በዲ/ን ዓለማየሁ ሀብቴ
ክፍል ፪
በሓዲስ ኪዳን የዓለምን ኃጢአት
አስወግዶ ሰውን ከአምላኩ ያስታረቀው የተወደደው የመስዋዕቱ በግ ነው፡፡ ይህ የመሥዋዕቱ በግ ለዘመናት ሲጠየቅ የኖረው የእግዚአብሔር
በግ ነው፡፡ የመሥዋዕቱ በግ የት አለ? ብሎ ይስሐቅ ለጠየቀው ጥያቄ ትክክለኛው መልስ የተገኘው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
በአጭር ቁመት፣ በጠባብ ደረት ተወስኖ፣ በኩነተ ሰብእ፣ በለቢሰ ሥጋ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ ነው፡፡
የመሥዋዕቱም በግ መገኘቱን ለይስሐቅ (ለዓለም) የነገሩት መጋቤ ሓዲስ፣ አብሳሬ ትስብእት፣ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤልና መጥምቀ
መለኮት ቅዱስ ዮሓንስ ናቸው፡፡
ቅዱስ ገብርኤል የመሥዋዕቱ በግ መገኘቱን ለዓለም ያበሰረው ጽድቃችን የመርገም ጨርቅ ሆኗል ብለው
በቀቢጸ ተስፋ ለወደቁት የምሥራች በማሰማት ነው፡፡ ሉቃ. ፪፥፲-፲፩ መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ
ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። አጥማቄ መለኮት ቅዱስ ዮሓንስ
ደግሞ የመሥዋዕቱ በግ የት አለ? የሚለውን ይስሐቅ ጥያቄ በቀጥታ መልሷል፡፡ ዮሐ. ፩፥ ፳፱ በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ
ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፡- ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘየዓትት ኃጢአተ ዓለም (የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ እንሆ)፡፡ የዓለምን ኃጢአት ሊያስወግድ የሚችለው ሰዎች የሚሠውት ተፈጥሮአዊ በግ ሳይሆን የእግዚአብሔር
በግ ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሔር በግ ደሙ የዓለምን ኃጢአት የሚያጥብ፣ የተዘጋውን የገነት በር የሚከፍት፣ የአዳምን በደል የሚደመስስ፣
ለዘመናት በሰው ላይ ሰፍኖ የነበረውን የሴይጣንን ግዛት የሚያፈርስ እውነተኛ መድኃኒት ነው፡፡ የእግዚአብሔር በግ እግዚአብሔር ዓለሙን
የወደደበትና ለሰው ያለውን አምላካዊ ፍቅሩን የገለጠበት፣ ችርነቱን፣ መግቦቱን፣ ርህራሄውን ያሳየበት ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍቅር
ነውና፡፡ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤ የመሥዋዕቱ በግ ልዑለ ባሕርይ የእግዚአብሔር አንድያ ልጁ ነው፡፡ ዮሐ.
፫፥፲፮ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የእግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን
እንዲሁ ወዶአልና፡፡ ሊቁ አባ ሕርያቆስም ይህን እግዚአብሔር ለሰው ያለውን ፍቅር በማድነቅ ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ
ወአብጽሆ እስከ ለሞት (ኃያሉ እግዚአብሔር ወልድን የሰው ፍቅር ከልኡል መንበሩ ሳበው ለሞትም አደረሰው) ብሏል(ቅዳሴ ማርያም)፡፡
ይህ የመሥዋዕቱ በግ፤ የዓለምን
ኃጢአት የሚያስወግደው የእግዚአብሔር በግ ለዓለም ድህነት የተሠዋው አፅመ አዳም ባለበት በማዕከለ ምድር በቀራኒዮ አደባባይ ነው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ ራሱን በመስቀል ላይ ሠውቶልናል፡፡ ሕመማችንን ታመመ፣ አበሳ በደላችንን ተሸከመ፣
መከራችንን ተቀበለ፣ ተናቀ፣ ተተፋበት፣ ስለእኛ ቆሰለ፣ ሞታችንን በመስቀል ላይ ሞቶ ሕይወቱን ሰጠን፡፡ ኢሳ. ፶፫፥፩-፱ የሰማነውን
ነገር ማን አምኖአል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጧል? በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል፡ መልክና
ውበት የለውም፣ ባየነውም ጊዜ እንወደው ዘንድ ደም ግባት የለውም፡፡ የተናቀ ከሰውም የተጠላ፣ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፡
ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፣ እኛም አላከበርነውም፡፡ በአውነት ደዌአችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሟልና እኛ ግን
እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሰፈ እንደ ተቸገረም ቆጠርነው፡፡ እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቆሰለ፣ ስለበደላችንም ደቀቀ
የደህንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፣ በእርሱም ቁስል እና ተፈወስን፡፡ እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን ከእኛ
እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ፡፡ ተጨነቀ ተሰቃየም አፉንም አልከፈተም
ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፣ በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡ በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ ስለ ሕዝቤ
ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስታዋለ? ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፣ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ
ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፣ በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም ነበር፡፡
ስለእኛ መከራ መስቀልን ተቀበለ፡፡
የሾህ አክሊል ደፍቶ ተንገላታ፣ አጥንቱ አስኪታይ ተገረፈ፣ ታመመ፣ ሞተ፡፡ በድካሙ አበረታን፣ በሕማሙ ፈወሰን፣ በሞቱ አዳነን፡፡
ወበሕማማቲሁ ቤዘወነ እንዲል ግብረ ሕማማት፡፡
ይህ የመሥዋዕቱ በግ፤ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደው የእግዚአብሔር በግ ለመሥዋዕትነት መሠውያው
መስቀል ላይ ሆኖ ክፉዎች አይሁድ መከራ ሲያበዙበት፣ ሲገርፉት፣ የሾህ አክሊል በራሱ ላይ ደፍተው ሲዘባበቱበት፣ በችንካር ሕማሙን
ሲያበዙበት አልተቆጣም፡፡ ክፉም ቃልም አልተናገራቸው፡፡ በፈቃዱ መከራን በሥጋው የተቀበለ፤ መከራን ሁሉ የታገሠ እርሱ
ነው፤ እንደ
በግ ሊሠዋ
መጣ፤ በግ
በሚሸልተው ሰው
ፊት እንዳይናገር አልተናገረም፤
በነገሩም ሐሰት
አልተገኘበትም እንዲል
ሀይማኖተ አበው ዘጎርጎርዎስ፡፡
ይልቁንም የፍርሃት የትዕቢት አይደለ ለሰው መድኃኒት አብነት የሚሆኑ ሰብአቱ አጽርሓ
መስቀል (ሰባቱ የመስቀል ላይ ጩኸት) የተባሉትን ብቻ አሰምቶ ተናግሯል፡፡ ቃላተ ርኅራኄ ሰበአተ እንተ ዲበ መስቀል ነበበ እንዲል፡፡
እነዚህ ጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ የተናገራቸው ሰባቱ ቃለተ ርኅራኄ የሚከተሉት ናቸው፡፡
፩. ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ
(አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ) ማቴ. ፳፯፥፵፮፡- ስለ አዳም ተገብቶ ሲጸል፡፡
፪. አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና
ይቅር በላቸው፡፡ ሉቃ. ፳፫፥፴፬፡- ከባቴ አበሳ ነውና ይቅርታን ሲያስተምረን፡፡
፫. እውነት እልሃለሁ፣ ዛሬ ከእኔ
ጋር በገነት ትሆናለህ፡፡ ሉቃ. ፳፫፥፵፫፡- በመከራ ብንመስለው እንደሚታደገን ሲያጠይቅ፡፡
፬. አባት ሆይ ነፍሴ በእጅህ አደራ
እሰጣለሁ፡፡ ሉቃ. ፳፫፥፵፮፡- የነፍሳችን ጌታ እግዚአብሔር መሆኑን ሲያሰተምረን፡፡
፭. አንቺ ሴት እነሆ ልጅሽ… እነኋት
እናትህ፡፡ ዮሐ. ፲፱፥፳፮፤ ለድንግል እናቱ ልጆቿ እንድንሆን አደራ ሲሰጣት፡፡
፮. ተጠማሁ፡፡ ዮሐ. ፲፱፥፳፱፤
የአደምን የ፶፭፻ ዘመናት በሲኦል መጠማት እንደ ተጠማለትና በደሙ እንደረከው ለመግለጽ፡፡
፯. ተፈጸመ፡፡ ዮሐ. ፲፱፥፴፤
ኪዳነ አዳም ፣ ድህነተ ዓለም መፈጸሙን፣ ካሳ መከፈሉን ሲያጠይቅ ነው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ለቤዛ ዓለም በመሥዋዕትነት በቀረበ ጊዜ አዲስ የመሥዋዕት ሥርዓት ሠርቷል፡፡ በሐዲስ ኪዳን ዘለዓለማዊ የሆነ አዲስ የክህነት አገልግሎት
ፈጽሟል፡፡ በዘመነ ብሉይ የነበረ ፍጹም ድህነት የማይሰጠውን አሮጌ
የክህነት ሥርዓት ሽሮ በአዲስ ሥርዓት፣ በአዲስ አገልግሎት፣ በአዲስ ክህነት፣ በአዲስ መሥዋዕት፣ በአዲስ ሊቀ ካህናትነት ፈጽሞታል፡፡
የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት ፍጹም ባልሆነ የክህነት አገልግሎት ስለራሱና ስለሕዝቡ ኃጢአት ሥርየት የደም መሥዋዕት ይዞ በዓመት አንድ
ጊዜ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባ ነበር፡፡ የሐዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ንጹሓ ባሕርይ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለሙ ሁሉ ድህነት በፍጹም
የክህነት አገልግሎት ዘለዓለማዊ የድህነት መሥዋዕት አንድ ጊዜ ፈጽሟል፡፡ ዕብ. ፱፥፲፩-፲፬ ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው
መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፣ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፣ የዘለዓለምን
ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም፡፡ የኮርማዎችና የፍየሎች
ደም በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ ሥጋን ለማንጻት የሚቀድሱ ከሆኑ፣ ነውር የሌለው ሆኖ በዘለዓለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሄር
ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን?
