የአምላክ የማዳን ሥራው ድንገተኛ
ሳይሆን በቅዱሳን ነቢያት የተተነበየ፣ በተስፋ ሲጠበቅ የቆየ እንደሆነ ሁሉ ትንሣኤውም አስቀድሞ በነቢያት፤ በኋላም በራሱ በመዲኅን
ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የተነገረ የተስፋ አዳም ፍጻሜ፣ የድህነተ ዓለም መደምደሚያ ነው፡፡
በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ
በለቢሰ ሥጋ በኩነተ ሰብእ ያለ ዘርዓ ብእሲ ከቅድስት ድንገል ማርያም የተወለደው ፈቃዱ በሆነች ቅድስት ሞቱ ዓለምን ለማዳን ነው፡፡
የአምላኩን ትእዛዝ ተላልፎ በምክረ ሴይጣን ስቶ፣ በገቢረ ኃጢአት በነፍስ በሥጋ ለሞተው አዳም በደሉን ደምስሶ፣ እዳውን ክሶ፣ ቅድስት
ነፍሱን ሰጥቶ፣ በሞቱ ሕይወት ለመስጠት ነው፡፡
አይሁድ በክፋት ተነሳስቶው ምንም
በደል የሌለበት ንጹሃ ባህርይ ቤዛ ዓለም ክርስቶስን በመስቀል ላይ ሰቅለው፣ በብዙ መከራ አንገላተው ገደሉት፡፡ ባለ ጠጋው ደቀመዝሙር
የአርማትያሱ ዮሴፍና ሕግ አዋቂው ኒቆዲሞስ የኢየሱስን ቅዱስ ሥጋውን በንፁህ የተልባ እግር በፍታ በክብር ከፍነው፣ የከበረ ሽቱ
ረብርበው ይጸልይበት በነበረው በአትክልቱ ቦታ በጌቴሴማኒ በአዲስ መቃብር ቀበሩት፡፡ ማቴ. ፳፯፥፶፯-፷፣ ዮሐ. ፲፱፥፴፰-፵፡፡
ኢየሱስን እያገለገሉ ከገሊላ የተከተሉት
እነ መግደላዊት ማርያም በሩቅ ሆነው ሲመለከቱ በዚያ ነበሩና ክርስቶስ በተቀበረ በሶስተኛው ቀን መቃብሩን ለመቀባት ያዘጋጁትን ሽቱ
ይዘው ማልደው ወደ መቃብሩ ሄዱ፡፡ መቀብሩም ተከፍቶ ባዶውን አገኙት፡፡ የሚፈልጉትን የክርስቶስን ሥጋ በዚያ አላገኙምና ተደናግጠው
ሲያመነቱ የጌታ መላእክት ፀዓዳ ለብሰው ተገልጠው አናገሩአቸው፡፡ እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ፥ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ
ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤ ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው። ሕያውን ከሙታን መካከል
ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም ብለው ትንሣኤውን አበሰሩአቸው፡፡ ሉቃ. ፳፬፥፬-፭፡፡
ኃለፊያትና መጻኢያት የተገለጹለት
መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ የአምላክ ትንሳኤ ተገልጾለት በመዝሙር ፸፯፥፷፭ ላይ ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቀዕ አምንዋም
ወከመ ኃያል ወህዳገ ወይን ወቀተለ ፀሮ በድህሬሁ በማለት ከትንሳኤ ክርስቶስ ብዙ ዓመታት በፊት ዘምሯል፡፡ ነቢያት እንደተነበዩት
እርሱም ከሞቱ አስቀድሞ እንደተናገረው ክርስቶስ ኢየሱስ መቃብር ክፈቱልኝ፣ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ሙስና መቃብርን አጥፍቶ በስልጣኑ
ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷል፡፡
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቅድስት ቤተ
ክርስቲያናችን በአማን ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን ብላ ታምናለች፣ ትመሰክራለች/ታስተምራለች፡፡ አዎ ክርስቶስ በእውነት ተነስቷል፡፡
እርሱ ሕይወተ ኩሉ ነውና ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለም፡፡ ክፋተ አይሁድ፣ አቀብተ መቃብር፣ ማሕተመ መቃብር አላስቀሩትም፡፡ ሶስት
በዓልት ሶስት ሌሊት በከርሰ መቃብር ቆይቶ በሶስተኛው ቀን በሕቱም ድንግልና እንደተወለደ እንዲሁ መቃብር ከፋች መግነዝ ፈች ሳያሻው
በሕቱም መቃብር ተነሥቷል፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
አማናዊት ትንሣኤውን ለወደጆቹ/አማንያን ለማስረዳት ከትንሣኤው በኋላ ብዙ ጊዜ ተገልጦ ተይቶአቸዋል፡፡
ሀ. ከሁሉ በፊት ለመግደላዊት ማርያም፡
ዮሐ. ፳፥፩-፲፰
ለ. ለኤማሁስ መንገደኞች፡ ሉቃ.
