Monday, May 25, 2015

የመሥዋዕቱ በግ የት አለ ? ዘፍ. ፳፪፥፯

                                                                                                     በዲ/ን ዓለማየሁ ሀብቴ
              ክፍል ፩  
መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የኃጢአት ማስተሥርያ ነው፡፡ በዘመነ ብሉይ ሰው በአምላኩ ፊት ስለበደሉ መጸጸቱን (ንስሓ መግባቱን) ለማሳየት፣ ሞገስ ለማግኘት፣ እምነቱን ለመግለጽ፣ ምስጋና ለማቅረብ፣ ፍቅሩን ለማሳየት መሥዋዕት ያቀርብ (ይሰዋ) ነበር፡፡ በወቅቱም ለመሥዋዕት ከሚቀርቡት እንስሳት መካከል በግ ዋነኛው ነበር፡፡
አቤል በሕገ ልቡና ተመርቶ፤ በፍፁም እምነት፣ በንፁህ ሕሊና፣ በበጎ አእምሮ ለአምላኩ ለእግዚአብሔር ያቀረበው፤ አምላኩም ያሸተተለት ተወዳጅ መሥዋዕት ቀንዱ ያልከረከረ፣ ፀጉሩ ያላረረ፣ ጥፍሩ ያልዘረዘረ ፀዓዳ በግ ነው፡፡ ዘፍ. ፬-፭ አቤልም በግ ጠባቂ ነበረ (አርቢ)፤ ቃየንም ምድርን የሚያርስ (ገበሬ) ነበረ፡፡ ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፤ አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኩራትና ከስቡ አቀረበ፡፡ እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም፡፡