Monday, April 27, 2015

‘ክርስቶስ ካልተነሳ እንኪያስ ስብከታችን ከንቱ ነው፡፡ እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት’’ 1ቆሮ.15፥14፡፡


‘ክርስቶስ ካልተነሳ እንኪያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ከንቱ ናት’’ 1ቆሮ.15፥14፡፡ ከቅዱሳን ጋር ባላጋሮችና የማዕዘኑ ድንጋይ ክርስቶስ በሆነ በነቢያትና በሓዋርያት መሰረት እየታነፃችሁ ብቁ የእግዚአብሔር ማህደር ለመሆን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እየተሰራችሁ ያላችሁ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤት ሰዎች እንኳን በዘመነ ትንሳኤ በሰላም አደረሳችሁ፡፡ ኤፌ.2፥19-22 ውድ አንባብያን አሁንም በተለመደው አምዳችን ይህች በጣም አጭርና ግልጽ የሆነች ጦማር ይዤላችሁ ቀርቤያለሁ፡፡ መቼም ቢሆን ሰውም እንደ ጨረቃ ሰሌዳ ከራሱ የሆነ ብርሃን ስለሌለው የብርሃናት አባት እግዚአብሔር የዕውቀቱ ብርሃን ጥበብና ማስተዋሉ አእምሮውንና ለብዎውን በልባችሁ ሰሌዳ ይፅፍላችሁ ዘንድ እንዲሁም የቃሉ ደጅ እንዲከፍትላችሁ የዘወትር ፀሎቴ ነው፡፡ «ደግሞ የወንጌልን ምስጢር በግልጥ እንዲያስታውቀኝና ቃሉን ለመፅሐፍ ብዕሬን ያቃና ዘንድ ስለ እኔ ፀልዩ» ኤፌ 6፥19

