Saturday, February 24, 2018

ልቡና (ጾም)

ለብሉይ ሰውነታችን ሕዋሳትን ሁሉ እየቃኘ በበጎ ሥራ የሚያውቸው እንደ ንጉሥ የሚያዝ ልቡና አለው፡፡ ያለ ልቡና መሪነት ሕዋሳት ሁሉ ምንም ለሠሩ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ልቡና የሌለው ሰው እብድ ዝንጉዕ ይባላል እንጂ ሕያው ሰው አይባልም፡፡
እንደዚሁም ለሐዲሱ ሰውነታችን ሥራዎቹን የሚያከናውንበት የሥራ መሪው ጾም ነው፡፡ ያለ ጾም መሪነት ምንም በጎ ሥራ ሊሠራ አይችልም፡፡ ይህንንም ወደ ሌላ ሳንሄድ በልተን ጠጥተን በጠገብን ጊዜ የሚሰማን ስሜትና በምንጾበት ወራት የሚሰማን ስሜት ብናመዛዝነው ልንረዳው እንችላለን፡፡
ነገሩም እንደዚህ ነው፡፡ በበላን በጠጣን ጊዜ ኃይለ ፍትወት እየበረታ በመሄዱ መልአካዊ ጠባያችን ወደ እንሰሳዊ ጠባይዕ መለወጡ አይካድም፡፡
እንግዲህ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጳውሎስ በሮም ክታቡ በልቡናየ ያለ ሕገ እግዚአብሔር ያማረ ነበር፡፡ ነገር ግን ሌላ ሕገ ኃጢአት በሰውነቴ ውስጥ አገኘሁ፡፡ ይህ በሰውነቴ ያለ ሕገ ኃጢአት መብል መጠትን የጦር መሣርያ ይዞ፣ ሰውነቴን የጦር ሜዳ አድርጎ፣ በውስጤ ካለ ሕገ እግዚአብሔር ጋራ ተዋግቶ ድል አድርጎ ማረከኝ፡፡ ስለዚህ በሥጋ በደም ለኃጢአት የተሸጥኩ የተለወጥኩ ሆኛለሁና ያንን የምጠላውን የማልወደውን ኃጢአት በግድ እሠራለሁ እንጂ የምወደውን  ሕገ እግዚአብሔርን ልሠራ አልቻልኩም ያለው ደርሶብን፤ እኔ የተዋረድኩ ሰው ነኝ እንግዲህ ከጎስቋላ ከወራዳ ሰውነቴ ማን ባዳነኝ እያልን ሑሩ እምኔየ ከመባል የማያድን፣ የማይረባ፣ የማይጠቅም የጸጸትና የምኞት ቃል እንናገራለን፡፡
ከመብል ከመጠጥ ተከልክለን በሕግ እንደተወሰነው ብንጾም ግን ኃይለ ፍትወት እየደከመ በመሄዱ በእኛ ያለ እንስሳዊ ጠባይዕ ወደ መልአካዊ ጠባይዕ መለወጡ አይጠረጠርም፡፡
ስለዚህ ያ በማናቸውም ጊዜ ልንፈጽመው የምንወደው ስዒን የሚያስቀርብን ሕገ እግዚአብሔር ኃይል አግኝቶ፣ ጾምን የጦር መሣርያ አድርጎ፣ ተዋግቶ፣ ያንን ሳንወድ በግድ የምንገዛለትን ሕገ ኃጢአት ድል ነሥቶ ወደ እርሱ ይማርከናል፡፡
ያን ጊዜ እኛም በራሳችን የሀይማኖት ቁር (ቦርቦርቴ) ደፍተን፣ ወገበ ልቡናችንን በንጽሕና ዝናር ታጥቀን፣ ምግባረ ወንጌልን እንደ ጫማ ተጫምተን፣ መንፈስ ቅዱስን እንደ ሴይፍ መዘን፣ ጸሎትን እንደ አላባሽ ጋሻ መክተን፣ ፍቅርን እንደ ጽሩር ለብሰን፣ ያለፍርሃት ተጸርረን ቆመን የክርስቶስን ፍቅር ሊያስተወን የሚችል ማነው? ሕማም ነውን፣ ምዳቤ ነውን፣ ስደት ነውን፣ ረሃብ ነውን፣ መራቆት ነውን፣ ችጋር ነውን፣ ማነው ሊለየን የሚችል፤ እኛስ በጾም ሁሉን ድል እንነሣለን እንጂ ድል የሚነሣን ከክርስቶስ አንድነት የሚለየን የለም እያልን ልንፈክር (ልንመከ) እንችላለን፡፡
አሁን ከዚህ በላይ በተናገርናቸው ንግግሮች በመሰልናቸው ምሳሌዎች ጾም ለትሩፋት አበጋዝ መሪ ሠሪ እንደሆነ ልንረዳ ችለናል፤ ተረድተናል፡፡
እንግዲህ ይህ ሐዲሱ ሰውነታችን ጾምን አስተዋይ ልቡና አድርጎ በጾም ልብነት እያሰበ እያስተዋለ ከላይ በተዘረዘሩት መሣርያዎች ተሰልፎ ተጸርሮ ካልተገኘ ጠባዪን መወሰን መግታት አቅቶት ከዚህ ከጎስቋላ ሰውነቴ ማን ባዳነኝ የሚል ከሆነ እንደዚያው እንደ ብሉዩ ሰውነት እብድ ዝንጉዕ ይባላል እንጂ ሐዲስ ሰው ኢየሱስ ክርሰቶስን መምሰል፣ ሐዲስ ሰው መባል አይገኝምና ሐዲስ ሰው ሆኖ ክርስቶስን መስሎ ለመገኘት ጾምን መሣርያ አድርገን እንትጋ አንስነፍ ይህ እንስሳዊ ፍትወት ድል አይንሳን፡፡     
ምንጭ፡- ሐዲስ ሰውነት በመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ሁለተኛ እትም (îÿÿó)  


           

No comments:

Post a Comment