Friday, December 25, 2015

በእስራኤላውያን የነፃነት ትግል የመቃቢያን ሚና

ጤና ይስጥልኝ የማኅቶት ታዳሚያን እንደምን ዋላችሁ!
ዛሬ እንድ ወዳጄ መቃቢስ ማነው ልጆችስ አሉት ወይ ከሉትስ እነማን ይባላሉ መቃቢያን በእስራኤል የነፃነት ትግል ታሪክ ውስጥ ያለቸውስ ቦታ ምንድን ነው ብለው ለጠየቁኝ ጥያቄ አጭር ማብራርያ እነሆ ብያለሁ፡፡ መልካም ንባብ፡፡
በእስራኤላውያን የነፃነት ትግል የመቃቢያን ሚና
እስራኤል በውጭ ገዢዎች ስልጣን ስር በመውደቅ ረጅም ታሪክ አለት፡፡ መቃቢያንም በዚህ የታሪክ ጉዞ ውስጥ ጉልህ ሚና ነበራቸው፡፡
ክክርስቶስ ልደት በፊት (፩፻፸፭ - ፩፻፶፯) ሶርያውያን በጨካኙ ገዥ አንጢያኮስ ኤጲፋኒስ መሪነት ኢየሩሳሌምን ወረሩ፡፡ አንጢያኮስ እንደ ስልት የተጠቀመው የኤሁድን ሀይማኖትና ባህል አጥፍቶ በግሪክ ባህልና ሀይማኖት መተካት ነበር፡፡ በዚህ ሴይጣናዊ ዘዴው አይሁድ አመጹበት፡፡ የነፃነት ታጋዮች ተደራጅተው በማታትዩ መሪነት ከይሁዳ ተራራዎች የደፈጣ ውጊያ ከፈቱበት፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ፩፻፷፭ ዓመት ማታትዩ ሶርያውያንን ድል አድርጎ ቤተ መቅደሱን እንደገና ሠራው፡፡ ማታትዩ ከሞተ በኋላ ሁለቱ ልጆቹ መቃቢስ የተባለው ይሁዳና ስምኦን ያበታቸውን መሪነት ተረክበው ራሳቸውን መቃቢያን ብለው ሰየሙ፡፡ ይህ ጊዜ ፋርሳውያንና ሳዱቃውያን ያቆጠቁጡበት ነበር፡፡ ፋርሳውያን የመቃብያን ተቃዋሚዎች ሲሆኑ ሳዱቃውያን ግን መቃብያንን ይደግፉአቸው ነበር፡፡ ለዚህ ድጋፋቸው ሳዱቃውያን የሊቃነ ካህናት ስልጣንና ማዕረግ ተሰጣቸው፡፡ በወቅቱ ሶርያ ውስጥ የነበሩት ሮማውያን ጣልቃ እንዲገቡ ተጋብዘው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ፷፭ ዓመት የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ወደ አለችሁ ፍልስጥኤም ሰተት ብለው ገቡ፡፡
የመቃብያን አብዮት ለእስራኤላውያን ያስገኘው ውጤት ፡-
፩. የአጭር ጊዜ ፖለቲካዊ ነፃነት
፪. ፖለቲካዊና ምጣኔ ህብታዊ ዕድገት
፫. በሕዝቡ ዘንድ ሀገርን የማሰደግ ስሜት መነሣሣት
፬. የኢየሩሳሌም ከተማ ደህንነት መጠበቅ
፭. የፓጋኖችን ድንገተኛ ሀይማኖታዊ ጥቃት በመቋቋም የአባቶቻቸውን ሀይማኖት ማቆየት መቻል
፮. ጠፍቶ የነበረው ሥርዓተ አምልኮና መሥዋዕት ማንሰራራት
፯. ቀልብ የሚስቡ ሀይማኖታዊ ቡድኖች መመሥረት
፰. የተወሰኑ ሀይማኖታዊ መዝሙራት መዘጋጀት ምሳሌ መዝ. ፸፰ ፣ ፹፫ ፣ ፹፭ ወዘተ
፱. ስለ ሀይማኖት የመሠዋት (ሰማዕትነት) የመቀበል አጠቃላይ አዲስ አመለካከት
፲. የመቃብያን ስምና ማሕተም ያለባቸው ሣንቲሞች መቀረጽ
መቃቢስ የማታትዩ ፫ኛ ልጅ ነው፡፡ በብዛት የሚታወቀው ይሁዳ ወይም ይሁዳ መቃቢስ ተብሎ ነው፡፡ መቃቢስ ሲላ፣ አብያና ፊንቶን የሚበሉ ፫ ልጆች አሉት፡፡ እነዚህ የመቃቢስ ልጆች ለአምልኮተ እግዚአብሔር የሚቀኑ ለሀይማኖታቸው ከጨካኙ ጣኦት አምለኪ ጽሩጻይዳን ጋር ተከራክረው አንገታቸውን ለሴይፍ የሰጡ ሰማዕታተ መቃብያን ናቸው (መጽሓፈ መቃቢያንን ይመልከቱ)፡፡ 