ዘመነ ትንሳኤ ማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፤ሎቱ ስብሐት፤ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት አባታችን አዳም የጣለብንን በእኛ ላይ የነበረ የሚቃወመን በትዕዛዛት የተፃፈውን የዕዳ ደብዳቤ ደምስሶ በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ ያስወገደበትን ነው» ቆላ 2፥14-15፡፡ ይህን የምናስብበትም ወቅት ነው፡፡ በዚህ በዓለ ሃምሣ ወይም ዘመነ ትንሳኤ ልናስበውና ልናስተውለው የሚገባ መሰረታዊ ነገር የክርስቶስ ትንሳኤን የተመለከተ ነው፡፡ የትንሳኤው ነገር ካልገባን ሓዋርያው እንዳለው የሰባኪዎቻችን ስብከትና የእናንተም እምነት ከንቱዎች ናቸው፡፡ ስለ ትንሳኤ ኋላ እንመጣበታለን ወደ ኋላ ልመልሳችሁና ስቅለቱን እንደመግብያ እንጠቀም፡፡
 ስቅለት ማለት ጌታችን የተሰቀለበት ቀን ነው፡፡ በስጋ አባታች የሆነ አዳም ሰብአዊ ዘር በሙሉን ይወክላል፡፡ ከዚህም የተነሳ ሁሉም የሰው ዘር ከአዳም ከሚመነጨው ጥንተ አብሶ ተካፋይ ሆኖ ለዘመናት ዘልቋል፡፡ በቅዱሳት መጣሕፍት እንዲህ እናነባለን «በጌጋየ አሃዱ ብእሲ ቦኣ ኃጥአት ውስተ ዓለም ወበይእቲ ኃጢኣት ሞት» ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢዓትም ሞት » ሮሜ 51፥2፡፡ የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው ሮሜ 6፥23፡፡ እገሌና እገሌ ሳይባል ዓለም በሙሉ በአንዱ በአዳም ምክንያት ሁላችን ኃጥያተኞች ነበርን ሮሜ. 3፥23፡፡ ሞት ስላችሁ ተፈልጦተ ነፍስ እምስጋ የነፍስ ከስጋ መለየት እንዳልሆነ ይገባችኋል፡፡ እናንተ ርጉማን ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀው ወደ ዘልዓለም እሳት ከእኔ ሂዱ (ሑሩ እምኔየ) ማቴ. 25፥41 የሚለው ነው እንጂ፡፡ ታድያ ወኮነ ሰብኣ ከማነ ዘእንበለ ኃጢኣት ባሕቲታ (ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም) ያለ ኃጢአት በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሐ ጠባይዕ ሳያድፍበት የተወለደ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለው ሉቃ.1፥28-25 ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለሙ ሁሉ ቤዛ ይሆን ዘንድ ሊሰቀል ተገባው፡፡ ይህ ደግሞ የታመነና ሁሉም ሊቀበሉት የተገባ ነው፡፡1ጢሞ. 1፥15
 ልዑለ ቃል ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ አረፍተ ዘመናት ሳይገታው መንፈሳዊ ዓይኑ ተከፍቶ ከሰባት መቶ ዓመታት በኋላ በቀራንዮ ምን እንደሚከናወን አይቶ በመንፈስ ቅዱስ ተነድቶ እንዲህ ብሎ ተናገረ፡፡ በእውነት ደዌአችን ተቀበለ ህመማችንም ተሸከመ … ስለበደላችንም ደቀቀ ስለ መተላለፋችን ቆሰለ…. የብዙዎች ኃጢአት ተሸከመ ስለአመጸኞች ማለደ፡፡ ኢሳ. 53፥4-12
አዎን ክርስቶስ ከፃድቃን ነፍሳት ጋር ይቆጥረን ዘንድ ከአመፀኞች ጋር ተቆጠረ እኛን ከዘለዓለም ፍርድ ያድነን ዘንድ እሱ እንደ ወንጀለኛ ተፈርዶበት በዕፀ መስቀል ተሰቀለ አቤት ! አያችሁ የእግዚአብሔር ፍቅር! “ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት” (ኣባ ሕርያቆስ) በገነት የተመላለሱ እግሮቹ በመስቀል ተቸነከሩ፡፡ አዳምን የፈጠሩ እጆቹ በመስቀል ተቸነከሩ፡፡ በአዳም ላይ የህይወት እስትንፋስ እፍ ያለ አፍ ሐሞትና ከርቤ የተቀላለበት መጠጥ ጠጣ ማቴ. 27፥48 ቅዳሴ ዮሐንስ አፈወርቅ)፡፡ ፅምኣ ነፍሳችን ያረካ ዘንድ ሓሞት ጠጣ በእግረ ልቡናችሁ ቀራንዮን እየዞራችሁ በዓይነ ህሊናችሁ ግራና ቀኝ ቃኘት ካደረጋችሁ ለድህንነታችን የተሰቀለ ክርስቶስን ታያላችሁ፡፡ ታድያ ኦ! ትሕትና ዘመጠነ ዝ ትህትና ኦ! ትዕግስት ዘመጠነ ዝ ትእግስት ኦ! ፍቅር ዘመጠነ ዝ ፍቅር የሚል የአንክሮ መዝሙር በውስጣችሁ እንደ ተጥለቀለቀ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ ተቀበረም 1ቆሮ. 15፥3፡፡ ስለዚህ ስቅለትን በተመለከተ የምናከብረው በጭሩ ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን እንደ ሞተና የእኛ አዳማዊ ባህርይ ደግሞ በክርስቶስ ጥንተ አብሶ(የኣዳም በደል) በመስቀል ላይ መወገዱን ያረጋገጠበት ቀን ነው፡፡ በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከህግ እርግማን ዋጀን፡፡ ገላ. 3፥13
