Thursday, March 24, 2016

ዐቢይ ጾምና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ



ክፍል አንድ
 በመምህር ሙሴ ኃይሉ
በተለያዩ መጻሕፍት እንደተጻፈውና በተለያዩ የቤተክርስቲያናችን መምህራን ሊቃውንት በየዓውደ ምሕረቱ ዘወትር እንደሚተነተነው ጾም ማለት በታወቀ፣ በተወሰነ፣ በተቀመረ... ጊዜ ከመብል ከመጠጥ መከልከል፣ መቆጠብ፣ መወሰን... ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን "ጾም" ከክርስቲያናዊ ምግባርና ትሩፋት የሚመደብ ኣስተምህሮ ነው፡፡ ጾም የተመሠረተውም ሆነ የታዘዘው ከፈጣሬ ሰማያት ወምድር ከእግዚአብሔር ነው፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ምዕመን ጾምን በመከተል ለሠራዔ ጾም (ጾም ለሠራለት) አምላክ እየተገዛ፣ እያመለከ፣ እያከበረ፣ እየታዘዘ... በበጎ ሕሊና ተሞልቶ ፈቃደ ሥጋውን (ትዕቢት፣ ስስት፣ ዝሙት፣ ቅንዓት...) ለፈቃደ ነፍሱ (የዋህነት፣ በጎነት፣ ርህሩህነት...) በማስገዛት በፈጣሪ መመሪያ፣ ትእዛዝ እና ፈቃድ መኖር ማለት ነው፡፡