Friday, September 9, 2016

ወርኃ ጳጉሜ

እንኳን ለወርኃ ጳጉሜ በሰላም አደረሰን 

የዘመናት ጌታ ቸሩ አምላካችን ቀሪውን ተረፈ ዘመን በሰላም አስፈጽሞ ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ ያሸጋግረን ፡፡ አሜን ፡፡

ውድ የማኅቶት ዘተዋሕዶ እድምተኞች እንደምን ከረማችሁ ?

ከዚህ በመቀጠል ውሉደ ተዋሕዶ ለፌስ ቡክ ገጼ ላይጳጉሜ ምን ማለት ነው ? ለምንስ አምስትና ስድስት ቀን ሆነች ? ብለው ለጠየቁኝ ጥያቄ አጠር ያለች መልስ እሰጣለሁ ተከታተሉኝ ፡፡ መልካም ንባብ ፡፡

ጳጉሜ ማለት ተረፍ ማለት ነው ፡፡ ከአስራ ሁለቱ የዓመቱ ወራት በዘመን ውስጥ የተረፈች ፣ የቀረች  ተረፈ ዘመን ናት ፡፡ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር አንድ ዓመት 365 ቀናት ፣ 6 ሰዓታትና 15 ኬክሮስ ነው ፡፡ ይህም ማለት አንድ ዓመት እያንዳንዳቸው ሣላሰ ሣላሳ ቀናት ያላቸው አስራ ሁለት ወራትና (ከመስከረም እስከ ነሓሴ) አምስት ቀናት ከስድስት ሰዓታት ያሉኣት አስራ ሦስተኛ ወር ወርኃ ጳጉሜ አሉት ፡፡ በዚህ መሠረት ጳጉሜ ወትሮ አምስት ቀን ከስድት ሰዓት ስትሆን በአራት ዓመት አንዴ (በዘመነ ዮሓንስ) ሽርፍራፊዎቹ ሰዓታት ተደማምረው አንድ ቀን ይሞላሉ ፡፡ በዚህ ጊዜ ጳጉሜ ስድስት ቀን ትሆናለች ፡፡

ለፍጡር ሁሉ ልኬትና ስፍር አለው ፡፡ እንደዚሁ ሁሉ ለዘመንም ልኬት ፣ ስፍርና ቁጥር  አለው ፡፡ ዘመን በቁጥር ይሰላል ፤ በሰዓታት ፣ በእለታትና በአዝማናት ተሰልቶ ይቀመራል ፡፡ በዚህ በዘመን ስሌት ቀመር ወርኃ ጳጉሜ አመስት ቀናት ስትሆን በዘመነ ዮሓንስ ስድስት ቀን ትሆናለች ፡፡ የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብርቅየ ሀብት ነው ፡፡

ከዚህ በተረፈ ሰፊውን ትንታኔ ለስነ ፈለካት የቤተ ክርስቲያን ሙሑራን ትቻለሁ ፡፡

ውድ ጠያቂዎቼ፡ ለጠቅላላ ግንዘቤ ይህችን ያህል ካልኩአችሁ አበው ሊቃውንት አስፍተው ፣ አራቀው ፣ አመስጥረውና ተርጉመው እንዲያስረዱችሁ ወደ ቤተ ክርስቲያን ጎራ በሉ የማኅቶት መልእክት ነው ፡፡

ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን ፡፡