በሰሙነ ሕማማት የምንጠቀምበት አንድ የተለመደ ቃል እንዲህ ይላል፡፡ «ዘመፅኣ ወሐመ በእንቲአነ ወበሕማማቲሁ ቤዘወነ፣ የመጣው ስለ እኛ የታመመው በሕማማቱ ዋጀን» የሚል ነው፡፡ እውነት ነው፡፡ ሐዋርያው እንዳለው ክርስቶስ እርሱ ራሱ እርግማን ሆኖ ከእርግማን ዋጅቶናል፡፡ ይህን በዓል ያሳለፍነው ታድያ ክርስቶስ በደሙ በሕማማቱ እንደ ዋጀን ከብዙ በጥቂቱ የስቅለቱ በዓል በዚህ ዓይነት ሁኔታ አክብረን ካጠናቀቅንና ከተረዳን ትንሳኤው በተመለከተ ደግሞ ከቅዱሳት መጻሕፍት እንመርምር፡፡
 «ስለ መተላለፋችን አልፎ የተሰጠው እኛን ስለ ማጽደቅም የተነሳውን ጌታችን ኢየሱስን ከሙታን ባስነሳው ለምናምን ለእኛ ይቆጥርልን ዘንድ ነው»፡፡ ሮሜ. 4፥25 ይላል፡፡ በመጻሕፍት እንደ ተፃፈ ቤተ ክርስቶያናችንም እንደምትሰብከው፣ ሊቃውንት እንደሚያስተምሩት ክርስቶስ የሞተው የኃጢአታችን ዕዳ ለመክፈል ከሙታን የተነሳው ደግሞ ፅድቃችን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ደግሜ እላለሁ ጽድቃችንን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ለሃምሣ ቀናት የክርስቶስ መነሳት በአስተምህሮቷ፣ በአምልኮ ስርዓትዋ፣ ማለትም በማህሌት፣ በሰዓታት፣ በስርዓተ ቅዳሴ፣ በመዝሙራት፣ በተለያዩ ጣዕመ ዜማ ታስተምራለች፤ ትሰብካለች፡፡ ወቅቱን ዘመነ ትንሳኤ ብላ ለይታ አስቀምጣለች፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ የክርስቶስን ትንሳኤ እንደማታስተምር ምስጢረ ትንሳኤ ሙታን እንደ ሌላት አድርገው የሚያስቡ እንዲሁም ትምህርቷ ጥላሸት ለመቀባት የሚሞክሩ እንክርዳዶች መኖራቸው ባይዘነጋም በጣም ከሚታወቁና ከተለመዱት አስተምህሮአዊ አንዱና ቀላሉ «ክርስቶስ ተንስኣ እሙታን ሞተ ወኬደ ለሞት ለእለ ውስተ መቃብር ወሃበ ሕይወተ ዘለዓለም ዕረፍት» /ስርዓተ ቅዳሴ/፡፡ የዘመነ ትንሳኤ ምስጢር ሁሉ በዚች አጭር ጥቅስ ተጠቅሷል፡፡
 ቡራኬው ይደርብንና ሐዋርያው ‹‹እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሳችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን አስቡ. . . ሞታችኋልና ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና» ቆላ. 3፥1-4፡፡ ከመንፈሳዊ ሞት ተቀስቅሰን ከክርስቶስ ጋር ተነስተን ክርስቶስ ባለበት በሰማያዊ ስፍራ መቀመጣችን ሕይወታችን ከክርስቶስ ጋር መሰወርዋን ደግመን ደጋግመን ቆም ብለን ልናስብ ይገባል፡፡ አሁን ብዕሬ ወደ እያንዳንዳችን ጓዳ እየገሰገሰች ነው ልትመጣባችሁ ነው ልባችሁ ሰፋ አድርጉ፡፡ እንደሚታወቀው አብዛኛው ህብረተሰባችን ዘመነ ትንሳኤን የሚያከብረው (የሚያሳልፈው) ከመብልና ከመጠጥ ጋር በተያያዘ ነው እንጂ ከክርስቶስ ጋር መነሳታቸውና ሕይወታቸው ከክርስቶስ እንደተሰወረ አያስታውሱም፡፡ ታድያ በመብልና በመጠጥ ከሆነ ትንሳኤ በመጣ ቁጥር ስለ አስቤዛ የምንጨናነቅ ከሆነ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያወርስም;; ሐዋርያውስ ምን አለ? «የእግዚአብሔር መንግሥት የጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችም» ሮሜ. 14፥17፡፡ በተለይ በአንዳንድ አካባቢማ ጉድ ነው ቤታቸው ቄጠማ ካልተጎዘጎዘ፣ ሰንደል ካልተጨሰ፣ በቡና ሲኒዎች ዙርያ እጣን ካልተጎለጎለ(ቡልል ቡል ካላለ)፣ አዲስ ልብስ ካልተለበሰ፣ የበግ ወይም የዶሮ ደም ካልፈሰሰ ትንሣኤን ያከበሩ አይማስላቸውም፤ የበዓሉ ድባብ አይታያቸውም፡፡ ኦ! ኦ! ኦ! የክርስቶስ ደም ለኃጢአታችን ስርየት መፍሰሱ እንዴት ነው? አልገባችሁም እንዴ? እንዲህ ከሆነ የትንሳኤ በዓል በዚህ ሁኔታ ካለፈ ከክርስትና በጣም ርቆናል ወይም ኋላ ቀርተናል፡፡ ማስተዋል! ማስተዋል! ማስተዋል! የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ ካልተዝናኑ፣ ጭፈራ ቤት ካልገቡ፣ ካልጠጡ በዓል አይባልም! ታድያ በዚሁ ሳምንት ከታዘብኳቸው ተነስቼ ከሐዋሪያው ጥቅስ በመነሳት የትንሳኤ በዓል ከዚህ ከተድበሰበሰ በነፍሳችን ላይ መንፈሳዊ ትንሳኤ የማይቀሰቅስ ከሆነ እኛ ምድራውያን ሐሳባችንም ምድራዊ ነው፡፡ እና? እናማ ስብከታችን ከንቱ ነው፡፡ እምነታችሁ ከንቱ ናት፡፡ ይቆዬን…፡፡

ከመምህር ጽጌ


No comments:

Post a Comment