Tuesday, September 27, 2016

ዝንቱ መስቀል ለአዳም ዘአግብኦ ውስተ ገነት፡፡

                                                                                                                         በዲ/ን ዓለማየሁ ሀብቴ
                                                                                                                    መስከረም ፲፯ ቀን ፳፻፱ ዓ/ም

የሰው ልጅ ሕገ እግዚአብሔርን በመጣስ ላመጣው የነፍስ በሽታ መድኃኒት ያገኘው ከክርስቶስ መስቀል ነው፡፡ በአዳም በደል ምክንያት በውርስ ይተላለፍ የነበረዉ ጥንተ አብሶ ለተባለዉ ደዌ ነፍስ በመስቀል በፈሰሰዉ ደመ ክርስቶስ ዓለም መድኃኒት አግኝቷል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእለተ አርብ (እለተ መድኃኒት) በመስቀል ላይ ባፈሰሰዉ ደመ ማህም ፌያታዊ ዘየማን ከአዳም ቀድሞ ገነት ገብቷል፡፡ አንተ ትቀድሞ ለአዳም በዊአ ዉስተ ገነት እዳለ ጌታ፡፡ ኢየሱስንም። ጌታ ሆይ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለው። ኢየሱስም። እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው።ሉቃ.፳፫÷ ፵፪-፵፫፡፡
ጌታችን በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደም አዳም ከዘላለም ባርነት (ከግብርናተ ዲያብሎስ) ነፃ ወጥቷል፡፡ ዝንቱ መስቀል ለአዳም ዘአግብኦ ውስተ ገነት (አዳምን ወደ ገነት የመለሰው ይሄ መስቀል ነው) እዲል፡፡ ብርሀነ ዓለም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ " በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ።" ይለናል ገለ.፭÷፩፡፡
በጌታችን መስቀል እዳ በደላችን ተደምሰሰ፣ ሲኦል ተመዘበረች፣ የሞትየ ኃይል ተሻረ፡፡ ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ? የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፤ ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። ፩ቆሮ.፲፭÷፶፭-፶፯፡፡
በመስቀለ ክርስቶስ በሰዉና በእግዚአብሔር መካከል የነበረዉ የጥል ግድግዳ (ኃጢአት) ፈርሶ ሰላም ሰፍኗል፡፡ እኛም የእግዚአብሔር ልጆች፣ የመንግሥቱ ዜጎች፣ የክብሩም ወራሾች ሆንን፡፡ ለዚህ እናንተ አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባላችሁ፥ ይህን አስቡ፤ በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ። አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፤ በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና። እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም። በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤ በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ። ኤፌ.፪÷፲፩-፳፪፡፡
በመስቀል ሰፍኖብን የነበረዉ የሴይጣን ኃይልና ስልጣን ተደመሰሰልን፡፡ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስን የምንቀወምበት ስልጣን ተሰጠን፡፡ በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል። አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። ቆላ.፪÷፲፬-፲፭፡፡
በዕፀ በለስ ምክንያት ለመጣዉ የሞት በሽታ በመስለ ክርስቶስ ፍቱን መድኃኒት አግኝተናል፡፡ ነግሶብን የነበረዉ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የጠፋልን በመስቀል ነዉና፡፡ እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤ እናንተ ቀድሞ ወገን አልነበራችሁም አሁን ግን የእግዚአብሔር ወገን ናችሁ፤ እናንተ ምሕረት ያገኛችሁ አልነበራችሁም አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል። ፩ጴጥ.፪÷፱-፲፡፡ 
