በሊቀ ትጉሃን ኃይለ ጊዮርጊስ ዳኘ
ሚያዝያ ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሰን!
«ትንሣኤ» የሚለው ቃል የግእዝ ቃል
መገኛው ‹ተንሥአ = ተነሣ› የሚለው ግስ
ሲኾን፣ ትርጕሙም መነሣት፣ አነሣሥ፣ አዲስ
ሕይወትን ማግኘት ማለት ነው፡፡ ‹ትንሣኤ› በየመልኩ፣ በየዓይነቱ ሲተረጐም አምስት ክፍል አለው፤
የመጀመርያው ትንሣኤ ሕሊና
ነው፤ ይህም
ማለት ተዘክሮተ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርን ማሰብ)
ነው፡፡
ሁለተኛውም ትንሣኤ ልቡና
ነው፤ የዚህም ምሥጢሩ ቃለ እግዘብሔርን መስማትና በንስሐ እየታደሱ በሕይወት መኖር
ነው፡፡
ሦስተኛው ትንሣኤ ለጊዜው (በተአምራት) የሙታን በሥጋ
መነሣት ነው፡፡ ነገር ግን በድጋሜ ሌላ ሞት ይከተለዋል፡፡
አራተኛው ትንሣኤ ክርስቶስ በሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱን ያመላክታል፡፡
የርእሰ ትምህርታችን መነሻም ይህ ነው፡፡
አምስተኛውና የመጨረሻው የትንሣኤ ደረጃ የባሕርይ አምላክ የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ መሠረት ያደረገ ትንሣኤ ዘጉባኤ ሲኾን፣ ይህም ከዓለም ኅልፈት በኋላ
ሰው ዅሉ
እንደየሥራው ለክብርና ለውርደት፣ ለጽድቅና ለኵነኔ በአንድነት የሚነሣው የዘለዓለም ትንሣኤ ነው፡፡