እግዚአብሔር አሁንም ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ ሲል
በድጋሚ ነቢዩ ዮናስን አዘዘው፡፡ የምነግርህንም ስብከት ስበክላት አለው።
እኛስ የዛሬዎቹ ሰባኪያነ ወንጌልና መምህራን ወደ ተላክንበት ቦታ እሺ በጀ ብለን እንሄዳልን? የውሎ አበሉ፣ መስተንግዶና ማረፍያው ሳያሳስበን በነፃ የተቀበልነውን ወንጌል በነፃ ለመስጠት ፈቃደኛ የምንሆን ስንቶቻችን ነን? በእውነት የሰዎች ድህነት፣ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የሚያሳስበን እውነተኞች ወንጌላውያን ነን? ዝናው ያሳሰበው፣ ክብሩ ያስጨነቀው ነቢዩ ዮናስ ሽሽቱ አላዋጣውም፡፡ ለዓሣ ሆድ ዳረገው እንጂ፡፡ ከሽሽቱ በግድ ሲመለስ ክብርና ዝና አይደለም መጠሊያ እንኳን ወደማያገኝባት ነነዌ እንዲሄድ ታዘዘ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የሚነግርህን ስብከት ስበክላት ነው የተባለው፡፡ በእውነት የምንሰብከው እግዚአብሔር ያዘዘንን ነው? እግዚአብሔር ያልላከቸው ያልታዘዙትን ስብከት የሚሰብኩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ዝናቸውን የሚናኙ፣ ጉራቸውን የሚቸረችሩ፣ ክብራቸውን የሚሰብኩ፣ ንግዳቸውን የሚያውጁ አስመሳይ ሸቃጭ ነጋዴዎች፣ ፖለቲካን የሚያቀነቅኑ ቅጥረኞች፣ ተሓድሶ (ኑፋቄን) የሚሰብኩ የበግ ለምድ ለባሽ ተኩላዎች ብዙ ናቸው፡፡ ቤተ ክስርስተያንን እናድስ ይሉናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሕንፃዋ እንጅ እምነቷ አይታደስም፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ናት፡፡ በሓጢአት የቆሸሹ አስተሳሰባቸው የዘቀጠ በአእምሮ ያረጁትን ታድሳለች እንጂ እርሷ የማታረጅ የማትታደስ ስንዱ እናት ሰማያዊት ተቋም ናት፡፡ እድሳት የሚያስፈልገው የተዘባ አመለካከት፣ በምንፍቅና የተበረዘ አስተሳሰብ፣ ማመን የተሳነው ልብ፣ ማገናዘብ ያቃተው አእምሮ ነው፡፡
ነቢዩ ዮናስም ተነሥቶ እንደ እግዚአብሔር ቃል ወደ ነነዌ ሄደ፡፡ ነነዌም የሦስት ቀን መንገድ ያህል እጅግ ታላቅ ከተማ ነበረች። ዮናስም የአንድ ቀን መንገድ ያህል ወደ ከተማይቱ ውስጥ ገባ፡፡ ሰበከም ካልተመለሳችሁ ንስሓም ከልገባችሁ ከተማችሁ ታላቋ ነነዌ በሶስት ቀን ውስጥ ትጠፋለች ብሎ አስተማረ፡፡ የነነዌ ሰዎችም የእግዚአብሔርን ቃል ሰሙ፡፡ በነቢዩ ዮናስ ስብከት አምነው ንስሓ ገቡ፡፡ ከሊቅ አስከ ደቂቅ ማቅ ለበሱ፣ ጾምን አወጁ፣ በአንድነትም ወደ እግዚአብሔር አለቀሱ፡፡
ይህ ነገር ወደ ቤተ መንግሥት ደርሶ በነነዌ ንጉሥ ዘንድ ተሰማ፡፡ ንጉሡም ይህ
የምሰማው ነገር ምንድን ነው ብሎ ጠየቀ፡፡ እንዲህም ብለው ነገሩት፡- ታላቅ እግዚአብሔር ሰው ወደ ከተማህ ገብቷል፡፡ በደላችሁ
በዝቷልና ካልተመለሳችሁ ንስሓም ከልገባችሁ ታላቋ ነነዌ በሶስት ቀን ውስጥ ትጠፋለች፡፡ አሳት ይበላታል፤ የሰዶምና ገሞራ እጣ
ፈንታ ይደርሳታል ብሏል፡፡ ሕዝቡም ፈርቶ ማቅ ለብሶ ጾም አውጇል አሉት፡፡
ታዲያ የንጉሡ ውሳኔ ምን ይሆን? ነቢዩን ያስረው ይሆን? ሕዝቤን አስደነገጥክ፣ ሰላም
ነስተህ፣ መዓት አውርተህ ሰውን አሸማቀህ ሥራ አስፈታህ ብሎ ይቀጣው ይሆን? አስታዋይና አርቆ ኣሳቢ እግዚአብሔርን የሚፈረው