በሐዲስ ኪዳን የክህነት አገልግሎት መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ አዳም ራሱን መሥዋዕት
አድርጎ በመስቀል ላይ ሲያቀርብ እራሱ መስዋዕት ሆኖ፣ እርሱ እራሱ መሥዋዕት አቅረቢ ሊቀ ካህን፣ መሥዋዕት ተቀባይ አምላክም እራሱ
ነበር፡፡ የሚሠዋ በግ
እርሱ ነው፤
የሚሠዋ ካህን
እርሱ ነው፤
ከባሕርይ አባቱ
ከአብ፤ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ
ጋርም መሥዋዕት የሚቀበል እርሱ ነው እንዲል ሀይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ፡፡ ፪ቆሮ. ፭፥፲፱ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ
ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ፡፡
በዚህ በሓዲስ ኪዳን የክህነት አገልግሎት
ሥርዓት የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤ የመሥዋዕቱ በግ በመስቀል ላይ በተሠዋ ጊዜ ሰባት ተኣምራት ተፈጽመዋል፡፡
ማቴ. ፳፯፥፵፭-፶፬:: በሰማይ ሶስት በምድር አራት ተአምራት
ተፈጽመዋል፡፡ ይኸውም፡-
፩. ፀሐይ ጨለመች (ከስድስት እስከ
ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ላይ ጨለማ ሆነ)፣
፪. ጨረቃ ደም ሆነች፤
፫. ከዋክብት ረገፉ፣
፬. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ለሁለት
ተቀደደ፣
፭. ምድር ተናወጠች፣ ዓለቶች ተሰነጠቁ፣
፮. መቃብራት ተከፈቱ፣
፯. ሙታን ተነሱ፡፡
የመሥዋዕቱ በግ በተሠዋ ጊዜ ተጣልተው
የነበሩ ሰባቱ መስተጻርራን ታርቀዋል፤ ተስማምተዋል፡፡ ሰው ሕገ እግዚአብሔርን ጥሶ ከፈጣሪው በመጣላቱ ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና
መላእክት፣ ሥጋና ነፍስ፣ ሰማይና ምድር ተጣልተው ነበር፡፡ ሰው ከአምላኩ ከተጣላ፣ ከፈጣሪው ከተለየ ፍጡራና ሁሉ ይጣሉታል፡፡ እነዚህ
ሰባቱ ማስተጻርራን የታረቁት ሰው ከፍጣሪው በታረቀ ጊዜ ነው፡፡ ሰው ከአምላኩ የታረቀው በመሥዋዕቱ በግ፤ በእግዚአብሔር በግ ነው፡፡
እግዚአብሔር ቀድሞ ለአዳም በገባለት ቃል ኪዳን (ኪደነ አዳም) መሠረት በመሥዋዕቱ በግ፣ በልጁ ደም ጠላቱ የነበረውን በደለኛውን
ሰው ታረቀው፡፡ ሮሜ. ፭፥፲ ጠላቶቹ ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቀን፣ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፡፡
በዚህ በመሥዋዕቱ በግ ጠላትነት ጠፋ፣ በሰማይና በምድር ዕርቅ፣ ሰላም ሆነ፡፡ ቆላ. ፩፥፲፱-፳ እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ
እንዲኖር፥ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና። እግዚአብሔር
አምላክ ለገዛ ልጁ ሳይራራ መሕያዊት ለምትሆን ሞት በመስቀል ላይ አሳልፎ የሰጠው፣ አጽመ አዳም ባለበት በቀራንዮ ተራራ ላይ የሠዋው፤
የሴይጣንን ግዛት አፍርሶ፣ በአዋጅ የተነገሩትን የሞት ትዕዛዛት ሽሮ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን የጥል ግድግዳ ለማስወገድ
ነው፡፡ ኤፌ. ፪፥፲፮ ጥልንም
በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።
