በዲ/ን ዓለማየሁ ሀብቴ
መስከረም ፳፩ ቀን ፳፻፱
ዓ/ም
መስቀል በዘመነ ብሉይ የወንጀለኛ መቅጫ መሣርያ የመረገም ምልክት ነበር፡፡ በጥንት
ፋርሶችና ሮማውያን ዘንድ ከባድ ጥፋት የፈጸሙ ወንጀለኞች በመስቀል ላይ ተሰቅለው ይቀጡ ነበር፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በሞቱ ሞትን ሽሮ፣ ኃጢአተ
አዳምን ደምስሶ፣ እዳ በደሉን ክሶ በኃይሉ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ከተነሳ በኋላ ወንጀለኞች ይቀጡበት የነበረው መስቀል ዲያብሎስ
የወደቀበት የድል አርማ፣ የክርስቲያኖች ምርኩዝ፣ የነፃነት ምልክት ሆኗል፡፡ ወወሀብኮሙ ትዕምርተ ለእለ ይፈርሁከ
ከመ ያምስጡ እም ገጸ ቀስት ወይድኅኑ ፍቁራኒከ (ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ፥ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው። ወዳጆችህ እንዲድኑ
መዝ.፶፱÷፬። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በገላ. ፫፥፲፫ ላይ በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ
ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን ብሎ አስተምሮናል፡፡
መስቀለ
ክርስቶስ እንደ እንቁ እያበራ፤ ድው በመፈወስ ሙት በመስነሳት በሚሠራቸው ተአምራት እየተሳቡ ብዙ አሕዛብ ክርስቲያን መሆን ጀመሩ፡፡
ከአይሁድም እንዲሁ አንዳንዶች ክርስትናን ተቀበሉ፡፡ ይህ የብዙዎች ወደ ክርስትናው መቀላቀል ክርስቶስን በምቀኝነት ተነሳስተው በመስቀል
ላይ ሰቅለው የገደሉትን አይሁድን አበሳጫቸው፡፡ እናንተ በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን
የአባቶቻችን አምላክ አስነሣው እንዲል የሐዋ.፭፥፴::
በዚህ
የተበሳጩት ሰቃልያነ ክርስቶስ አይሁድ የክርስቶስን መስቀል ደብዛውን አጥፍተው ከሰው ልቡና ለማስረሳት ቆርጠው ተነሱ፡፡
በኢየሩሳልም ከተማ አቅራቢያ ረባዳ ቦታ ላይ ትልቅ ጉድጓድ አስቆፈረው መስቀሉን ቀበሩት፡፡ የከተማዋ ቆሻሻ በዚያ እንዲጣል
አዘዙ፡፡ የከተማው ነዋሪ ሁሉ በየቀኑ ቆሻሻ ስለሚጥልበት ቦታውም ከሚጣለው ቆሻሻ ብዛትና ከጊዜ እርዝማኔ የተነሳ ጉብታ
(ኮረብታ) ሆነ፡፡
የኢየሩሳሌም
ክርስቲያኖች ባይፈቀድላቸውና መስቀሉን ማውጣት ባይችሉም ታሪኩንና ቦታውን ያውቁት ነበር፡፡ በኋላ ግን በጥጦስ ወረራ ወቅት (፸
ዓ/ም) ክርስቲያኖች ኢየሩሳሌምን ለቀው ተበታትነው፤ የከተማዋም መልክ ፈጽሞ ተለውጦ ስለነበር ታሪኩን ከማውሳት ባለፈ መስቀሉ
የተዳፈነበትን የሚያውቅ ጠፋ፡፡ በዚህ ምክንያት መስቀሉ ከሶስት መቶ ዓመታት በላይ ተቀብሮ ኖሯል፡፡
በኣራተኛው
መቶ ክፍለ ዘመን በ፫፻፳፯ ዓ/ም የታላቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌኒ የመስቀሉን ታሪክ ሰምታ ነበርና መስቀለ
ክርስቶስን ከተቀበረበት አስቆፍራ ለማውጣት ሠራዊቷን አስከትላ ወደ ኢየሩሳሌም አመራች፡፡ ኢየሩሳሌም ደርሳ መስቀሉ ያለበትን
ብትጠይቅ ብታስጠይቅ አውቃለሁ የሚል ሰው ጠፋ፡፡ ደጓ ንግሥት የኢየሩሳሌም ሽማግሌዎችን ሰብስባ መስቀሉ ያለበትን ቦታ
የምታገኝበትን ብልሃት እንዲነግሯት አማከረቻቸው፡፡ አነርሱም ከነዚህ በኢየሩሳሌም ዙርያ ከሚገኙት ኮረብታዎች አንዱ ይሆናል
ቦታውን በትክክል የሚያውቅ የለም አሉአት፡፡ ከእነርሱ ፍንጭ ማግኘት እንደምትችል አስባ መስቀሉ ያለበትን ኮረብታ ይነግሩአት
