Tuesday, October 17, 2017

እመሰ ረሳዕኩኪ ኢየሩሳሌም ለትርስዓኒ የማንየ መዝ. ፻፴፮ ፥ ፭

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ዱ አምላክ አሜን

ኢየሩሳሌም ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ፡፡

በዲያቆን ዓለማየሁ ሀበቴ

 (ክፍል ፩)

ኢየሩሳሌም  ማለት ሀገረ ሰላም  ማለት ሲሆን ፤ በቅዱስ መጽሐፍ ከነዓን ፣ ምድረ ርስት ፣ የተስፋ ምድር ፣ ማርና ወተት የሚፈስባት ሀገር ፣ የዳዊት ከተማ በመባል ትታወቃለች[1] ፡፡ ኢየሩሳሌም እግዚኣብሔር ለአብርሀምና ለዘሩ ርስት አድርጎ የሰጠው  የተስፋ ምድር ናት ፡፡ እግዚአብሔርም አብራምን አለው ፡- ከአገርህ ፣ ከዘመዶችህም ፣ ከአበትህም ቤት ፣ ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ ፡፡ ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ ፣ እባርክሃለሁ ፣ ስምህንም አከብረዋለሁ ፤ ለበረከትም ሁን ፤ የሚባርኩህንም እባርካለሁ ፣ የሚረግሙህንም እረግማለሁ ፣ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ ፡፡ አብራምም እግዚአብሔር እንደ ነገረው ሄደ ፡፡ ከካራን ወጥቶም ወደ ከነዓን ምድር ገባ ፡፡ እግዚአብሔርም ለአብራም ተገለጠለትና ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ አለው ፡፡ ዘፍ. ፲፪ ፥ ፩- ፯ ፡፡