እግዚአብሔር ወልድ ጠላቶቹ ሳለን በሞቱ ታረቀን፣ ደሙን አፍስሶ ሥጋውን ቆርሶ ከዘለዓለም
ሞት ዋጀን፣ በሞቱ ሞታችንን አጥፍቶ ሕይወትን ሰጠን፣ እርሱ ተዋርዶ እኛን አከበረን፣ ስለእኛ ሞቶ እኛን አዳነን፡፡ በጸሎተ ሃይማኖታችን
ኮነ ብእሴ በእንቲኣነ፣ ሓመ፣ ወሞተ፣ ወተቀብረ፣ ወተንሥአ እሙታን ብለን ቤዛነቱን እንመሰክራለን፡፡ የመሥዋዕቱን በግ፤ የዓለምን
ኃጢአት የሚያስወግደውን የእግዚአብሔር በግ ሥጋውን በልተን ደሙን ጠጥተን ዘለዓለማዊ ሕይወት እናገኛለን፡፡ ሥጋው ዘለዓለማዊ የሕይወት
ምግብ ደሙም ዘለዓለማዊ የሕይወት መጠጥ ነው፡፡ በዘመነ ብሉይ እስራኤላውያን በምድረ በዳ መና በልተው ሞቱ፡፡ ከሰማይ የወረደው
መና ከሞት ታድጎ ዘለዓለማዊ ሕይወት አልሰጣቸውም፡፡ እኛ በምሥጢራዊና መንፈሳዊ ልደት ከክርስቶስ የተወለድን የክርስቶስ ወገኖች፣
የመንግሥቱ ዜጎች የሆንን ክርስቲያኖች (እስራኤል ዘነፍስ) በመስቀል ላይ የተሠዋውን የመሥዋዕቱን የእግዚአብሔር በግ በልተን ዘለዓለማዊ
ሕይወት አግኝተናል፡፡ ከመስቀሉ ወደ
ሲኦል በመውረዱ አዳነን፤ በአባታቸው በአዳም በደል በሲኦል ተግዘው የነበሩ ጻድቃንን ፈታ
ከሙታን ተለይቶ አስቀድሞ በተነሣ በእውነተኛ ትንሣኤውም አስነሣን፤ የንስሐንም በር ከፈተልን፡፡ በአባታችን በአዳም በደል የተዘጋ የገነት ደጅን
የከፈተልን፤ ዕፀ
ሕይወትን የሚጠብቅ ኪሩብንም ያስወገደ፤ የእሳት ጦርን ከእጁ ያራቀ፤ ወደ ዕፀ ሕይወት ያደረሰን እርሱ ነው፤ ፍሬውንም (ሥጋውን ደሙን)
ተቀበልን ሀይማኖተ
እንዲል አበው ዘጎርጎርዎስ፡፡
ያለመሥዋዕቱ በግ ሥጋና ደም ሕይወት
የለም፡፡ ዮሐ. ፮፥፶፩-፶፯ ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጄራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጄራ ቢበላ ለዘለዓለም ይኖራል፤ እኔም ስለ
ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጄራ ሥጋዬ ነው፡፡ እንግዲህ አይሁድ፡ ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይችላል? ብለው
እርስ በርሳቸው ተከራከሩ፡፡ ሊያውስ ቢሆን ለአእላፍ እስራኤል ስንት ስንት ጉርሻ ሊደርሰን ነው? ደግሞም የሰው ሥጋ ቢበሉት ደሙ ቢጠጡት ደዌ ይሆናል ብለው አጥብቀው ተቃወሙት፡፡
ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፡- እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት
የላችሁም፡፡ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፣ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ፡፡ ሥጋዬ እውነተኛ መብል
ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና፡፡ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ፡፡ ሕያው አብ እንደላከኝ
እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፣ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል፡፡
የመሥዋዕቱን በግ ሥጋ በልተን ደሙን
ጠጥተን ከደዌ ሥጋ ደዌ ነፍስ እንድናለን፡፡ በደሙ ፈሳሽነት ኃጢአታችንን ባጠበው የእግዚአብሔር በግ እዳ በደላችን ተደምስሶ የቅድስና
ማዕረግ አግኝተናል፡፡ ሥጋ ወደሙ ደምሳሴ አበሳ፣ መሥተሥርየ ኃጢአት ወሀቤ ሕይወት ነው፡፡
No comments:
Post a Comment