ዘንድ አስገደደቻቸው፤ ትቀጣቸውም ጀመር፡፡ ሽማግሌዎቹ የማይሆንላቸው ሲሆን ጥቂት ጊዜ ስጪን ብለው ወደ እግዚአብሔር
አመለከቱ፡፡ የመስቀሉ መውጣት ፈቃደ እግዚአብሔር ነበርና ስሙ ኪርያኮስ/ኪራኮስ-ድጓ/ (እንባቆምም ይሉታል) የሚባል አረጋዊ
እግዚአብሔር ገልጾለት ንግሥት አንቺም በከንቱ አትድከሚ ሰውም አታንገላቺ፡፡ እንጨት አሰብስበሽ በአንድ ላይ ከምረሽ እጣን
አፍሰሽበት በእሳት አያይዢው፡፡ የእጣኑ ጢስ/ጭስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ አቅጣጫውን አይተሽ አስቆፍሪው፡፡ በዚህ
ምልክት ተገኚአለሽ አላት፡፡ እሌኒ ንግሥት ሀሰሰት መስቀሉ እንባቆም/ኪራኮስ ነቢይ ዘአንከረ ግብሮ እንዳለ ቅዱስ ያሬድ፡፡
ንግሥት
እሌኒ አረጋዊ ኪራኮስ እንደመከራት አንድ ዳውላ እጣን ላይ ለሰባት ቀናት ( አንድ የቀን ሱባኤ) ጸሎተ ምህላ አስደርጋ
በሰባተኛው ቀን ችቦ አሳስራ ያሰባሰበችውን እንጨት ደመራ አስደምራ በእሳት አቀጣጥላ እጣኑን ጨመረችበት፡፡ የእጣኑ ጢስ ወደ
ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ መስቀሉ ያለበትን ቦታ በጣት ጠቅሶ የማሳየት ያህል መስቀሉ ያለበት ቦታ ላይ ሰገደ፡፡ ዘእጣን አንጸረ
ሰገደ ጢስ እንዲል ድጓ፡፡
በዚህ
ምልክት ተመርተው መስረም ፲፯ ቀን ፫፻፳፯ ዓ/ም ቁፋሮ ተጀምሮ መጋቢት ፲ ቀን ፫፻፳፯ ዓ/ም መስቀሉ ለዘመናት ከተዳፈነበት
ወጣ/ተገኘ፡፡ የተገኙት መስቀሎች ሶስት ስለነበሩ ከሶስቱ ጌታ የተሰቀለበትን ለመለየት ድውያንን መጥተው እንዲዳስሱ ቢደረግ
ሁለቱ ማዳን ድው ማድን አልተቻለቸውም፡፡ አንዱ ድውያን ቢዳስሱት ፈወሳቸው፡፡ ሙት አምጥተው ቢጥሉበት አፈፍ ብሎ ተነሳ፡፡
የክርስቶስ መስቀል በእለተ አርብ በክርስቶስ ግራና ቀኝ ሁለቱ ሽፍቶች ከተሰቀሉባቸው መስቀሎች በገቢረ ተአምራት ተላየ/ታወቀ፡፡
ከዚህ
በኋላ ንግሥት እሌኒ በመካነ ስቅለቱ በጎልጎታ ትልቅ በተ መቅደስ አሠርታ መስቀሉን በዚያ በክብር አኖረችው፡፡ በዚያ
በኢየሩሳሌም መስቀሉ የሚሠራቸው ገቢረ ተአምራት በዙ፡፡ ዝናው በዓለም ሁሉ ተሰማ፡፡ በዓለም ያሉ ኃያላን ነገሥታት መስቀሉን
ወስደው የግላቸው ንብረት ለማድረግ መቋመጥ ጀመሩ፡፡ ከዘመኑ ኃያላን ነገሥታት አንዱ የፋርስ ንጉሥ ሆሎኮስ መስቀሉን ማርኮ ወደ
ሀገሩ ፋርስ ወሰደው፡፡ በዚህ ያዘኑ የኢየሩሳሌም ምእመናን ለሮሙን ግጉሥ ሕርቃል በመስቀሉ መማረክ ማዘናቸውን ገልጸው መስቀሉ
በማስመለስ እርዳን ብለው ጠየቁት፡፡ ንጉሥ ሕርቃልም በእርዳታ ጥሪያቸው ተስማማ፡፡ ወደ ፋርስ ወርደው ተዋግተው መስቀሉን
በክብር ወደ ኢየሩሳሌም መለሱት፡፡
አሁንም
መስቀሉን እኔ እወስድ እኔ እወስድ በማለት በዓለም ላይ ያሉ ኃያላን ነገሥታት ከፍተኛ ፍጥጫ ውስጥ ገቡ፡፡ ጠቡ እንዳይካረር
የኢየሩሳሌም፣ የቁስጥንጥንያ፣ የአንጾኪያ፣ የኤፌሶን፣ የአርማንያ፣ የግሪክና የእስክንድርያ የሀይማኖት መሪ አበው ጥላቻን
አጥፍተው ሰላምን ለማስፈን የጌታን መስቀልና ሌሎች ንዋየ ቅድሳትን በእጣ እንዲከፋፈሉ አደረጉ፡፡ በዚሁ መሠረት መስቀሉ ለኣራት
እጣ ተከፍሎ እጣ ሲጣል የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀኝ እጁ ያረፈበት ግማደ መስቀል ለአፍሪካ አህጉር ደረሳት፡፡
ይህ ግማደ መስቀል ከሌሎች ንዋየ ቅድሳት ጋር ወደ ግብጽ መትቶ የእስክንድርያው ፓትርያርክ በክብር አስቀመጠው፡፡
ይቆየን!
No comments:
Post a Comment