Monday, May 25, 2015

የመሥዋዕቱ በግ የት አለ ? ዘፍ. ፳፪፥፯

                                                                                                     በዲ/ን ዓለማየሁ ሀብቴ
              ክፍል ፩  
መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የኃጢአት ማስተሥርያ ነው፡፡ በዘመነ ብሉይ ሰው በአምላኩ ፊት ስለበደሉ መጸጸቱን (ንስሓ መግባቱን) ለማሳየት፣ ሞገስ ለማግኘት፣ እምነቱን ለመግለጽ፣ ምስጋና ለማቅረብ፣ ፍቅሩን ለማሳየት መሥዋዕት ያቀርብ (ይሰዋ) ነበር፡፡ በወቅቱም ለመሥዋዕት ከሚቀርቡት እንስሳት መካከል በግ ዋነኛው ነበር፡፡
አቤል በሕገ ልቡና ተመርቶ፤ በፍፁም እምነት፣ በንፁህ ሕሊና፣ በበጎ አእምሮ ለአምላኩ ለእግዚአብሔር ያቀረበው፤ አምላኩም ያሸተተለት ተወዳጅ መሥዋዕት ቀንዱ ያልከረከረ፣ ፀጉሩ ያላረረ፣ ጥፍሩ ያልዘረዘረ ፀዓዳ በግ ነው፡፡ ዘፍ. ፬-፭ አቤልም በግ ጠባቂ ነበረ (አርቢ)፤ ቃየንም ምድርን የሚያርስ (ገበሬ) ነበረ፡፡ ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፤ አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኩራትና ከስቡ አቀረበ፡፡ እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም፡፡
 በግ በብሉይ ኪዳን ዘመን ስለኃጢአት ስርየት ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ተወደጅ መሥዋዕት ነበር፡፡ ዘሌ. ፭፲፭-፲፮ ማናቸውም ሰው ቢበድል፥ ሳያውቅም ለእግዚአብሔር በተቀደሰው በማናቸውም ነገር ኃጢአትን ቢሠራ፥ ለበደል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ከመንጋ ነውር የሌለበትን አውራ በግ ያቀርባል እንደ ግምጋሜህ መጠን በብር ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ለበደል መሥዋዕት ያቀርበዋል። በተቀደሰ ነገር ላይ ስለ ሠራው ኃጢአት ዕዳ ይከፍላል፥ አምስተኛውንም እጅ ይጨምርበታል፥ ለካህኑም ይሰጠዋል። ካህኑም በበደል መሥዋዕት አውራ በግ ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል።
እግዚአብሔር በተዘረጋች እጅ፣ በበረታች ክንድ እስራኤልን ከአስከፊው የግብጽ ባርነት ነፃ ሲያወጣቸው ከሞተ በኩር የሚድኑበትን የበግ ጠቦት አርደው ደሙን በበራቸው መቃንና ጉበን ላይ በመርጨት ፋሲካ እንዲያደርጉ አዞአቸዋል፡፡ እነርሱም የፋሲካውን በግ አርደው ደሙን በሁለቱ መቃኖችና ጉበን ላይ ረጭተው ቤቶቻችንን ያዳነ የእግዚአብሔር የማለፉ መሥዋዕት ይህች ናት አሉ፡፡ ዘጸ. ፲፪፥፳፩-፳፯ ሙሴም የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጠርቶ አላቸው፡- በቤታችሁ ጠቦት ምረጡ፣ ወስዳችሁም ለፋሲካ እረዱት፡፡ ከሂሶጵ ቅጠልም ጭብጥ ውሰዱ፣ በዕቃ ውስጥ በለውም ደም ንከሩት፣ በዕቃውም ውስጥ ካለው ደም ሁለቱን መቃኖችና ጉበኑን እርጩ፤ ከእናንተም አንድ ሰው ከቤቱ ደጅ እስኪነጋ ድረስ አይውጣ፡፡ እግዚአብሔር ግብፃውያንን ይመታ ዘንድ ያልፋልና፤ ደሙንም በጉበኑና በሁለቱ መቃኖች ላይ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር በደጁ ላይ ያልፋል፣ አጥፊውም ይመታችሁ ዘንድ ወደ ቤታችሁ እንዲገባ አይተውም፡፡ ለእናንተ ለልጆቻችሁም ለዘለዓለም ሥርዓት አድርጋችሁ ይህችን ነገር ጠብቁ፡፡ እንዲህም ይሆናል እግዚአብሔር እንደተናገረ ወደሚሰጣችሁ አገር በገባችሁ ጊዜ ይህን አምልኮ ጠብቁት፡፡ እንዲህም ይሆናል፤ ልጆቻችሁ፡- ይህ አምልኮ ለእናንተ ምንድን ነው? ባሉአችሁ ጊዜ፥ እናንተ፣ በግብፅ አገር በእስራኤል ልጆች ቤቶች ላይ አልፎ ግብፃዊያንን በመታ ጊዜ፥ ቤቶቻችንን ያዳነ የእግዚአብሔር የማለፉ መሥዋዕት ይህች ናት ትሉአቸዋላችሁ።
የመሥዋዕቱ በግ የት አለ? ብሎ ለመጀመርያ ጊዜ ጥያቄ ያቀረበው የአብርሃም ልጅ ይስሐቅ ነው፡፡ ጥያቄውንም ያቀረበው ለእግዚአብሔር ሰው ለአባቱ ለአብርሃም ነው፡፡ ከስነ ፍጥረት መዝገብ መጽሓፍ ዘፍ. ፳፪፥ ፩-፲፬ እንደምናነበው አርከ እግዚአብሔር አብርሃም በስተእርጅና ያገኘውን ብርቅዬ አንድ ልጁን በሞርያ ተራራ ላይ ለእግዚአብሔር አምላኩ እንዲሠዋ ታዘዘ፡፡ አብርሃምም ውድ ልጁን ለመሠዋት ኣላቅማማም፡፡ የሰጠው እግዚአብሔር ነውና ልጁን ለመሥዋዕትነት የጠየቀው አብርሃም ሳይውል ሳያድር ማለዳ ተነስቶ ልጁን ለመሠዋት አህያውን ጭኖ፣ ሎሌዎቹን አስከትሎ፣ ልጁን ይስሐቅን፣ እሳት፣ የሚሠዋበትን እንጨትና ቢላዋ ይዞ ወደ ታዘዘው ተራራ ሄደ፡፡ በሦስተኛውም ቀን ሞርያ ተራራ ደረሰ፡፡ ሎሌዎቹንም እኔና ልጄ ወደ ተራራው ወጥተን ለእግዚአብሄር ሰግደን፣ መሥዋዕት ሠውተን እንመለሳለን፡፡ አናንተ አህያውን ይዛችሁ ከዚህ ከእግረ ደብር ቆዩን ብሎአቸው የሚሠዋበትን እንጨትት ልጁን ይስሐቅን አሸክሞ፤ እሳቱን ቢላውን ራሱ ይዞ ልጁን ሊሠዋ ወደ ተራራው ወጣ፡፡ ይስሐቅም አባቱን አብርሃምን፡- እንጨቱን፣ እሳቱን፣ ቢላውን ይዘናል፡፡ አይቴ ሀሎ በግዑ ለመሥዋዕት (የመሥዋዕቱ በግ የት አለ)? ብሎ ጠየቀው፡፡ አባቱ አብርሃምም፡- ልጄ የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል አለው፡፡ እግዚአብሔርም ወደለው ቦታ በደረሱ ጊዜ አብርሃም በዚያ መሠውያውን ሠራ፣ እንጨቱንም ረበረበ፣ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሠውያው በእንጨቱ ላይ አጋደመው፡፡ ይስሐቅም አባቴ አይኔ ብክን ብክን ሲል አይተህ፣ ለኔ ለልጅህ ራርተህ ሳትሠዋ ትተኸኝ ከፈጣሪህ ጋር እንዳትጣላ በልቤ ደፍተህ በማጅራቴ እረደኝ አለው፡፡ አባቱም አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በልቡ ደፋው፡፡ ዛሬ አባቶቻችን የይስሐቅን መሥዋዕትነት ለማስታወስ ደቦ ሲቆርሱ ዳቦውን ወደታች ደፍተው ይቆርሳሉ፡፡ አብርሃምም እጁን ዘረጋ፣ ልጁን ሊያርድ ቢላዋ አነሳ፡፡ እግዚአብሔርም መልአክ አብርሃምን ጠርቶ በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፣ አንዳችም አታድርግበት፤ አንድ ልጅህን አልከለከልከኝምና እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደሆንክ አሁን አውቃለሁ አለው፡፡ አብርሃምም ዞር ባለ ጊዜ አንድ ፀአዳ በግ በዱር ውስጥ ሁለት ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ፡፡ ይህን ሠዋ ሲለኝ ነው ብሌ ሄዶ በጉን ወሰደው፣ በልጁም ፈንታ መሥዋዕት አድርጎ ሠዋው፡፡ አብርሃምም ያንን ቦታ ያህዌ ይርኤ (እግዚአብሔር ያያል) ብሎ ጠራው፡፡
