Monday, February 16, 2015

ጾም


ጾም (ጦም) ማለት ለተወሰነ ጊዜ እህል ከመብላት ውሃ ከመጠጣት መታቀብ ወይም ለተወሰኑ ወራት ከጥሉላት ምግቦች መከልከል ማለት ነው ፡፡ የጾም ሀይማኖታዊ ትርጉም ሰውነት ከሚያስፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ መከልከል ፤ መወሰን ፤ ለሰውነት የሚያጎመዠውን ነገር ሁሉ መተው ፤ ለሰው ሁሉ መልካሙንና በጎውን ማድረግ ፤ ሰውንም ሆነ እግዚአብሔርን  ከሚያሳዝን ክፉ ሁሉ መራቅ ነው ፡፡ ጾም ፈጣሪን መለመኛ ከሐጢአት ቁራኝነት መላቀቂያ መሣሪያ ስለሆነ በጾም ወራት ሕዋሳት ሁሉ ከክፉ ሥራ መቆጠብ አለባቸው ፡፡ ይጹም ዓይን ፤ ይጹም ልሳን ፤ እዝንኒ ይጹም እምሰሚዓ ሕሱም በተፋቅሮ [1]፡፡ አንድ ክርስቲያን በጾም ወራት ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ ሕዋሳቱን ሰውንና እግዚአብሔርን ከሚያሳዝኑ ክፉ ሓሳቦችና ተግባራት መቆጠብና መከልከል  አለበት ፡፡
የጾም ጥቅም ፡- ጾም የሥጋ ምኞትን የምታጠፋ ፤ የነፍስን ቁስል የምታደርቅ ፤ ለጎልማሶችም ጸጥታንና እርጋታን የምታስተምር ፤ ከእንስሳዊ ግብርና ጠባይ የምትከለክልና ፤ ሰው መላእክትን መስሎ የሚኖርባት ደገኛ ሥርዐት ናት ፡፡ ጾምን ጾመው የተጠቀሙ ቅዱሳን አበው ጾምን የጸሎት እናት ፤ የእንባ ምንጭ ፤ የጽድቅ መሠረት ፤ ብለዋታል[2]፡፡
እግዚአብሔር የጾምን ሥርዐት የሠራው አዳምን ፈጥሮ ወደ ገነት ባስገባበት ወቅት ነው ፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው ፡- ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ ፤ ነገር ግን መልካሙንና ክፉውን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ ፡፡ ዘፍ. ፪ ፲፯ ፡፡ ይህ አምላካዊ ትዕዛዝ ሁለት ተላላቅ ዓላማዎች አሉት ፡፡ አንደኛው ዓላማ  ፈጣሪና ፍጡርን ፤ ገዥና ተገዥን ፤ አዛዥና ታዛዥን የሚያስረዳ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የጾም ትምህርት ነው :: በሐዲስ ኪዳንም ጾም ሰው ሰራሽ ሕግ ሳይሆን ራሱ መዲኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው የሥራው ሁሉ መጀመሪያ አድርጎ የሠራው ሕግ ነው ፡፡ ማቴ. ፬ ፥ ፪ ፤ ሉቃ. ፬ ፥ ፪ ፡፡
በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሁለት ዐይነት አጽዋማት አሉ ፡፡ እነዚህም ፡-
ሀ. የሕግ አጽዋማት ፡- በሕግ በይፋ በትዕዛዝ የሚጾሙ የአዋጅ አጽዋማት ናቸው ፡፡
ለ. የፈቃድ አጽዋማት ፡- ያለአዋጅ በግል የሚጾሙ የፈቃድ አጽዋማት ናቸው ፡፡
ሀ. የሕግ አጽዋማት
ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያናችን በቀኖና የተቀመሩ በሕግ የታወጁ ሰባት አጽዋማት አሉአት ፡፡
 እነዚህም አጽዋማት፡-
      ፩ . ዐቢይ ጾም                                    ፭. ጾመ ገሃድ
 ፪ . ጾመ ሐዋርያት                                 ፮ .  ጾመ ነነዌ
      ፫ . ጾመ ፍልሰታ                                  ፯ . አርብና ረቡዕ ናቸው  
      ፬ . ጾመ ነቢያት
. ዐቢይ ጾም ፡- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ከተጠመቀ በኋላ ሳይውል ሳያድር እለቱኑ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄዶ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሞ ተላላቅ የሴይጣን ፈተናዎችን ድል ያደረገበት የአጽዋማት ሁሉ ርእስ ነው ፡፡ ማቴ. ፬ ፥ ፩ - ፲፩ ፤ ማር. ፩ ፥ ፲፪ - ፲፫ ፤ ሉቃ. ፬ ፥ ፩ - ፲፫ ፡፡ በዚህ ጾም ሶስቱ አርእስተ ኃጣውእ ስስት ፤ ትዕቢትና ፍቅረ ንዋይ ድል ሆነዋል ፡፡ ጌታችን ስስትን በመግቦተ እግዚአብሔር ፤ ትዕቢትን በትህትና ፤አፍቅሮ ንዋይን በፍቅረ እግዚአብሔር አሸንፏል ፡፡ ዐቢይ ጾም የባለበው ራሱ ጌታ ስለጾመውና የሴይጣን ጥበብና ፈተና ስለተሸረበት ነው ፡፡ ዐቢይ ጾም በሕዝቡ ዘንድ ሁዳዴ ይባላል ፡፡ ሁዳድ ማለት የመንግሥት መሬት ፤ የመንግሥት ርስት ማለት ነው ፡፡ የመንግሥት ሁዳድ በሚታረስበት ፤ አዝመራው በሚሰበሰብበት ጊዜ ልጅ አዋቂ ሳይባል የመንግሥቱ ዜጋ ሁሉ ለሥራ ታጥቆ እንደሚነሳ ይህንንም የጌታ ጾም የጌታ ሁዳድ የክርስቶስ ዜጎች የሆኑ ምዕመናን ሁሉ ይጾሙታልና የሁዳዴ ጾም ተባለ ፡፡ ዐቢይ ጾም ስንምንት ሳምንታት ሃምሳ አምስት ቀናት አሉት ፡፡ ከነዚህ ሃምሳ አምስት ቀናት ውስጥ ስምንት ቅዳሜና ሰባት እሁድ ይገኛሉ ፡፡ እነዚህም አስራ አምስት ቀናት ሲሆኑ ከጥሉላት እንጂ ከእህል ውሃ ስለመሰይጦሙ የጦሙ ወራት አርባ ቀን ብቻ ነው ፡፡
የቤተ ክርስቲያናችን የዜማ ፈርጥ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው በሁዳዴ ውስጥ ለሚገኙት እሁዶች ሁሉ የተለየ መዝሙር ስለሠራላቸው እያንዳንዱ እሁድ በመዝሙሩ ይጠራል ፡፡
 

[1]ድጓ ዘያሬድ
[2]ብርሀኑ ጎበና አምደ ሀይማኖት ሶስተኛ እትም %90- ገጽ 1))3

No comments:

Post a Comment