ሆሣዕና ማለት መድኃኒት ማለት ነው ፡፡ ዕለቱ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ሆኖ ሆሣዕና በአርያም እየተባለ በምስጋና በይባቤ ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ የገባበት እለት ነው ፡፡
ቤዛ ዓለም ክርስቶስ በማዕከለ ምድር
በቀራኒዮ አደባባይ ተሰቅሎ የአዳምን በደል በመደምሰስ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለህ ብሎ የገባለትን ቃል ኪዳን ይፈጽምለት ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ ፡፡
ጌታችን ከቅዱሳን ሓዋርያቱ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ቀርበው ደብረ ዘይት በሚባል
ተራራ አጠገብ ወደ ቤተ ፋጌና ቢታንያ ሲደርሱ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን በፊታችሁ ወደለችው መንደር ሂዱ ከውርንጭላዋ ጋር የታሰረች
አህያ ታገኛላችሁ ፈታችሁ አምጡልኝ ፡፡ ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ አላቸው ፡፡ እነሱም የታዘዙትን አደረጉ ፡፡
አህያይቱን ከውርንጭላይቱ ጋር አመጡለት ፡፡ ልብሳቸውንም በአህዮቹ ላይ ጎዘጎዙለት ፡፡ እርሱም ተቀመጠባቸው ፡፡ ሕዝቡም ጌታን
አከበሩት ፡፡ በመንገዱም እጅግ ብዙዎችም ልብሳቸውን ፣ የዛፍ ቀንበጥ ፣ የዘንባባ ቅጣል አነጠፉለት ፡፡ ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በእግዚአብሔር
ስም የሚመጣ የተባረከ ነው ፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ አመሰገኑት ፡፡ ለእውራን ብርሃን ለአንከሶች ምርኩዝ ሆናቸው ፡፡ ችግረኞችን
ረዳ ሕሙማንን ፈወሳቸው ፡፡ መላ ኢየሩሳሌም ክብሩን አይታ ተደመመች ፡፡ ማቴ. ፳፩ ፥ ፩ - ፲፮ ፤ ማር. ፲፩ ፥ ፩ - ፲ ፤
ሉቃ. ፲፱ ፥ ፳፱ - ፴፰ ፤ ዮሓ. ፲፪ ፥ ፲፪ - ፲፭ ፡፡
በነቢዩ ዘካርያስ ፡- አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል
በይ ፤ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ፡፡ ትሁትም ሆኖ በአህያም በአህያይቱ ግልገል በውርንጭላይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል
የተባለው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ ፡፡ ዘካ. ፱ ፥ ፱ ፡፡
ነቢዩ ዳዊት በመዝሙር ፰ ፥ ፩
- ፪ ላይ አቤቱ ጌታችን ስምህ በምድር ሁሉ እጅግ ተመሰገነ ፤ ምስጋናህ
በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ ብሏልና ፡፡ ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ ስለጠላትህ ጠላትንና ቂመኛን ለማትፋት ብሎ
እንደተነበየው ፡- በኢየሩሳሌም ያሉ ሕጻናትም ክፋትን በማያውቅ ጥዑም አንደበታቸው ዘመሩለት ፡፡ ክፉዎች ፈሪሳውያን ግን አልተደሰቱም
ነበር ፡፡ አምላክ በፍጡራኑ ሲመሰገን ከፋቸው ፡፡ በቅንዓት በምቀኝነት ተነሳስተው መምህር ሆይ ደቀ መዛሙርትህ እንዳይጮሁብን ገስፃቸው
፡፡ ዝምም አስብላቸው ብለው ጠየቁት ፡፡ ጌታም እነዚህ ዝም ቢሉ አንደበት የሌላቸው ግዑዛን ድንጋዮች ያመሰግኑኛል አላቸው ፡፡
በዚች እለት ፡-
Ø ትንቢተ ነቢያት ተፈጽሟል
Ø ጌታ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ
መቅደስ ገብቷል
Ø ሕፃናት በነጸፃነት አመስግነዋል
Ø ሕሙማን ተፈውሰዋል
Ø አንደበት የሌላቸው ግዑዛን ድንጋዮች
አመስግነዋል
Ø ቤተ መቅደስ ከሥጋውያንና ሥጋዊ
ንግድ ነጻ ወጣች
Ø ምቀኞችና ትዕቢተኞች አፍረዋል
እኛም ምቀኝነታችንን ፣ ክፋታችንን
፣ ትዕቢታችንን ሁሉ ትተን በክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባ ጌታ ወደ
ልባችን እንዲገባ ሆህተ ልቡናችንን እንክፈትለት ፡፡ በትህትና ዝቅ ብለን ክብራችንን ሁሉ በፊቱ እናንጥፍ ፡፡ እርሱም በአደባባይ
ያከብረናል ፡፡ እንደ ኢየሩሳሌም አእሩግና ሕፃናት በቅን አንደበት እንዘምርለት ፡፡
የክርስቶስ ተከታዮች ነንና ችግረኞችን
በመርደት ፣ ለሚስኪናን በመራራት ፣ ሕሙማንን በመጠየቅ ፣ የታሰሩትን በማስፈታት ፣ ያዘኑትን በማረጋጋት ፣ የተረሱትን በማስታወስ
፣ በቀቢጸ ተስፋ የወደቁትን ከወደቁበት ሃዘን በማረጋጋት በግብር እንምሰለው ፡፡
የዕለቱ መዝሙር መነሻ ፡- ወእንዘ
ሰሙን
ምንባብ፡- ዕብ. ፫ ፥ ፩ - ፲፫
፣ ፩ዮሓ. ፩ ፥ ፮ - ፲ ፣ የሓዋ. ፭ ፥ ፳፮ - ፴፮
ምስባክ፡- እምአፈ ደቂቅ ወህፃናት
አስተዳሎከ ስብሓት በእንተ ፀላኢ እንዘ ትስቱ ለፀላኢ ወለገፋኢ ፡፡ መዝ. ፰ ፥ ፪
ወይም
ኦ እግዚኦ አድህንሶ ኦ እግዚኦ
ሠርሶ ቡሩክ ዘይመፅዕ በስመ እግዚአብሔር ፡፡ መዝ. ፩፻፲፯(፩፻፲፰) ፥ ፳፭ - ፳፮
ወስብሐት ለእግዚእብሔር
No comments:
Post a Comment