ይህ የሐዲስ ኪዳነ መሥዋዕት ምሳሌ ነው፡፡ ደብር (ተራራ) የቀራንዮ፣ አብርሃም የእግዚአብሔር አብ፣ ይስሐቅ የእግዚአብሔር ወልድ፣ እሳት የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፣ ቢላዋ የሥልጣነ እግዚአብሔር፣ እንጨት የመስቀል፣ ሁለቱ ሎሌዎች የሁለቱ ወንበዴዎች፣ አድግ (አህያ) የአድገ ሆሣዕና፣ ህሊና አብርሃም የመቃብር ምሳሌ ነው፡፡ አንድም በግ የጌታ፣ ይስሐቅ የምዕመናን፣ ዕፀ ሳቤቅ የመስቀል ምሳሌ፡፡ ዕፀ ሳቤቅ ብሂል ዕፀ ሥርየት እንዲል፡፡ ምሥጢሩ የጌታን ነገረ ሞት ለአብርሃም፤ የአብርሃምንም ዜና ኂሩት ለሰው ለመግለጽ ነው፡፡ 
የዛሬዎቹ ልጆች ለወላጆቻችንና ለእግዚአብሔር ፈቃድ ምን ያህል ታዛዦች ነን? ወይስ አዋቂዎች እኛ ብቻ ነን ብለን ለወላጆቻችን ሀሳብና ፈቃድ ቦታ አንሰጥም? ወላጆችስ  ከልጆቻችን፣ ከሀብታችን፣ ከለን ነገር ሁሉ፣ ከራሳችንም ጭምር እግዚአብሔርን አናስቀድማለን? ምድራዊውም ሆነ ሰማያዊው ሕይወታችን የሠመረ እንዲሆን፣ የቤተሰብ ፍቅር እንዲዳብር፣ ኑሮአችን ሰላማዊ እንዲሆን፤ ልጆች ለወላጆቻችን እንታዘዝ፣ ወለጆችም ልጆቻችንን ሳናስቆጣ በመልካም ሥነ ምግባር እናሳድጋቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ፈቃደ እግዚአብሔርን እናስቀድም፡፡
ከላይ ያየናቸው የዘመነ ብሉይ አበይት አባግዓ መሥዋዕት (የአቤል በግ፣ ቤዛ ይስሐቅ በግ፣ የእስራኤል የፋሲጋ በግ) ሁሉም አይቴ ሀሎ በግዑ ለመሥዋዕት (የመሥዋዕቱ በግ የት አለ)? ብሎ ይስሐቅ የጠየቀውን የሰው ልጅ የህልውና (የድኅነተ ዓለም) ጥያቄ ሊመልሱ አልቻሉም፡፡ ጊዜያዊ ድህነትን እንጂ ዘለዓለማዊ ድህነትን ለሰው ልጅ አላስገኙም፡፡ የተዘጋውን የገነት በር መክፈት፣ አዳምን ከወደቀበት ሞተ ነፍስ (የነፍስ ሞት) ማንሳት አልቻሉም፡፡ ሰዎች ለዘመናት የሠውት መሥዋዕት ሁሉ ድህነትን ሊያስገኝላቸው በለመቻሉና እውነተኛውን የመሥዋዕቱን በግ ስላላገኙ በቀቢፀ ተስፋ ወድቀው ጽድቃችን የመርገም ጨርቅ ሆነ እስከማለት ሁሉ ደርሰው ነበር፡፡ ኢሳ. ፷፬፥፭-፯ እነሆ አንተ ተቆጣህ እኛም ኃጢአት ሠራን ስለዚህም ተሳሳትን፡፡ ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፣ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፡፡ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፣ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል፡፡ ስምህንም የሚጠራ፣ አንተንም ሊይዝ የሚያስብ የለም፣ ፊትህን ከእኛ ሰውረሃል፣ በኃጢአታችንም አጥፍተኸናል፡፡ ይሁንና የዓለምን ኃጢአት አስወግዶ ሰውን ከወደቀበት አንስቶ ከአምላኩ የሚያስታርቅ የመሥዋዕቱ በግ የት አለ ብለው ከመጠየቅ አልቦዘኑም፡፡ ፍለጋውንም አላቋረጡም፡፡ የመሥዋዕቱ በግ የሰው ልጅ ህልውና መሠረት ነው፡፡ ፍለጋውም ዘመናትን የወሰደ፣ በጉጉት ሲጠበቅ የኖረ ነው፡፡ ጥያቄው የሰው ልጅ ታሪካዊ የሕይወት ጥያቄ ነው፡፡ የመሥዋዕቱ በግ የት አለ? የሚለው ታሪካዊ የሰው ልጅ የሕይወት ጥያቄ መልስ ያገኘው እግዚአብሔር አምላክ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ብሎ ለአዳም የገባለትን ቃል ኪዳን በፈጸመበት በዘመነ ሐዲስ ነው፡፡

ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment