በስመ አብ ወወልድ ወመንፈሰ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
ሰኔ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፭ ቍጥር ፻፷፬ በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው የዘንድሮዉን መደበኛ የርክበ ካህናት ስብሰባ የጉባኤው መክፈቻ ሥርዓተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከበዓሉ ዋዜማ ከግንቦት ፲፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሰኔ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ድረ ለዐሥራ ስድስት ቀናት ያህል ባደረገው ጉባኤ ጠቀሜታ ባላቸው የአጀንዳ ነጥቦች ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
ከእነዚህ መካከል የሚከተሉት በዋናነት ይጠቀሳሉ፤
፩. የ፳፻፰ ዓ.ም የርክበ ካህናት ጉባኤን በተመለከተ ቅዱስ ፓትርያርኩ ያደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንዳበቃ ጉባኤው ሥራውን ቀጥሏል፡፡
፪. የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ዓመታዊ ሪፖርት በጽሑፍ ቀርቦ ጉባኤው ካዳመጠ በኋላ በሪፖርቱ ላይ ውይይት በማድረግ ለወደፊቱ የሚወሰኑት ኹሉ የአፈጻጸም ችግር እንዳይደርስባቸው ክትትል ይደረግ ዘንድ ተወስኗል፡፡
፫. እስከ አሁን እየተሠራበት ያለው ቃለ ዓዋዲ የቤተ ክርስቲያናችን መተዳደሪያ ደንብ ወቅቱን ባገናዘበ መልኩ እንዲሻሻል በተሰጠው መመሪያ መሠረት የተዘጋጀው ረቂቅ ቀርቦ ምልዓተ ጉባኤው ከተነጋገረበትና ከታየ በኋላ የረቂቁ ዝግጅት በቋሚ ሲኖዶስ ታይቶ እንዲታተም ተወስኗል፡፡
፬. ስለ ቅዱስ ፓትርያርክ እንደራሴ አስፈላጊነት ጉዳይ ቅዱስ ሲኖዶስ ከተነጋገረ በኋላ የእንደራሴ አስፈላጊነት በምን ዓይነት ሕግ ላይ ተመሥርቶ መመረጥ አለበት የሚለዉን በማጥናት ለጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የሚያቀርቡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ጨምሮ ሰባት አባላት እንዲመረጡ ተደርጓል፡፡
፭. ተፈጥሮ ባስከተለው ድርቅ ምክንያት በየመጠለያው ለሚገኙ ወገኖች የዕለት ደራሽ ርዳታ፣ ለተፈናቀሉ ወገኖችም ለመልሶ ማቋቋሚያ አገልግሎት የሚውል የገንዘብና የቁሳቁስ ርዳታ ይደረግ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ጥሪዋን ታስተላልፋለች፤ የድርሻዋንም አስተዋፅኦ አድርጋለች፡፡
፮. በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት የሚያገለግል ሕንፃ መገንባት ይቻል ዘንድ ቦታ እንዲሰጥ ከገዳሙ ማኅበረ መነኰሳት የቀረበውን ጥያቄ ምልዓተ ጉባኤው የተቀበለው ስለኾነ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ማእከላዊ አስተዳደር በኩል ቦታ ተፈልጎ እንዲሰጥ ተዋስኗል፡፡
፯. ቅዱስ ሲኖዶስ በየአህጉረ ስብከቱ ክፍት በኾኑ መንበረ ጵጵስናዎች ብቁ የኾኑ ኤጲስ ቆጶሳትን መርጦ ለመሾም ባለው ዕቀድ መሠረት፣
ፈተናዉንና መሰናክሉን ኹሉ አልፈው ዕውቅና ያገኙትን፤
በብሔር ዓቀፍና በዓለም ዓቀፍ ትምህርት የበሰሉትን፤
የወቀውቱንም ችግር ይፈታሉ ተብለው እምነት የተጣለባቸውንና የሚጣልባቸውን፤
ለተልእኮ የሚፋጠኑትን መነኰሳት በመመርመር፣ በማጥናትና በማጣራት ውጤቱን እስከ ሰኔ ፴ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ድረስ የሚያቀርብ አስመራጭ ኰሚቴ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡
፰. ሀ. ብፁዕ አባ ያሬድ ሊቀ ጳጳስ የኢትዮጵያ ሱማሌ ሀገረ ስብከት ሥራን እንደያዙ በአርሲ ሀገረ ስብከት፤
ለ.ብፁዕ አባ እንጦንስ ሊቀ ጳጳስ በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከ፤
ሐ.ብፁዕ አባ ያዕቆብ ሊቀ ጳጳስ በደቡብና ምዕራብ አፍሪካ አህጉረ ስብከት፤
መ.ብፁዕ አባ እንድርያስ ሊቀ ጳጳስ የሊቃውንት ጉባኤ የበላይ ሓላፊነቱን ሥራ እንደያዙ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ሓላፊ በመኾን ተመድበው እንዲሠሩ ምልዓተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
፱. በውጭ ላሉት አህጉረ ስብከት ጥናት ተደርጎ በቋሚነት የሚሠሩ አባቶች እስኪመደቡ ድረስ፣
ሀ/ ሰሜን፣ ሰሜን ምሥራቅና ሰሜን ምዕራብ አውሮፓ አህጉረ ስብከት፣
ለጊዜው በብፁዕ አባ ሙሴ የደቡብ ምዕራብና የደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ፤
ለ/ አውስትራልያ ሀገረ ስብከት፣
በብፁዕ አባ ሔኖክ የምዕራብ ወለጋና የአሶሳ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ፤
ሐ/ ምሥራቅ አፍሪካ፣ ኬንያና ጅቡቲ አህጉረ ስብከት፣
በብፁዕ አባ ዳንኤል የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ፤
መ/ ምሥራቅ አፍሪካ፣ ሰሜን ሱዳንና ግብፅ አህጉረ ስብከት፣
በብፁዕ አባ ሉቃስ በክልል ትግራይ ዞን ወልቃይት ጸገዴ ሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ ኾኖ፣
በተጨማሪም የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የበላይ ሓላፊ ኾነው እንዲሠሩ፤
ሠ/ ደቡብ ሱዳን ሀገረ ስብከት፤
በብፁዕ አባ እስጢፋኖስ የጅማ፣ የኢሉባቡርና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ ሲል ምልዓተ ጉባኤው በአንድ ድምፅ ተስማምቶ ወስኗል፡፡
፲. በውጭ አህጉረ ስብከት ካሉት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ያለው የሰላሙ ንግግር ይቀጥል ዘንድ ሰላም ለማንኛውም መሠረት መኾኑ ታምኖበት ይህንኑ ሰላም ለማምጣት አስፈላጊው ጥረት ኹሉ እንዲደረግ፡፡
፲፩. ስለ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ረዳት ሊቀ ጳጳስ ምደባ ጉዳይ ቅዱስ ሲኖዶስ ከተወያየ በኋላ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ ፶ መሠረት ብፁዕ አባ ሕዝቅኤል በያዙት ሀገረ ስብከት ሥራቸው ላይ ደርበው እስከ ጥቅምት ወር ፳፻፱ ዓ.ም ድረስ የፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ኾነው እንዲሠሩ ተስማምቷል፡፡
፲፪. በየሦስት ዓመቱ የሚደረገው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ እኪኪያጅና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ምርጫ ካሉት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል በማወዳደር፡-
ሀ. ብፁዕ አባ ዲዮስቆሮስ ሊቀ ጳጳስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣
ለ. ብፁዕ አባ ሳዊሮስ ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ኾነው ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት እንዲሠሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ተመርጠዋል፡፡
፲፫. በሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት ሓላፊነት በቤተ ክርስቲያናችን እየተረዱ የሚያድጉ እጓለ ማውታ ሕፃናት በየአህጉረ ስብከቱ መኖራቸው የሚታወቅ ነው፤ ይኸው የሕፃናትና የቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት እጓለ ማውታ ሕፃናትን በማሳደግና በማስተማር ረገድ ለሀገራችንና ለቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ አለኝታ ስለኾነ፣ አስከ አሁን ከነበረው ይዘት በበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቅዱስ ሲኖዶስ ተወስኗል፡፡
፲፬. የቤተ ክርስቲያናችን እምነትና ሥርዓተ አምልኮ እስከ አሁን ድረስ ተከብሮና ተጠብቆ እንደ ኖረ ኹሉ አሁንም ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያለው የመንፈሳዊና የማኅበራዊ አገልግሎት መዋቅር በበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ መመሪያ ተሰጥቷል፡፡
፲፭. በቤተ ክርስቲያኒቱ ማእከላዊ አሰዝተዳደር ቀልጣፋና ቅንነት የሰፈነበት አሠራር እንዲኖር፣ በየደረጃው የተዘረጉትም የልማት አውታሮች የበለጠ ውጤት እንዲኖራቸው ለማስቻል፣ ከመንበረ ፓትርያርክ ሥራ አስኪያጅ ጀምሮ ኹሎችም የየአህጉረ ስብከቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሓላፊነት ያለባቸው ስለኾነ ተከታትለው እየሠሩ እንዲያሠሩ ተወስኗል፡፡
፲፮. በመከናወን ላይ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አጀማመር ኹሉም ኅብረተሰብ እጁን ሲዘረጋ እንደቆየ ኹሉ፣ አሁንም ለፕሮጀክቱ አፈጻጸም መላው ኀብረተሰብ የበኩሉን ድርሻ ይፈጽም ዘንድ ቀዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡
፲፯. ከሀገራችን ኢትዮጵያ ውጭ ባሉት አንዳንድ አህጉር እየደረሰ ያለውን የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግር በጆራችን እንሰማለን፤ በዓይናችንም እናያለን፡፡ ለማስረጃም ያህል፡-
በመሬት መንቀጠቀጥ፣ በጎርፍ መጥለቅለቅና በሰደድ እሳት ዘግናኝ አደጋ የሚደርስ ኅልፈተ ሕይወት፤
በእርስበርስ የውስጥ ጦርነት የደረሰውና እየደረሰ ያለው ዕልቂት፤
የእግዚአብሔርን ህልውና በሚፈታተኑ አንዳንድ ግለሰቦች ግንዛቤ ጉድለት እየደረሰ ያለው የጦርነት አደጋ፤
በየብስ፣ በውቅያኖሶችና በሰማይ ላይ በሚበሩ አውሮፕላኖች የሚደርሰው ዘግናኝ ዕልቂትና የመሳሰሉት ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው፡፡
ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካችን ጉዳት ለደረሰባቸው መጽናናትን፣ መረጋጋትን እንዲሰጥልን፤ ቅን ልቡና፣ ትሑት ሰብእና
ለሚጎድልባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችም ትዕግሥቱን፣ ርኅራኄውን እንዲያበዛልን እንጸልያለን፡፡
በመጨረሻም በሀገራችን ጎልቶ የሚታየው ድህነት እንዲወገድ፤ የተራበው፣ የተጠማው፣ የታረዘው መሠረታዊ ፍላጎቱ ተሟልቶለት እንዲኖር፤ በሀገራችን ኢተዮጵያ፣ በዓለሙም ኹሉ ሰላም እንዲሰፍን ቅዱስ ሲኖዶስ በመጸለይ ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፤ ይቀድስ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤
አሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ሰኔ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም፡፡
ወደፊት > |
---|
No comments:
Post a Comment