Thursday, February 25, 2016

በአክናፈ መላእክት ይጠብቀናል፡፡



በወዳጁ በነቢዩ ዮናስ ስብከት የሕዝበ ነነዌን እዝነ ልቡና ከፍቶ በንሥኃ ወደ ራሱ የጠራ፤ ምህላ ጸሎታቸውን ተቀብሎ ቁጣውን በምህረት፣ መዓቱን በትእግስት የመለሰ አምላክ፤ ዛሬም በጾመ ነነዌ ፍጻሜ በቸሪት እናቱ ሰዓሊተ ምህረት፣ አቁራሪተ መዓት፣ አፍጣኒተ ረድኤት፣ ምዕረገ ጸሎት፤ በእለተ ኪዳነ ምሕረት እክለ በረከቱን ሊመግበን ዝናመ ምሕረቱን አውርዶልናል፡፡
ምሕረቱን ከእኛ ያላራቀ፣ በዐይነ ምሕረቱ የጎበኘን፣ እንደ ሰውነታችን ክፋት እንደ ኃጢአታችን ብዛት ተቆጥቶ ያላጠፋን ቸሩ አምላካችን ይክበር፤ ይመስገን፡፡ አምላካችን በትእዛዙ ለሚሆነው ይቅርታ ስፍር ቁትር የለውም፡፡ ገናና እግዚአብሔር እርሱ ብቻ ነውና ይቅር ባይ፣ ከቁጣ የራቀ፣ በይቅርታውም ብዛት የሰውን ኃጢአት የሚያስተሠርይ፤ ለኃጥአን ንሥኃ የሠራ የፃድቃን አምላክ ነው፡፡
አማላካችን ሁል ጊዜ በሕግ በአምልኮ ወደ እርሱ የሚቀርቡትን በረድኤት፣ በምሕረት፣ በቸርነት ይቀርባቸዋል፤ በበረከትም ያትረፈርፋቸዋል፡፡ ጠባቂ መልአክ ተራደኢ ሰማእት ያዝላቸዋል፡፡ በአክናፈ መላእክት ይጠብቃቸዋል፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል። እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም በእርሱ የሚታመን ሰው ምስጉን ነው። የሚፈሩት አንዳችን አያጡምና ቅዱሳኑ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ፍሩት እንዲል መዝ. ፴፫(፴፬)፥ ፯- ፱።  እድሜ ለንሥኃ ዘመን ለፍስሃ ሰጥቶ የሕይወት ዘመናቸውን ይባርክላቸዋል፡፡ በረድኤት ስቦ በፍቅር አቅርቦ ዘለዓለማዊት መንግሥቱን ይሰጣቸዋል፡፡
በደዊት መዝሙር ኢትዮጵያ ተበጽእ እደዊሃ ሀበ እግዚአብሔር ተብሎ እንደ ተነገረው አሁንም ኢትዮጵያውን ሁሉ ለሰው ልጅ ደህንነት፣ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ስለ ለዓለም ሰላም በአንቅሆ ህሊና፣ በአንቃዕዶ ልቡና፣ በሰፊሃ እድ ዘወትር ወደ እግዚአብሔር መጸለይ ይገባናል፡፡  

በዐይነ ምሕረቱ የጎበኘን አማላካችን ምስጋና ይሁን፡፡

No comments:

Post a Comment