስ ከእነርሱ ጋር አልነበረም ፡፡ በኋላ ከሔደበት ሲመጣ ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሣኤውን ቢነግሩት ‹‹እኔ ሳላይ አላምንም›› አላቸው ፡፡ በሳምንቱ ቶማስ በተገኘበት ጌታችን በድጋሜ ለሐዋርያት ተገለጸላቸው ፡፡ በዚህች ዕለት ቅዱስ ቶማስ በጦር የተወጋ ጎኑን ችንካር  የተቸነከረ እጁንና እግሩን ካላየሁ አላምንም በማለቱ ክርስቶስ ቶማስን ‹‹ጣትህን ወደዚህ አምጣና በጎኔ አግባው ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው ቶማስም ደስሶት ጌታዬ አምላኬም ብሎ መሰከረ ፡፡ ኢየሱስም ስለ አየኸኝ አምነሀል ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዐን ናቸው አለው›› ተብሎ እንደ ተጻፈ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የጌታችንን ጐን የዳሰሰበትና እጁ የደረቀችበት እንደገና መልሳ የዳነችበት መታሰቢያ ነው ። ለቶማስ ታሪክ መታሰቢያ ትሆን ዘንድ ይህቺ ዕለት በሐዋርያው ቶማስ ስም ተሰይማለች ዮሐ. ፳ ፥ ፳፬ - ። ምንም እንኳን ታሪኩ የዳግማይ ትንሣኤ ቢሆንም አበው ታሪክ ከታሪክ እንዳይደራረብ ብለው የቶማስ መታሰቢያው ማክሰኞ እንዲሆን ሕግ ሥርዓት ሰርተው ደንግገዋል ። ዩሐ. ፳፯ - ፳፱
ረቡዕ
አልዓዛር ትባለለች ። ጌታችን ከሞተና ከተቀበረ ከአራት ቀን በኋላ ከመቃብር ጠርቶ ላስነሣው ለአልዓዛር መታሰቢያ ትሆን ዘንድ ፤ በክርስቶስ ሥልጣን የአልዓዛርን ከሞት መነሣት አይተው ብዙ ሕዝብ በጌታችን ስለ አመኑ ዕለቲቱ (ረቡዕ) ‹አልዓዛርተብላ ታሰይማለች ዮሐ. ፲፩ ፥ ፴፰ - ፵፮ ፡፡
አልዓዛር ጌታችን በጥንተ ስብከት ያስነሳው ሲሆን ታሪኩ በዮሐንስ ወንጌል በምልአት ተመዝግቧል ። አልዓዛር ከሞት የተነሳው መጋቢት ፲፯ ቀን ነው ። በዚሁ ቀን መታሰቢያ እንዳያደርጉለት የግርግር ወራት ሆነ በ፳፪ም ሆሳዕና ሆነ ፤ በ፳፫ም ርግመተ በለስ ወአንጽሖ ቤተ መቅደስ ሆነ ፡፡ በዓሉ ከበዓል ይዋል ብለው አበው የውኃ በዓል ከውኃ ብለው ቃና ዘገሊላን ከጥምቀት ጥግ እንዳዋሉት ትንሣኤው ከትንሣኤ ጋራ እንዲሄድ አደረጉ ። አንድም አልዓዛር በትንሣኤ ሥጋ እንደተነሣ እኛም ትንሣኤ ልቡና ፣ ትንሣኤ ህሊና እንነሣለንና ።
በዚህ ዕለት ትንሣኤና ሕይወት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ አልዓዛርን ከሞተ ከተቀበረ ከአራት ቀን በኋላ ማስነሣቱን ለአይሁድ ቅንዓት ለጌታ ሞት ምክንያት ከሆኑት ታላላቅ ተአምራት አንዱ የአልዓዛር ትንሣኤ መሆኑን አልዓዛርን በብሉይ ሥጋ በቃሉ ጠርቶ ከመቃብር ያስነሣው ጌታ በሐዲስ ሥጋ መነሣቱን ሞት ይይዘው ዘንድ የማይችል አምላክ መሆኑን እርሱ ለፍጥረት ሁሉ ትንሣኤና ሕይወት መሆኑን የምናምንበትን ሁሉ ትንሣኤ ዘለክብር የማያምኑበትን ትንሣኤ ዘለሐሳር ማስነሣት የሚቻለው ጌታ መሆኑን ፥ ቤተክርስቲን ታስባለች ፣ ታከብራለች ፣ ትሰብካለች (ዮሐ. ፲፩ በሙሉ)
ኀሙስ