የሮማውያን ግዛት (፷፫ ቅ.ክ - ፷፮ ዓ/ም)
በመቃብያን የነፃነትን አየር የተነፈሱ አይሁድ ዳግም ለዘመናት በሮማውያን ቅኝ ግዛት ስር ወደቁ፡፡ ሮማውያን በአስተዳደራዊ ስልትና መዋቅር የተዋጣለቸው ናቸው፡፡ በእስራኤል ክልላዊ አስተዳዳሪዎችን መድበው ሁለንተናዊ ቁጥጥራቸውን አጠናከሩ፡፡ አንጢፔተር የአይሁድን እምነት የተቀበለ ኤዶማዊ ነበር፡፡ በሮማውያን ከፍተኛ ድጋፍ የይሁዳ ገዥ ሆነ፡፡ በመጥፎነቱ የሚታወቀው ልጁ ሄሮድስ ፩ኛ የፍልስጥኤም ገዥ ሆኖ ተሸመ፡፡ በ፴፯ ቅ.ክ አስተዳዳሪ ፤ በ፴ ቅ.ክ ንጉሠ ነገሥት ሆነ፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ ፍልስጥኤምን ይገዛ የነበረውና ታላቁ ሄሮድስ ተብሎ የሚጠራው ይህ ክፉ ንጉሥ ነው፡፡ አስተዳደሩ የተዋጣለት ገዥ ነበር፡፡ የግሪካውያንንና የሮማውያንን በአይሁድ ዘንድ ለማስፋፋት ብዙ ጥሯል፡፡ ከመሞቱ በፊት መንግሥቱን ለሶስት ልጆቹ በማከፋፈል አርኬላዎስን የይሁዳ፣ አንጢጳስን የገሊላና ፕርያ፣ ፍሊጶስን የኢቱርያና ትሪኮንያ ገዥዎች አድርጎ ሾሞአቸዋል፡፡
አርኬላዎስ (፬ ቅ.ክ - ፮ ዓ/ም)
አርኬላዎስ በክፋትና ጭካኔው ከአባቱ የባሰ ምህረት የለሽ ሰው ነው፡፡ ጠላቶቹን ሁሉ ያለ ርኅራኄ ፈጃቸው፡፡ ሊቃነ ካህናት የሚሾሙትና የሚሻሩት በእሱ ድንገተኛ ፍላጎትና ውሳኔ ነው፡፡ ተሰሚነት ያላቸው ቤተሰቦቹ እርሱን ከስልጣን ለማውረድ ሴራ አሲረው ተወካዮችን ወደ ሮማው ቄሳር ልከው ከሰውታል (ይህን ታሪክ ከሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፱ ፥ ፳፪ - ፳፯ ካለው ታሪክ ጋር ያገናዝቡት)፡፡ በመጨረሻም አውጉስጦስ ቄሳር አርኬላዎስን ወደ ፈረንሳይ አጋዘው፡፡ በእሱም ምትክ ሮማዊ ወኪል ወይም እንደራሴ (Procurator) ሾመ፡፡
አንጢጳስ
አንጢጳስ በወንጌል የአራተኛው ክፍል ገዥ (Tetrach) ተብሎ ተጠቅሷል፡፡ ማቴ. ፲፬ ፥ ፩፡፡ በስልጣን ዘመኑ ግዛቱን ስልጣኑን አስከብሮ ለማቆየት ምንም ያልሠራ ደካማ ገዥ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም ቀበሮ ብሎ ጠርቶታል፡፡ ሉቃ. ፲፫ ፥ ፴፩፡፡
አንጢጳስ የንጉሥ አሬጡስን ልጅ አግብቶ ከፈታ በኋላ የወንድሙን የፍሊጶስን ሚስት ሄሮድያዳን ከወንድሙ ቀምቶ አገባ፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ በዚህ እኩይ ተግባሩ ይገስፀው ሰለነበር ዮሐንስን በወህኒ አስሮት ነበር፡፡ በልደቱ ቀን የሄሮድያዳ ልጅ ሰሎሜ በዘፈንና በዳንስ ልቡን ስላስደሰተችው የመንግሥቱን እኩሌታ እንኳ ቢሆን የለመነችውን ሁሉ ሊሰጣት በመኳንንቱና መሳፍንቱ ፊት ማለላት፡፡ ልጅቱም ከእናቷ ተማክራ የዮሐንስን አንገት ስለለመነችው የመጥምቁ ዮሐንስን አንገት በሴይፍ አስቆርጦ ሰጣት፡፡ አንጢጳስ የንጉሥ አሮጡስን ልጅ ፈትቶ ሌላ በማግባቱ ከንጉሡ ጋር ቅራኔ ውስጥ ገቡ፡፡ በጨረሻም ንጉሡ ተቆጥቶ ወደ ገውል የዛሬዋ ፈረንሳይ አግዞት እዚያው ሞተ፡፡