በጌታችን መስቀል ላይ ዘለዓለማዊ የሕይወት ምግብ ተፈትቶልናል፤ ዘለዓለማዊ የሕይወት መጠጥ ፈሶልናል፡፡ መስቀል የዘለዓለም ማዕድ የተፈተተበት የሕይወት ገበታ ነው፡፡ ስለዚህም መስቀል ኃይልነ፣ መስቀል ፅንዕነ፣ መስቀል ቤዛነ፣ መስቀል መድኃኒተ ነፍስነ ብለን እንፀልያለን፡፡ መፅናኛነቱን፣ ቤዛነቱን፣ መመኪያነቱን፣ መድኃኒትነቱን አምነን ኃይላችን መንፈሳዊ አርማችን መሆኑን እንመሰክራለን፡፡ መስቀል ከጠላት ማምለጫ ቀስት መመከቻ ምልክታችን ነውው፡፡ ወወሀብኮሙ ትዕምርተ ለእለ ይፈርሁከ ከመ ያምስጡ እም ገጸ ቀስት ወይድኅኑ ፍቁራኒከ (ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ፥ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው። ወዳጆችህ እንዲድኑ መዝ.፶፱÷፬። ቅዱስ ጳውሎስም፡- ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ ብሏል። ገላ.፮÷፲፬፡፡
ንግሥት እሌኒ መስቀሉን በብዙ ድካም ፈልጋ ያገኘችዉ ይህን ስሐምታዉቅና ስለምታምን ነዉ፡፡ እሌኒ ንግሥት ሀሰሰት መስቀሉ ኪራኮስ ነብይ ዘአንከረ ግብሮ እንዳለ ቅደሐስ ያሬድ፡፡ መድኃኒትነቱን አዉቃ መስቀሉን ፈልጋ አገኘች፡፡ እጅግ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እኛም የመስቀሉ ፈላጊዎች፤ በቅዱስ መስቀሉም መድኃኒትነት ተጠቃሚዎች ለመሆን መትጋት አለብን፡፡ 
በዓለማችን የመስቀሉ መድኃኒትጀት ያልገባቸዉ ለመስቀሉ ጠላት ሆነዉ የሚኖሩ ወገኖች አሉ፡፡ ኃጢአት፣ ድንቁርና ልቦናቸዉን ያሳወራቸዉ፣ በዓለም ሞኝነት ተጠልፈዉ የወደቁ፣ በሴይጣን ወጥመድ የተያዙ የጥፋት ልጆች ናቸዉ፡፡ ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ። መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። ፊል.፫÷፲፰-፲፱፡፡ 
እነዚህ ሞኝ ተላላዎች መስቀልን ለምን ትጠላላችሁ ለምን አታከበሩም ሲባሉ አባታችን የሞተበትን መስቀል እንዴት እናከብራለን? አባታችን በመስቀል ስለምተ መስቀልን አንወድም ይላሉ፡፡ አይ አለማወቅ ክርስቶስ እኮ በመስቀል ተሰቅሎ የምተው ለመድኃኒትነት ነዉ እንጂ ሞት አሸንፎት አይደለም፡፡ እርሱማ ክብር ይግባዉና በመስቀል ላይ በፈፀመዉ ቤዛነት አዳምን አድኖ ሙስና መቃብርን አጥፎቶ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፎቱልኝ ሳይል በኃይሉ ተነስቷል፡፡ ይልቅስ በመስቀል ድል የተመታ፣ ስልጣኑ የተሻረ፣ ኃይሉ የሞተ፣ የተጎዳ የግብር አባታቸው ሴይጣን ነው፡፡ ለክርስቶስ መስቀል ጠላት ሆነው በሞኝነት ወደ ጥፋት ጎዳና እየነጎዱ ናቸዉ፡፡ " የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና። ፩ቆሮ.፩÷፲፰፡፡ 
እኛ ግን ኃይላችን መስቀል ነዉና መስቀል ክርስቶስ ዓለሙን ያዳነበት ልዩ የክብር ዙፋን መሆኑን እናምናለን፡፡ ያለሀፍረት የአክብሮት ሰግደትም እሰግድለታለን፡፡ በእንተ ዝንቱ አዘዙ መምህራነ ወንጌል ቅዱስ ንስግድ ለመስቀል ወለማርያም (ቅዱስ ያሬድ)፡፡ መዝሙረኛዉ ዳዊትም በመዝሙር ፩፻፴፩÷፯ ላይ ወረከብናሁ ዉስተ ኦመ ገዳም፡፡ ወንበዉእ እንከሰ ውስተ አብያቲሁ ለእግዚአብሔር ወንሰግድ ውስተ መከን ሀበ ቆመ እግረ እግዚእነ (እነሆ፥ በዱር ውስጥም አገኘነው። ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን፤ እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን በማለት ለክቡር መስቀሉ ዘምሯል፡፡ 
እኛም መገብተ ሀይማኖት መምህራነ ወንጌል ባስተማሩን ደገኛ ሕግ ፀንተን ጌታችን የተሰቀለበትን ቅዱስ መስቀል እናከብረዋለን፣ ጠላታችን ዲያብሎስን ድል እንነሳበታለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ልዑል፡ ወለወላዲቱ ድንግል፡ ወለመስቀሉ ክቡር፡፡

No comments:

Post a Comment