Friday, April 24, 2015

የወንድምህ የደሙ ድምጽ ከምድር ወደ እኔ ይጮሀል፡፡ ዘፍ. 4፥10

የአምላካችሁን ስም በሚገባ ተሸከማችሁ፣ ስለክርስትና አንገታችሁን ገብራችሁ፣ የአህዛብን ክፋትና ጭካኔ የተሞላ  ሕፁፅ አእምሮ በደማችሁ ጎርፍ ለዓለም ያስተማራችሁ፣ ዛሬም የሰማዕትነት ቡቃያ ዳግም በአህዛብ ምድር እንዲያቆጠቁጥ ያደረጋችሁ ሰማዕታተ  ሊቢያ እናንተ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ  የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰማዕታት ናችሁ፡፡

እናንተ ኢትዮጵያውያን ከዋክብት ክቡር ደማችሁ ደመ ከልብ ሆኖ አይቀርም፡፡ ወንድሙን በግፍ የገደለው ገዳዩን ቃየንን የወንድምህ የደሙ ድምጽ ከምድር ወደ እኔ ይጮሃል፡፡ አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምክ ነህ፡፡ ብሎ ነፍሰ ገዳዩን የገሰጸ አምላክ ደማችሁን ይበቀልላችኋል፡፡ ዘፍ. 4፥10-11
በገዛ ደሙ የዋጃችሁ ቸሩ አምላካችን ደማችሁን በክብር ያፍሳል፡፡ የሰማዕታትንም ክብር ያቀደጀችኋል፡፡ ስለስሙ ተርዳችኋልና መንግሥቱን ያወርሳችኋል፡፡ በአህዛብ ተጠልታችኋል በአምላካችሁ ዘንድ ክብራችሁ ታላቅ ነው፡፡ እናንተ በግፍ የታረዳችሁ ንጹሓን ወንድሞቼ በአደባባይ መታረዳችሁን ሳይ እጅግ አዘንኩ፤ ልቤም በሓዘን ተሰበረ፡፡ በጽናታችሁ ግን ኮራሁባችሁ፡፡ ክርስትና ሰማዕትነት ነው፤ ሰማዕትነትም ታላቅ ክብር ናት፤ የሕይወትንም አክሊል ታቀዳጃለች፡፡ ብንሞትም በክርስቶስ ሕያዋን ነን፡፡ ሞተንም ድሉ የኛ ነው፡፡ ክርስቲያን ሞቶ እንጂ ገድሎ አያሸንፍና፤ ሁሌም ባለድል፣ ሁሌም አሸናፊዎች ነን፡፡
  • እንደሚታረዱም በጎች ሆነናል፡፡ መዝ. 44፥22 
  • በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፣ ይገድሉአችሁማል፣ ስለስሜም በአህዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናለችሁ፡፡ ማቴ. 24 ፥ 9 
  • ስለአንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፣ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን… ሮሜ. 8፥36
እናንተ የወገኖቻችሁን(ያደምን ዘር) አንገት በሴይፍ የቀላችሁ የአይ ኤስ አይ ኤስ አባላት ቀታሊያነ ሰብእ(ሰውን የምትገድሉ) አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶላችኋልና እኛ ልጆቹ እንወዳችኋለን፡፡ ነገር ግን አረመኔያዊ እኩይ ተግባራችሁን እንቃወማለን፤ እናወገዝማለን፡፡ እናንተ የምትጠሉት፣ ወገኖቹንም የምታሳድዱበት የዓለም ቤዛ ቸሩ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ይወዳችኋልና ለንስሓ አብቅቶ እጃችሁን ከደም እንዲያነጻ እንጸልይላችኋለን፡፡ ክርስትና ፍቅር ነውና፡፡  




ሥላሴ ነፍሶቻችሁን በአብርሃም እቅፍ ያኑሩልን ፡፡
ላዘነው ወገኖቻችሁ ሁሉ ማጽናናትን ያድሉን ፡፡
ዲ/ን ዓለማየሁ ሀብቴ
ሚያዚያ 13 ቀን 2007 ዓ/ም










No comments:

Post a Comment