፳፬፥፲፫-፴፩
ሐ. ቶማስ በሌለበት በዝግ ቤት
ለሓዋርያት፡ ዮሐ. ፳፥፲፱-፳፮
መ. በጥብርያዶስ ባሕር ለሐዋርያት፡
ዮሐ. ፳፩፥፩-፱
ሠ. ለአስራ አንዱ ሓዋርያትና ከእነርሱ
ጋር ለነበሩት፡ ሉቃ. ፳፬፥፴፫-፶፫
ረ. በስምንተኛው ቀን ቶማስ ባለበት
በዝግ ቤት ለሐዋርያት፡ ዮሐ. ፳፥፳፮-፴፩
በትንሣኤ ክርስቶስ ያገኘነው ፀጋና
በረከት፡-
o ትንሣኤ ሞትና ሲኦል የተሸነፉበት ነው፡፡
፩ቆሮ. ፲፭፥፶፭-፶፯ ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?
የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፤ ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።
o ትንሣኤ የሴይጣን ስልጣን የተሸረበት
ክርስቶስ ምርኮን የማረከበት ነው፡፡
ኢሳ. ፶፫፥፲፪ እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል
ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፡፡
ኤፌ. ፬፥፰ ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን
ሰጠ ይላል።
o ትንሣኤ በሞት ጨለማ የነበረ ሕዝብ
የሕይወት ብርሀን ያየበት ነው፡፡
ኢሳ. ፱፥፪ በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ
ብርሃን ወጣላቸው።
፩ተሰ. ፭፥፬-፭ እናንተ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ቀኑ እንደ ሌባ
ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም፥ ሁላችሁ የብርሃን ልጆች የቀንም ልጆች ናችሁና።
o ትንሣኤ እብነ ኃጢአትን ለመፈንቀል
ነጋ ለኪዳን ጠባ ለቁርባን ወደ መቃብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የምንገሰግስበት ነው፡፡
ዮሐ. ፳፥፩ ከሳምንቱም በፊተኛው
ቀን መግደላዊት ማርያም ገና ጨለማ ሳለ ማለዳ ወደ መቃብር መጣች ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሎ አየች።
o ትንሣኤ በመቃብር ያሉ ሙታን ድምጸ
እግዚአብሔርን የሚሰሙበት ጆሮ ነው፡፡
የሐ.፭፥፳፭ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ
የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ።
o ትንሣኤ ከዓለማዊ ከንቱ ምኞትና
ኃጢአት የምንርቅበት ቅዱስ ሕይወት ነው፡፡
ቲቶ. ፪፥፲፩-፲፬ ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም
ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን
የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር
ያስተምረናል፤ መድኃኒታችንም ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥
ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል፡፡
o ትንሣኤ ሞት የተሸነፈበት ዘለዓለማዊ
ሕይወት ነው
ዮሐ. ፲፩፥፳፭-፳፮ ኢየሱስም፦ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ
ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት።
o ትንሣኤ በሰው እጅ ያልተሠራ ሰማያዊ
ርስት እንዳለን ያወቅንበት ነው፡፡
፪ቆሮ. ፭፥፩ ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ
በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና።
ፊልጵ. ፫፥፳ እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን
እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፡፡
o ትንሣኤ በመላእክት ሥርዓት በሰማይ
የምንኖርበት ሕይወት ነው፡፡
ማቴ. ፳፪፥፴ አሙንቱሰ ይከውኑ በሰማያት ከመ መላእክተ እግዚአብሔር
(በትንሣኤስ
እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ እንጂ አያገቡም አይጋቡምም)።
o ትንሣኤ ሰማያዊ ኑሮን የምንናፍቅበት
ሰማያዊ ሀብትን የምናስብበት ነው፡፡
ሰው በምድር እያለ በሰማያዊ ሥርዓትና ሕግ ከእግዚአብሔር ጋር ሰማያዊ
ሕይወት የሚኖር ልዩ ፍጡር ነው፡፡
ቆላ. ፫፥፩-፭ እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር
ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ። በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም። ሞታችኋልና፥ ሕይወታችሁም
በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና። ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ
ጋር በክብር ትገለጣላችሁ። እንግዲህ በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፥ እነዚህም ዝሙትና ርኵሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም
ጣኦትንም ማምለክ የሆነ መጎምጀት ነው።
o ትንሣኤ ከኃጢአት እንቅልፍ የምንነቃበት
ነው፡፡
ኤፌ. ፭፥፲፬ ንቃዕ ዘትነውም ወተንሥዕ እሙታን ወያበርህ ለከ ክርስቶስ
(አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል ይላል)።
o ትንሣኤ ከሕይወት ከተማ ከኮበለልንበት
የኤማሁስ መንገድ የምንመለስበት የምስራች አዲስ የሕይወት ዜና ነው፡፡
ሉቃ. ፳፬፥፴፫-፴፬ በዚያችም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም
ተመለሱ፥ አሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም። ጌታ በእውነት ተነሥቶአል ለስምዖንም ታይቶአል እያሉ በአንድነት ተሰብስበው
አገኙአቸው።
በክርስቶስ ትንሣኤ ከሞት በላይ ሕይወት ከመቃብር በላይ ትንሣኤ መኖሩን
እንገነዘባለን፡፡ የሰው ልጅ ዐረፍተ ዘመን ሲገታው ነፍሱ ከሥጋው ተለይታ ሥጋው ወደ መቃብር የሚወርደው ለጊዘው ነው፡፡ ገበሬ የዘራት
አንዲት የስንዴ ቅንጣት ብዙ የምትፈራው መሬት ውስጥ ፈርሳ በስብሳ በመነሣት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ፩ቆሮ. ፲፭ ላይ
እንዳስተማረው ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን፣ ይህ የሚሞተው የማይሞተውን፣ ይህ ሥጋዊ
አካል መንፈሰዊውን አካል ለብሶ ዳግም ሕያው ሆኖ ይነሣል እንጂ ፈርሶ በስብሶ አይቀርም፡፡ ታሞ የሞው፣ አውሬ የበላው፣ አርጆቶ
የሞተው፣ ወንበዴ የገደለው፣ … ሁሉ በኩረ ትንሣኤ ክርስቶስን አብነት አድርጎ ምግባሩን ለብሶ ይነሣል፡፡
ይህ በኃለኛው ዘመን በትንሣኤ ዘጉበኤ የሚሆን ነው፡፡ ለእኛ በሕይወተ
ሥጋ ላለን እያንዳንዷ ቀን እለት ሞታችን እለተ ትንሣኤአችንም ናት፡፡ ከሕገ እግዚአብሔር ርቀን ጣኦት ስናመልክ፣ ሰው ስንበድል፣
ስንዋሽ፣ ስንሰርቅ፣ ጉቦ ስንቀበል በአጠቃላይ በኃጢአት ስንወደወቅ በሥጋ የቆምን ቢመስለንም በነፍስ እንሞታለን፡፡ ሞትሃ ለነፍስ
ርሂቅ እም እግዚአብሔር (የነፍስ ሞቷ ከእግዚአብሔር መለየቷ ነው) እንዲል፡፡ በኃጢአታችን ተጸጽተን በንሥኃ ወደ ነፍሳችን አረኛ
ወደ እግዚአብሔር ስንመለስ ደግሞ ከሞት ተነሥተን በሕይወት እንኖራለን፡፡ ስለዚህ በፈቃደ ሥጋ ተገንዘን በኃጢአት መወቃብር የወደቅን፣
በበደል አልጋ የተኛን፣ በኃጢአት ያሸለብን ሁሉ ዛሬ ትንሣኤ ልቡና ሊኖረን በንሥኃ ልንነሣ ይገባናል፡፡
በኃጢአት ወድቆ በንሥኃ መነሣት (መንፈሳዊውን ሀብት አጥቶ ማግኘት፣ በነፍስ
ታሞ መዳን፣ በዓለም ጠፍቶ ኖሮ መመለስ) ትንሣኤ ነው፡፡ ከኩኔ ወደ ጽድቅ፣ ከጨለማ ወደ ብርሀን፣ ከዓለማዊነት ወደ መንፈሳዊነት፣
ከቀማኛነት ወደ መጽዋችነት መመለስ ትንሣኤ ነው፡፡ ሰማያዊውን ሕይወት አስቦ ከአመንዝራነት ወደ ድንጋለ ህሊና መመለስ ትንሣኤ ነው፡፡
እንግዲህ ወገኖቼ ሆይ፡- ከፈቃደ ሥጋ፣ ከዐይን አምሮት መቃብር የምንነሣበት፣
ካሸለብንበት የኃጢአት እንቅልፍ የምንነቃበት ዛሬ መሆኑን አውቀን በንሥኃ፣ በትንሣኤ ልቡና በሕግ በአምልኮ ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ፡፡
ፈያታዊ ዘየማንን (ጥጦስ) እናስበው፡፡ የተሰጠችው ጊዜ ሶስት ሰዓት ብቻ ነበረች፡፡ በሚገባ ተጠቅሞባት ወደ ዘለዓለም ሕይወት ገባ፡፡
እኛም ዛሬ ጊዜ ተሰትቶናል፤ ሳያመልጠን እንጠቀምበት፡፡ አስከ ዛሬ ተንተናል፤ አሁን እንንቃ፣ ከሙታን መንደር እንውጣ፣ ከኃጢአት
መበቃብር በትንሣኤ ህሊና እንነሣ፡፡ የመዳን ቀን ዛሬ ነውና፡፡ ሮሜ. ፲፫፥፲፩ ወዘኒ ተአምሩ ከመ በጽሓ ጊዜሁ ለነቂህ እምንዋም
(ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና)።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment