Wednesday, May 18, 2016

፳፬ ሰዓት የቴሌቪዥን ስርጭት

የቤተ ክርስቲያናችን የ፳፬ ሰዓት የቴሌቪዥን አገልግሎት ከቀናት በኋላ የሙከራ ስርጭት ይጀምራል
 
በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በተወሰነው መሠረት፤ ቤተ ክርስቲያናችን፣ በሀገር ውስጥ እና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ምእመናን ድምፅዋን የምታሰማበት እና መረጃ የምትሰጥበት 24 ሰዓት የቴሌቪዥን አገልግሎት ከኹለት ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የሙከራ ስርጭቱን እንደሚጀመር ተገለጸ፡፡
የስርጭት አገልግሎቱን ለመስጠት ለወድድር ከቀረቡት ሦስት ኩባንያዎች መካከል በጠቅላይ /ቤቱ የብዙኃን መገናኛ ድርጅት ቦርድ ከተመረጠውና በእስራኤል ከሚገኘው የኮሚዩኒኬሽን ኩባንያ ጋር የሥርጭት ስምምነት ውሉ ፓትርያርኩ ኢየሩሳሌምን እየጎበኙ በነበሩበት በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ መፈጸሙም ታውቋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ለአገልግሎቱ 12 ሚሊዮን ብር የአንድ ዓመት በጀት ያጸደቀ ሲኾን፤ በዚኽ ሳምንት በተፈረመው የስምምነት ውል መሠረት ቤተ ክርስቲያናችን፣ 30,050 ዶላር(660 ሺሕ ብር በላይ) በየወሩ ለኩባንያው እንደምትከፍል ተጠቁሟል፡፡
የብዙኃን መገናኛ ድርጅቱን በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ በቦርዱ የተመደቡት እና ስምምነቱን ከኩባንያው ጋር የተፈራረሙት / ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ናቸው፡፡ በኹለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የሙከራ ስርጭቱን ይጀምራል የተባለው አገልግሎቱ፤ የድርጅቱን ሎጎ(መለዮ) ከማስተዋወቅ ባሻገር ቀደም ሲል ተቀርጸው ከቆዩ የምስል ወድምፅ ክምችቶች የተመረጡ ትዕይንቶች፣ ትምህርቶችና መዝሙራት እየቀርቡበት የሚቆይ ሲኾን፤ መደበኛ ዝግጅቱ ከሦስት ወራት በኋላ መተላለፍ ይቀጥላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል፡፡
ቀረፃውንና ዝግጅቱን በሀገር ውስጥ በማከናወን መካከለኛው ምሥራቅን፣ ደቡብ አውሮፓን፣ ሰሜንና ምሥራቅ አፍሪቃን የሚያካልለው የሳተላይት ሥርጭቱ፥ ለተቀረው ዓለም ዝግጅቱን በኢንተርኔት በመጫን እንደሚያስተላልፍ ተጠቅሷል፡፡
በመንበረ ፓትርያርኩ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ሕንፃ በተሰጡት ስምንት ቢሮዎች ውስጥ ሥራውን በማከናወን ላይ የሚገኘው አገልግሎቱ፤ በቀጣይ፣ የአኹኑን የኦዲዮ ስቱዲዮ በዘመናዊ መልክ የማደራጀት ዕቅድም ይዟል፡፡
ዘጠኝ አባላት ያሉትና በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ እና የምሥራቅ ጎጃም ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የሚመራው ቦርዱ፤ ተጠሪነቱ ለሥራ አስኪያጁ የኾነ ኤዲቶሪያል ቦርድ እና ሰባት አባላት ያሉት የዝግጅት ኮሚቴ ሠይሟል፤ በቅርቡም፣ ከፍተኛ የሥርጭት ቴክኒክ ክህሎትና ልምድ ያለው የምክትል ዋና ዳይሬክተር እንዲኹም 22 ሠራተኞች ቅጥር ለማካሔድ የሚያስችል መስፈርት አውጥቶ ማጠናቀቁም ተገልጧል፡፡
 
ዋና ዳይሬክተሩ / ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል
በመጀመሪያው ዙር 10 ሰዎች በላይ ተወዳድረውበታል በተባለው የዋና ዳይሬክተሩ ቦታ፣ በቦርዱ መመዘኛ መሠረት ለመጨረሻው ዙር ካለፉት አምስት ሰዎች አንዱ የኾኑትና በመጨረሻው ፈተና ቅድሚያውን ይዘው የተመረጡት / ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል፤ በመጀመሪያ ዲግሪ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በሥነ መለኰት፤ በኹለተኛ ዲግሪ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሩቅ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል በመንበረ ፓትርያርክ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር እና ቅርስ መምሪያ እንዲኹም በውጭ ጉዳይ መምሪያ በሓላፊነት ሠርተዋል፡

No comments:

Post a Comment