ይህች ዕለት ‹‹ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ (አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም) ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ፤›› ተብሎ ቃል የተገባለት የአዳም ተስፋው ተፈጽሞ ከነልጅ ልጆቹ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመግባቱ መታሰቢያ ሆናየአዳም ኀሙስወይምአዳምተብላ ትከበራለች ሉቃ. ፳፬ ፥ ፳፭ - ፵፱ ፡፡
የአዳም ምሉዕ ተስፋው የተፈጸመለትን ምስጢር የምናስታውስበትና የምንዘክርበት ዕለት ነው ። ምክንያቱም ለክርስቶስ ሰው መሆን ዋና ምክንያቱ ጸሎተ አዳም ወሔዋን ነው ፡፡ ርደተ ሲኦልን በሚጠታቸው ፣ ርደተ መቃብርን በሙስና መቃብር ፣ ጽልመተ ሲኦልን በብርሃነ መለኮት ለውጦ ሞተ ሥጋ ወነፍስ ቀርቶላቸውኃጢአት ከበዛችበት ዘንድ ጸጋ እግዚአብሔር ትበዛለችብለው ያመሰገኑበት መታሰቢያ ነው ፡፡ አዳምና ሔዋን ከሲኦል የወጡት ዓርብ አይደለምን ኀሙስ መዘከሩ መከበሩ ለምንድን ነው ያሉ እንደሆነ ዓርብ የአምላካቸውና የመድኃኒታቸው የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ስለሆነ ዝክረ አዳም ኀሙስ እንዲከበርለት አበው ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው በይነዋል ። ያውስ ቢሆን ሰኞ ፣ ማክሰኞ ፣ ረቡዕ አለመዋሉ ኀሙስ መዋሉ ለምንድ ነው ቢሉ ፤ ከእሑድ እስከ ኀሙስ አምስት ቀን ይሆናል ። በኀሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እም ወለተ ወለትከ (አምስት ቀን ከእኩል ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ) ብሎት ነበርና እንደተፈጸመለት ለማጠየቅ ነው ። በዚህች ዕለት የሁላችን አባት ለአዳም የተሰጠው የተስፋ ቃል ስለመፈጸሙ አዳም ከነልጆቹ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻ ስለ መውጣቱ ይታሰባል ፣ ይዘከራል ፤ ይሰበካል ዘፍ. ፲፭
ዓርብ
ቤተ ክርስቲያን ትባላለች ። ጌታችን ከልደቱ እስከ ሞቱ ያደረገው የማዳን ጉዞ በሙሉ የተፈጸመው ዓርብ ነው ።ወይቤ ተፈጸመ ኵሉእንዲል ። ዓርብ የቤተ ክርስቲያን ሁለመናዊ ምስጢር የተፈጸመበት ዕለት ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን ትባላለች ። በእለተ ዓርብ ለቤተ ክርስቲያን መሠረት የሆኑ ዋና ዋና ምስጢራት ተሟልተዋል ። ለምሣሌ መስቀል ምልክቷ ሆኖ በመደኃኒትነት ተሰጥቶአታል ፤ የሕንጻዋ መሠረት ቀራኒዮ ተተክሎላታል ፤ የምትፈትተው ሥጋ መለኮት በቀራኒዮ ተቆርሶላታል ፤ ልጆቿን ከማኅጸነ ዮርዳኖስ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ የምትወልድበት ማየ ገቦ ፈስሶላታል ። ስብከት ፣ ትምህርት ፣ ተአምራት ፣ ትንሣኤ ተደርጎላታል ። ቤተክርስቲያን ይህንን ሁሉ ምሥጢራት ያገኘችው በዕለተ ዓርብ ስለሆነ እለቷ ቤተ ክርስቲያን ተብላ ተሰይማለች ። የዓርብ ትርጓሜው የሥራ መክተቻ ፣ ምዕራብ ፣ መግቢያ ማለት ነውና ።  