ፊሊጶስ (፬ ቅ.ክ - ፴፬ ዓ/ም)
ፊሊጶስ ከሁለቱ ወንድሞቹ የተሸለ የማስተዳደርና የመምራት ችሎታ ነበረው፡፡ ጥንተዊዋን የጳኒያን ከተማ ዳግም ገንብቶ  ፊሊጶስ ቂሳርያ ብሎ ሰይሟታል፡፡ ማቴ. ፲፮ ፥ ፲፫ ፤ ማር. ፰ ፥ ኧ፯፡፡ ይህ የሮማውን ቄሳር ለማስደሰትም ጭምር ነው፡፡ ፊሊጶስ በ፴፬ ዓ/ም ሲሞት መንግሥቱ የሮም ግዛት ወደ ነበረችው የሶርያ አውራጃ ተዳበለ፡፡
ከሄሮድስ ቤተሰብ የሆኑ አግሪጳ ፩ኛና አግሪጳ ፪ኛ የሚባሉ ሌሎች ሁለት ገዥዎችም በታሪክ ይታወቃሉ፡፡ አግሪጳ ፩ኛ የክርስቲያኖች ቀንደኛ አሳዳጅ ነበር፡፡ የሐዋ. ፲፪፡፡ ለፋርሳውን ከፍተኛ አክብሮት ያለው ታማኝ አይሁዳዊ ነው፡፡ አግሪጳ ፪ኛ ሰለቅዱስ ጳውሎስ ክስ ጉዳይ ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ሰፊ ክርክር አድርጎ ሐዋርያው ምንም ጥፋት ስላልተገኘበት ወደ ቄሳር ይግባኝ ባይል ኖሮ እፈታው ነበር በሎ በፍትህን ፈረደ፡፡ የሐዋ. ኧ፭ ፤ ኧ፮፡፡ 
ሮማውያን እንደራሴዎች (Roman Procurators)
አርኬላዎስ ከተጋዘ በኋላ ይሁዳ በሮማውያን እንደራሴዎች አስተዳደር ስር እንዴት እንደወደቀች ከላይ ተመልክተናል፡፡ ጴንናዊው ጲላጦስ ይሁዳን ያስተዳደረ ፭ኛው ሮማዊ ወኪል (እንደራሴ) ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ሮማውያን እንደራሴዎች እብዶችና በስልጣን የባለጉ ናቸው፡፡ ከአይሁድ ከፍተኛ ንቀትና ጥላቻ ነበራቸው፡፡
ከ፷፮ ዓ/ም ጀምሮ አይሁድ ከፍተኛ ቅንዓት ባላቸው መሪዎች አማካኝነት በሮማውያን ላይ ጦርነት ከፈቱ፡፡ ነገር ግን በቂ የሰለጠነ የሰው ኃይልና ድርጅታዊ መዋቅር ስላልነበራቸው በጦርነቱ ብዙ ኪሳራ ደረሰባቸው፡፡ በ፸ ዓ/ም የቫስፓሲያን ልጅ ጢጦስ ኢየሩሳሌምን ሙሉ በሙሉ አወደማት፡፡ ታላቁ የሰሎሞን ቤተ መቅደስም ተቃጠለ፡፡ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ አይቀርም ብሎ ጌታ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ፡፡ የኔሮን ቄሳር አልጋ ወራሾች ትራጃንና ሓድርያን አይሁድን በጭካኔ አሳደዱአቸው፡፡ እናት አገራቸውንና ቤተ መቅደሳቸውን አሳጡአው፡፡ አገራቸውን ለቀው ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት ተሰደዱ፡፡ እስራኤላውያን ከተበተኑበት ከየዓለማቱ በ፲፱፻፵፰ ዓ/ም ጠንካራዋን አገራቸውን እስራኤልን እንደገና መሠረቱ፡፡ አሁን ለምዕራብ ኢሲያ ሰላም እጦት ምክንያት በሆነው የስድስት ቀናት ጦርነት ከአረብ ሀገራት መሬት ወስደው ግዛታቸውን አጸኑ፡፡   

No comments:

Post a Comment