የነነዌ ንጉሥ ከዙፋኑ ወርዶ አመድ ላይ ተቀመጠ፣ መጎናጸፊያውን አውልቆ ማቅ ለበሰ፡፡ ሰውና እንስሳት አንዳች አይቅመሱ፣
እንስሳትም አይሰማሩ፣ ውሃም አይጠጡ፡፡ ሰውና እንስሳት በማቅ ይከደኑ፤ ወደ እግዚአብሔርም በብርቱ ይጩኹ፣ ሰዎችም ሁሉ ከክፉ መንገዳቸውና በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ። እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ተመልሶ ይጸጸት እንደ ሆነ፥ ከጽኑ ቍጣውም ይመለስ እንደ ሆነ ማን ያውቃል? ብሎ ታላቅ ሱባኤ አወጀ፡፡ “እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን
አየ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም”። ዮና. ፫፡፡
ለሕዝቡ የሚያስብ፣ ለሀገር የሚቆረቆር እውነተኛ የሀገር መሪ የሕዝብ አስተዳዳሪ ይህ
ነው፡፡ በሠራዊት ብዛት የማይቀለበስ፣ በጦር መሣርያ ብዛት የማይመለስ፣ በስልጣኔ የማይገታ፣ በመንግሥታት የተባበረ ክንድ
የማይመከት በሀገር ላይ የተቃጠውን የእግዚአብሔር ቁጣ በሱባኤ የሚመልስ፣ በምህላ የሚቀለብስ አማኝ ንጉሥ፡፡ አሁን ዓለማችን
እንዲህ ያሉ ነገሥታት ያስፈልጉአታል፡፡ ዓለማችን ዛሬ ትልቅ ችግር ውስጥ ነው ያለችው፡፡ ረሃቡ፣ በሽታው፣ ጦርነቱ፣ የተፈጥሮ
ቁጣው (የአየር ለውጡ፣ የመሬት መንቀጥቀጡ፣ የሰደድ አሳቱ፣ ማዕበሉ፣ አውሎ ነፋሱ፣… ወዘተ) እያስጨነቁኣት ነው፡፡ አንድም
ቀን በሰላም ውላ አድራ አታውቅም፡፡ የሰውን አንገት የሚቀሉ፣ ሴቶችን የሚያስነውሩ፣ ቅርስ የሚያጠፉ፣ ሀገር የሚበታትኑ፣
ሕዝብን በጅምላ የሚጨፈጭፉ መዓተኞች አሉባት፡፡ ይህ ቁጣ ነው፡፡ የዓም ስልጣኔ የነገሥታት ብርታት ሊያስታግሰው አልቻለም፡፡
እግዚአብሔር ካልመለሰው በቀር በሰው አቅም የሚገታ አይደለም፡፡ ዓለም ሰላም የምታገኘው በኃያላን ነገሥታት ስምምነት፣ በጦር
ኃይል ጥምረት አይደለም፡፡ ከፈርጣማ ክንዳቸው ወርደው በእግዚአብሔር የሚታመኑ ነገሥታት ሲኖሩኣት ብቻ ነው፡፡ የሰላም አለቃ
የሰላም ንጉሥ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡
የነነዌ ሰዎችና እንስሳት ሶስት ቀንና ሶስት ሌሊት ጾመው የእግዚአብሔርን ምህረት
አገኙ፡፡ ከቁጣ ዳኑ፤ ከመዓትም አመለጡ፡፡ በዘመናች ግን ጾምን የሚቃወሙ ከእንስሳት ያነሰ አስተሳሰብ ያለቸው አልታጡም፡፡ ጾም
በእግዚአብሔር የተወደደች የምህረት ማግኛ መንገድ ነች፡፡ “አሁንስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና
በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ። ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ፥ ቍጣው የዘገየ፥
ምሕረቱም የበዛ፥ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ። ኢዩ. ፪፥ ፲፪- ፲፫”፡፡
ይህ የእግዚአብሔር ምህረቱ፣ ቸርነቱና ይቅር በይነቱ ነቢዩ ዮናስን አለስደሰተውም፡፡
ዮናስ ከነነዌ ሕዝብ ድህነት ይልቅ አሁንም ስለክብሩ መጨነቅ ጀመረ፡፡ ሐሰተኛ ነቢይ እንዳይበል ፈራ፡፡ እግዚአብሔር ለነነዌ
ሕዝብ ምህረት በማድረጉም ተቆጣ፡፡ እንዲህም ብሎ ጸለየ፡- “አቤቱ፥ እለምንሃለሁ በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን?
