በዲ/ን ዓለማየሁ ሀብቴ
መስከረም ፳፩ ቀን ፳፻፱ ዓ/ም
ግማደ
መስቀሉ ለብዙ ዘመናት በእስክድርያ በክብር ተቀምጦ እያለ የግብጽ እስላሞች ቁጥራቸው እየበዛ በመምጣቱ የኃይል የበላይት
አግኝተው የእስክንድርያ ክርስቲያኖችን መከራ አብዝተውባቸው ማሰቃየት ጀመሩ፡፡ ይባስ ብለውም ሁለቱን ንዑዳን ክቡራን ጳጳሳት
አባ ሚካኤልና አባ ገብርኤልን አስረው ያሰቃዩአቸው ጀመሩ፡፡ የእስክንድርያ ክርስቲያኖች በዘመኑ ኃያል ለነበረው የኢትዮጵያ
ንጉሥ አፄ ዳዊት፡- ታላቁ ንጉሥ ሆይ እግዚአብሔር ኃይል እንዳበዘልህ እናውቃለን፡፡ በእኛ በእስክንድርያ በለን ክርስቲያኖች
ላይ በዚህ በግብጽ ያሉ እስላሞች ስቃይ አጽንተውብናል፡፡ ኃይልህን አንስተህ እስላሞቹን አስታግስልን፡፡ ጳጳሳቱ አባ ሚካኤልና
አባ ገብርኤልም አስረውብናል፡፡ እነርሱንም አስፈታልን ብለው መልእክት ላኩ፡፡
አፄ
ዳዊትም መልእክቱ እንደ ደረሳቸው ከብዙ ሠራዊት ጋር መነኮሳትን፣ ባሕታውያንንና ካህናትን አስከትለው ወደ ግብጽ ጉዞ ጀመሩ፡፡
በጉዞአቸውም በዛሬቱ ሞቃድሾ (መቅደስ ማለት ነው፡፡ የመድኃኒዓለም ቤተ መቅደስ ነበረባት) ላይ አርፈው ታላቅ ጉበኤ አደረጉ፡፡
ጉባኤውም፡-
ሀ.
ሁለቱ ጳጳሳት በአስቸኳይ እንዲፈቱ
ለ.
በእስክንድርያ ክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰው ግፍ እንዲቆም
ሐ.
የክርስቶስ ግማደ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ወሰነ፡፡
ለአደን
ወደ ጫካ በሄደው ሠራዊት ላይ የአንበሳ መንጋ ከፍተኛ ጉዳት ስለአደረሰ ንጉሡ የሞቱትን ቀብሪ ዳሃር (ከቀብር መልስ ማለት
ነው) ላይ ቀብረው የቆሰሉትን አንስተው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ፡፡
አፄ
ዳዊት ብዙ ሠራዊት ይዘው ወደ ግብጽ ዘመቱ፡፡ ሱዳን ካርቱም (ሲናር) ላይ ከተሙ፡፡ የግብጽ ኃያላን የአፄ ዳዊትን መምጣትና
ያስከተሉትን ሠራዊት ብዛት ሰምተው ደነገጡ፡፡ ፈርተውም የፈለጉትን ቢጠይቁ ሊፈጽሙላቸው ተስማምተው ይቅርታ ለመጠቅ ከእጅ መንሻ
ጋር መልእክተኞችን ንጉሡ ወደ አረፉበት ወደ ሲናር (ካርቱም) ላኩ፡፡ አፄ ዳዊት ሱዳን ካርቱም ላይ ሆነው ሁለቱ ጳጳሳት
በአስቸኳይ እንዲፈቱ እስላሞች ከክርስቲያኖች ጋር እንዲታረቁ ብለው መልእክተኞችን ወደ ግብጽ ላኩ፡፡ ግብጾቹም ወዲያው ከክርስቲያኖች
ጋር ታርቀው ሁለቱን ጳጳሳት ከእስር ፈትተው እጅ ወርቅና ብር አስይዘው ወደ አፄ ዳዊት ለኩአቸው፡፡ አፄ ዳዊትም እስላሞች
ከክርስቲያኖች ጋር ስለታረቁና ጳጳሳቱ ስለተፈቱ ደስ ብሎኛል የላካችሁልኝን ገጸ በረከት ግን አልቀበልም፡፡ እኔ የምፈልገው
የክርስቶስን መስቀል ነው፡፡ በሀገሬ ኢትዮጵያ ረሀብ ቸነፈር ገብቷል፡፡ ከዚህ ችግር የሚታደነኝ የጌታዬ የክርስቶስ መስቀል
ነው፡፡ ግማደ መስቀሉን በአስቸኳይ እንድትልኩልኝ፡፡ ይህ ባይሆን ግን ሀገራችሁን ግብጽን በጦር ወግቼ የጌታዬን መስቀል በምርኮ
ወደ ኢትዮጵያ አወስደዋለሁ ብለው አስጠንቅቀው ወደ ግብጽ መልሰው ለኩ፡፡ አባ ሚካኤልና አባ ገብርኤልን ግን ከእርሳቸው ዘንድ