ከሆሣዕና ቅዳሜ በፊት ያለችው ዐርብ የጌታችን ዐርባው ጾም የሚፈጸምባት የጾመ ድጓው ቁመትም የሚያበቃባት ዕለት በመኾኗ በቤተ ክርስቲያንተጽዒኖትባላለች ፡፡ የከባድ ሥራ ማቆሚያ (ማብቂያ) ዕለት በመኾኗም በሕዝቡ ዘንድየወፍጮ መድፊያ ፣ የቀንበር መስቀያትባላለች ፡፡
ዳግኛም በመጀመርያ የሰው ልጆች አባትና እናት የኾኑት አዳምና ሔዋን ስለተፈጠሩባት ፤ በኋላም በሐዲስ ኪዳን ጌታችን ለቤዛ ዓለም ስለ ተሰቀለባትና የማዳን ሥራውን ስለ ፈጸመባትዕለተ ስቅለት፣ አማናዊቷ ዐርብትባላለች ፡፡
የሰሙነ ፋሲካዋ ማለትም የትንሣኤ እሑድ ስድስተኛዋ ዐርብ ደግሞ በክርስቶስ ደም ለተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መታሰቢያ ትኾን ዘንድቤተ ክርስቲያንተብላ ትጠራለች ማቴ. ፳፮ ፥ ፳፮ - ፳፱ ፤ ሐዋ. ፳ ፥ ፳፰ ፡፡
በዚህ ዕለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በክርስቶ ሞትና ትንሣኤ ስለ መመሥረቷ እራሱን ስለ እርሷ አሳልፎ ስለ መስጠቱ ቤተ ክርስቲያንም የእርሱ አካል ስለ መሆኗ (ኤፌ. ፳፩ ) ፣ የነቢያትና የሐዋርት መሠረት በሆነው በክርስቶስ ላይ ስለ መመሥረቷ መሰብሰቢያዋም ክርስቶስ ስለ መሆኑ (ኤፌ. ፲፱ - ፳፪ ) ፣ በክቡር ደሙ ፈሳሽነት ስለ መታጠቧ (ራዕ. ÷ - ፰ ) ከነገድ ከቋንቋ ስለ መመረጧ በደሙ ተዋጅታ አንድ መንጋ ስለ መሆኗ በሰማይ ሠራዊት በምድር የሰው ፍጥረት ያላገኘችውን ሕይወት በእርሱ ብቻ ስለ ማግኘቷ (ራዕ. በሙሉ) በወርቅ በብር ሳይሆን በክቡር በክርስቶስ ኢየሱስ ደም ስለ መዋጀቷ (ጴጥ. ፲፰ - ፳፩) ፣ ከልዩ ልዩ አነዋወር ተጠርታ በእርሱ ላይ ስለ መታነጿ (ጴጥ. -፮) እያሰበች ቤተክርስቲያን የቤተክርስቲያንን ሕይወት ትሰብካለች
ቀዳሚት ሰንበት
ቅዱሳት አንስት ትባለለች፡፡ በሰሙነ ፋሲካው ያለችው ቀዳሚት ሕዝቡ ከአንዳንዱ በስተቀር ገበያ እንኳን ስለማይገበያይባትየቁራ ገበያ ፣ የገበያ ጥፊያስትባል ፣ በቤተ ክርስቲያን ግን በዘመነ ሥጋዌው በገንዘባቸውና ጉልበታቸው ላገለገሉት ፤ በስቅለቱ ዋይ ዋይ እያሉ እስከ ቀራንዮ ድረስ ለተከተሉት ፤ በትንሣኤው ዕለት በሌሊት ወደ መቃብሩ ሽቱና አበባ ይዘው ለገሰገሱት ፤ በትንሣኤውም ጌታችን ከዅሉ ቀድሞ ለተገለጸላቸው ቅዱሳት አንስት መታሰቢያ ኾናቅዱሳት አንስትተብላ ትጠራለች ማቴ. ፳፭ ፥ ፩ - ፲፩ ፤ ሉቃ. ፳፫ ፥ ፳፯ - ፴፫ ፤ ፳፬ ፥ ፩ - ፡፡
 በዕለተ ትንሣኤ ሌሊቱን ሲመላለሱ ያደሩ ሴቶች የድካማቸውና ጌታን የመሻታቸው ዋጋ መታሰቢያቸው ነው ። ይህች እለት አንስት አንከራ ተብላም ትጠራለች ፡፡ አንስት አንከራ መባሉ ሌሊት ሲመላለሱ ሁለት መላእክት አይተው ከብሩህነታቸው የተነሳ የተደነቁበትና በመቃብሩ ያለውን መዓዛ ትንሣኤ አሽትተው የተመሰጡበት ዕለት ስለሆነ እንዲሁም ድካማቸው ከንቱ እንዳልሆነ ለማጠየቅ ነው ። አንድም ጌታችን አስቀድሞ ለእነርሱ ታይቶ ትንሣኤውን ያረጋገጠበት ስለሆነ እነርሱ ከአምላክነቱ ግርማ የተነሳ ረቡኒ ብለው ያደነቁበት ዕለት መታሰቢያ ነው ። አንድም በጠቅላላው ከሕማማቱ እስከ ትንሣኤው ብዙ የእንባ መሥዋዕት ያቀረቡ እናቶች የሚታሰቡበት ስለሆነ አንስት አንከራ ይባላል ።