አንተ ቸርና ይቅር ባይ፥ ታጋሽም፥ ምሕረትህም የበዛ፥ ከክፉው ነገርም የተነሣ የምትጸጸት አምላክ እንደ ሆንህ አውቄ ነበርና
ስለዚህ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል ፈጥኜ ነበር። አሁንም፥ አቤቱ፥ ከሕይወት ሞት ይሻለኛልና እባክህ፥ ነፍሴን ከእኔ ውሰድ አለው።
እግዚአብሔርም፦ በውኑ ትቈጣ ዘንድ ይገባሃልን? አለ። ዮናስም ከከተማይቱ ወጣ፥ ከከተማይቱም በስተ ምሥራቅ በኩል ተቀመጠ፡፡
ከተማይቱንም የሚያገኛትን እስኪያይ ድረስ በዚያ ለራሱ ዳስ ሠርቶ ከጥላው በታች ተቀመጠ። እግዚአብሔር አምላክም ቅል አዘጋጀ፥
ከጭንቀቱም ታድነው ዘንድ በራሱ ላይ ጥላ እንድትሆን በዮናስ ላይ ከፍ ከፍ አደረጋት፡፡ ዮናስም ስለ ቅሊቱ እጅግ ደስ
አለው።በነጋው ግን ወገግ ባለ ጊዜ እግዚአብሔር ትልን አዘጋጀ፥ እርስዋም ቅሊቱን እስክትደርቅ ድረስ መታቻት። ፀሐይም በወጣች
ጊዜ እግዚአብሔር ትኩስ የምሥራቅ ነፋስ አዘጋጀ ዮናስ እስኪዝል ድረስም ፀሐይ ራሱን መታው ለራሱም ሞትን ፈለገና። ከሕይወት
ሞት ይሻለኛል አለ። እግዚአብሔርም ዮናስን፦ በውኑ ስለዚች ቅል ትቈጣ ዘንድ ይገባሃልን? አለው። እርሱም፦ እስከ ሞት ድረስ
እቈጣ ዘንድ ይገባኛል አለ። እግዚአብሔርም፦ አንተ ትበቅል ዘንድ ላልደከምህባት ላላሳደግሃትም፥ በአንድ ሌሊት ለበቀለች፥
በአንድ ሌሊትም ለደረቀችው ቅል አዝነሃል። እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሀያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች
ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን? አለው”። ዮና.፬፡፡
ነቢዩ ዮናስ በየዋህነቱ ለእግዚአብሔር አልታዘዝ ቢልም እግዚአብሔር አምላኩ
አላሳፈረውም፡፡ እግዚአብሔር ሁልጊዜም ወደጆቹን ያከብራቸዋል እንጂ አያሳፍራቸውም፡፡ የሰውና የእግዚአብሔር ሀሳብ ለየቅል
ነው፡፡ ሰው ጥፋትን ሲያስብ እግዚአብሔር ድህነትን ያዘጋጃል፡፡ ሰው ክብርን ሲያስብ እግዚአብሔር ያዋርደዋል፡፡ ሰው ውርደትን
ሲሻ እግዚአብሔር ደግሞ ያከብረዋል፡፡
ነነዌ እንዳትጠፋ
እግዚአብሔር አምላክ ጾም ጸሎታቸውን ተቀብሎ ጩኸታቸውን ሰምቶ ቁጣውን በምህረት መዓቱን በትእግስት መለሰላቸው፡፡ ወደጁ ዮናስም
እንደፈራው ሀሰተኛ ነቢይ እንደይባል የተቃጠው በእግዚአብሔር ቁጣ ነነዌ ላይ የታዘዘው እሳት የረጃጅም ዘፎችን ጫፍ ጫፋቸውን
በልቶ ተይቶ መመለሱን ሊቀውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዮናስም የተናገረው በመታየቱ ተደስቶ
እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡ ወገኖቼ እኛ በታማኝነት እንታዘዘው እንጂ አምላካችን እግዚአብሔር አያሰፍረንም፡፡ እኛ ወደምንቀርመው
