Saturday, March 14, 2015

፭. ደብረ ዘይት



 አምስተኛው እሑድ ደብረ ዘይት ይባላል፡፡ ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ተራራ ማለት ነው፡፡ ደብረ ዘይት ብዙ የወይራ ዛፍ ያለበት ተራራ ሲሆን ስያሜውንም ያገኘው ከዚሁ ነው፡፡ ጌታ በደብረ ዘይት ተራራ ተቀምጦ ስለዳግም ምጽዓት ወይም የዓለም መጨረሻ ለቅዱሳን ሓዋርያቱ አስተምሯል፡፡ ጌታችን ቅዱሳን ሐዋርያቱን አስከትሎ ከመቅደስ ወጥቶ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሲሄደ ሐዋርያት የሰሎሞንን ቤተ መቅደስ ውበት የድንጋዩን አጠራረብ፣ ንድፈ ሕንፃውን፣ የወርቅ ዝምዝሙን፣ የሓር ጭምጭማቱን አይተው ተደነቁ፡፡ ግታም መልሶ፡- ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው። ይህን ውብ ሕንፃ የነደፉ እጆች በሞት ይታሰራሉ፣ ይሁን ድንቅ ንድፍ ያፈለቀ አእምሮ ይያዛል፤ በድንጋይ የተመሰለ ሕንፃ ሰውነታችሁ ይፈርሳ፣ በሞት ይለወጣል፡፡ ይህች በጨረቃ ደምቃ፣ በከዋክብት አሸብርቃ፣ በፀሓይ ሙቃ በውበቷ ምታማልላቸው ዓለም ታልፋለች አላቸው፡፡