በዚህ ዕለት የክርስቶስን አካል ሽቱ ለመቀባት ፍርሃታቸውን በክርስቶስ ፍቅር ለውጠው በጋለ ፍቅር አካሉን መፈለጋቸውን ወደ መቃብሩ ሲመላለሱ ማደራቸውን ማርያምም ትንሣኤውን ቀድማ ስለማየቷ ሴቶችም የመላእክትን ራእይ ስለ ማየታቸው ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች  ማቴ. ፳፰ - ፲፭ ፣ ማር. ፲፮ - ፣ ሉቃ. ፳፬ - ፲፪ ዮሐ. - ፲፰
እሑድ
ዳግም ትንሣኤ ነው ። በዚህች ሰንበት ከላይ እንደ ተጠቆመው ጌታችን በትንሣኤው ዕለት ማታ በዝግ ቤት ገብቶ ፣ በቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ተገኝቶ «ሰላም ለዅላችሁ ይኹን» ብሎ ትንሣኤውን ሲገልጽላቸው ሐዋርያው ቶማስ አልተገኘም ነበር ፡፡
ቶማስ ከሔደበት ሲመለስ ጌታችን እንደ ተነሣ እና እንደ ተገለጸላቸው ሐዋርያት በደስታ ሲነግሩት «በኋላ እናንተአየንብላችሁ ልትመሰክሩ ፤ ልታስተምሩ ፤ እኔ ግንሰምቼአለሁብዬ ልመሰክር ፤ ላስተምር ? አይኾንም ፡፡ እኔም ካላየሁ አላምንም» በማለቱ የሰውን ዅሉ ፤ ይልቁንም የመረጣቸው ወዳጆቹን የልብ ሐሳብ የሚያውቀው ፣ ቸርነቱ ወሰን የሌለው የባሕርይ አምላክ መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ  ክርስቶስ ልክ እንደ መጀመሪያው ትንሣኤ ዕለት ቅዱሳን ሐዋርያት በአንድነት ሳሉ በዝግ ቤት ገብቶ «ሰላም ለዅላችሁ ይኹን» በማለት በመካከላቸው ቆመ ፤ ቶማስንም «ያመንህ እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን ፤ እነሆ የተቸነከሩ እጆቼንና እግሮቼን ፣ የተወጋ ጐኔንም እይ ፤» ብሎ አሳየው ፡፡
እርሱም የችንካሩን ምልክት አይቶ ፣ የአምላኩን የተወጋ ጎኑን ዳስሶ ትንሣኤውንና አምላክነቱን እንደ ፍላጎቱ በመረዳቱ «ጌታዬ ፣ አምላኬ ብሎ መስክሮ» አመነ ፡፡ ስለዚህም የትንሣኤው ምሥጢር ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋርያት የተገለጠበት ዕለት በመሆኑ የትንሣኤው ሳምንት እሑድዳግም ትንሣኤተብሎ ይጠራል ፤ ይከበራል :: ዮሐ. ፳ ፥ ፳፬ - ፴ ፡፡
ዳግማዊነቱ ጌታችን ሳምንት ሰንብቶ ቶማስ በለበት በዝግ ቤት ዳግመኛ ስለተገለጸላቸው ዳግም ትንሣኤ ይባላል ። ምሥጢሩ ግን ከእሑድ ከቀዳማይ ትንሣኤ ጀምረው ቢቆጥሩ ስምንት ቀን ይሆናል ። አንድ ቀን እንደ አንድ ሺሕ ቆጥሮ ስምንት ሺሕ ይሆናል ። ዳግማይነቱ ለትንሣኤ ነውና በስምንተኛው ሺሕ ዘመን ዳግም በትንሣኤ ዘጉባኤ እንነሣለን ለማለት ዳግም ትንሣኤ ተባለ ።
በአጠቃላይ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሰሙነ ፋሲካ የሚፈጸመው መንፈሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዅሉ ልክ እንደ መጀመሪያው የትንሣኤ ሥርዓት ኾኖ ይከናወናል ፡፡ ብርሃነ ትንሣኤውን የገለጸልን አምላካችን ለብርሃነ ዕርገቱም በሰላም ያድርሰን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

No comments:

Post a Comment