ቃርሚያ ሳይሆን እርሱ ወደአሰማራን እርሻ እንሂድ፡፡ ያኔ እንከብራለን፡፡ እንበለጽገለንም፡፡
የአዳም ዘር ሁሉ ሆይ፡- ዛሬ የዓለም ማዕበሉ እንዳያውከን (መከራ፣ ሓጢአት)፣ አንበሪው (ሴይጣን፣ ሞተ ነፍስ)
እንዳይውጠን እግዚአብሔር ወደላከን ወደ ታላቂቷ ከተማ ወደ ነነዌ
(ንስኀ ወደሚሰበክባት፣ ፍቁራነ እግዚአብሔር ነቢያት ወሐዋርያት ወደ አሉባት፣ ለዓለም ሁሉ ወደሚጸለይባት ቅድስት ቤተ
ክርስቲያ) መሄድ ይገባናል፡፡ ክርስቶስ በደሙ በመሠረታት ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበን ስለሰው ደህንነት፣ ስለዓለም ሰላም
እንጸልይ፡፡ አንድ ልብ መካሪ አንድ ሀሳብ ተናጋሪ ሆነን በአንድነት ጉባኤ ጾምን እናውጅ፡፡ ቅዱስ መጽሓፍ እንዲህ
ይመክረናል፡- “በጽዮን መለከትን ንፉ፥ ጾምንም ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ፥ ሕዝቡንም አከማቹ፥ ማኅበሩንም ቀድሱ፥ ሽማግሌዎቹንም
ሰብስቡ፥ ሕፃናቱንና ጡት የሚጠቡትን አከማቹ ሙሽራው ከእልፍኙ፥ ሙሽራይቱም ከጫጉላዋ ይውጡ። የእግዚአብሔርም አገልጋዬች ካህናት
ከወለሉና ከመሠዊያው መካከል እያለቀሱ። አቤቱ፥ ለሕዝብህ ራራ፥ አሕዛብም እንዳይነቅፉአቸው ርስትህን ለማላገጫ አሳልፈህ አትስጥ ከአሕዛብ መካከል።
አምላካቸው ወዴት ነው? ስለ ምን ይላሉ? ይበሉ። ኢዩ. ፪፥ ፲፭- ፲፯”፡፡ ታዲያ ጾማችን የእውነት ጾም ይሁን፡፡ ራሳችንን
በእግዚአብሔር ፊት አዋርደን ከልብ እንጸልይ፣ በትህትና እንመጸውት፡፡
እንግዲህ ወገኖቼ፡- የሰው ክብር የሀገር ፍቅር ይኑረን፤ የሰውን ችግር እንረዳ፣
ርህራሄ ይኑረን፡፡ አሰመሳዮች እውነትን ይሥሩ፣ ቀማኞች የቀሙትን ይመልሱ፣ ጉበኞች (በዘመኑ ቋንቋ ሙሰኞች) ደመወዛቸው
ይብቃቸው፣ ደኞች በእውነት ይፍረዱ፣ ነጋዴው በሚዛን አይበድል፣ አለቃው ሠራተኛን አያስቆጣ፣ ሠራተኛውም በሥራ አይለግም፡፡
በደዮች ማሩኝታ እንጠይቅ፣ ተበደዮችም ይቅርታ እናድርግ፡፡ ክብር ለሚገባው ሁሉ ክብር እንስጥ፡፡ ምንፍቅና ያለበት ይመን፣
የሚጠራጠር አይኑር፣ ተሓድሶዎችም ህሊናቸውን አጽድተው በንሥኀ ይታደሱ፡፡ ሰበኪያነ ወንጌል መምህራን በእውነት ያስተምሩ፣
አበቶች ለተሸሙለት ለመንጋው ይጨነቁ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቁ፣ ስለእርሷ ይኑሩ፡፡ “በገዛ ደሙ የዋጃትን
የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ
ተጠንቀቁ። የሐዋ. ፳፥ ፳፰፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
No comments:
Post a Comment