አቆዩአቸው፡፡ ግብጾቹም አፄ ዳዊት ገናና ኃያል ንጉሥ ነበሩና ጦርነቱን ፈርተው ግማደ መስቀሉን አጽመ ቅዱሳንን ጨምሮ ከብዙ
ንዋየ ቅድሳት ጋር ለአፄ ዳዊት ላኩላቸው፡፡ ግማደ መስቀሉ በወርኀ መስከረም በታላቅ ክብር ሱዳን ካርቱመም (ሲናር) ገባ፡፡
በዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ ለሶስት ቀናት ታላቅ ብርሀን ሆነ፡፡ ንጉሡም በጣም ተደሰቱ፡፡
ግማደ
መስቀሉ ወደ መሀል ሀገር ኢትዮጵያ ሳይገባ አፄ ዳዊት ከበቅሎአቸው ወድቀው እዚያው ሲናር በረሃ (ሱዳን ውስጥ) አረፉ፡፡
በምትካቸው ቆስጠንጢኖስ ዘኢትዮጵያ ተብለው የነገሡት ልጃቸው አፄ ዘርዓያዕቆብ ወደ ሲናር ሄደው ከከበሩ ንዋየ ቅድሳት ጋር ግማደ
መስቀሉን ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ አመጡት፡፡
በዋና
ከተማቸው በደብረ ብርሀን ለግማደ መስቀሉ መቅደስ አሠርተው የከበረ ማረፊያ እስከሚያዘጋጁለት ድረስ በመናገሻ አምባ አስቀመጡት፡፡
ንጉሡ ለግማደ መስቀሉ ማረፍያ ሊያሠሩለት ላይ ታች ሲሉ ጌታ፡- አንብር መስቀልየ ዲበ መስቀል (መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ ላይ
አስቀምጥ) በሚል ራዕይ በተደጋጋሚ ያዛቸው ጀመረ፡፡ መስቀለኛ ቦታ አግኝቶ ለማስቀመጥ በእንጦጦ ማርያም፣ በደርሄ (ሸዋ)
በጨጨሆ፣ በአንኮበር፣… ወዘተ ተራራማ ቦታዎች አስቀምጠውት ነበር፡፡ አንብር መስቀልየ ዲበ መስቀል የሚለው ትእዛዝ ግን
አላቋረጠም ነበር፡፡ ግማደ መስቀሉን በመናገሻ ከተማቸው ደብረ ብርሀን በስተምስራቅ ወደምትገኘው መስቀለኛ ቦታ አንሳስ ማርያም
መጋቢት ፲ ቀን ገብቶ ለአሥራ አምስት ዓመታት ያህል ተቀምጧል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መጋቢት ፲ ቀን በየዓመቱ በዓለ መስቀል
በደብረ ብርሀን ከተማ ይከበራል፡፡ በዓለ ደመራውም በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡ ይሁንና መሬት እየተንቀጠቀጠች አልረጋ
ስለአለችና አንብር መስቀልየ ዲበ መስቀል የሚለው የጌታ ትእዛዝ አላቋርጥ ስለአለ እግዚአብሐር የፈቀደውን መስቀኛ ቦታ ለማግኘት
ንጉሡ ሰባት ቀን ሱባኤ ገቡ፡፡ ግሼን አምባ በራዕይ ተገለጠችላቸው፡፡ ግማደ መስቀሉ ይዘው በኢትዮጵያ ያሉ ተራራዎችን አዳረሱ፡፡
በመጨረሻም በወሎ ክፍለ ሀገር በአምባሰል ተራራ በመስቀል ቅርፅ የተሠራች አንድ መግቢያ ብቻ ያላት ግሼን ደብረ ከርቤን አይተው
በራዕይ የተነገረኝ ተራራ ይህ ብለው ተራራውን ሰባት ጊዜ ከዞሩ በኋላ መስከረም ፳፩ ቀን ፲፬፻፵፮ ዓ/ም ወደ ተራራው ወጥተው ግማደ
መስቀሉን በእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖሩት፡፡ ይህም ቀን በግሼን ደብረ ከርቤ በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡
የመስቀሉ
በረከት ይደርብን፡፡
No comments:
Post a Comment