Monday, February 22, 2016

ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፡፡ ዮናስ ፩፥ ፪ ክፍል ፩


ይህ ከእግዚአብሔር ለሰው ልጅ የተሰጠ ትእዛዝ ነው፡፡ ለነቢዩ ዮናስ የተሰጠ የሕይወት አድን መመርያ፣ ሰውን የማዳን ተልእኮ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ዓላማ ሰውን ማዳን ነው፡፡ ዮናስ ማለት ርግብ፣ የዋህ ማለት ነው፡፡ ዮናስ የዋህ ነቢይ ነው፡፡
ነነዌ ከአንድ መቶ ሃያ ሺ በላይ ሕዝብ የሚኖርባት ታላቅ ከተማ ናት፡፡ ነነዌ በነቢያት ብዙ ሸክም (ኃጢአት) የተነገረባት፣ የእግዚአብሔር ቁጣ የተቃጣባት የኃጢአት አምባ ናት፡፡
የነነዌ  ምልዓተ ኃጢአት እንደ ሕዝቧ ብዛት ነበር፡፡ በከተማዋ የሚሠራው ኃጢአት፣ ግፍና በደል እግዚአብሔርን አስቆጥቶ ቅጣት ታዘዘባት፡፡ በእሳት ተለብልባ ልትጠፋ፣ ሰውና እንሰሳዋን ሊበላ ጽኑእ የእግዚአብሔር ቁጣ እሳት ቃጣባት፡፡ ተፀፅታ  ከኃጥአቷ ካልተመለሰች በሶስት ቀን ውስጥ እንድትጠፋ በእግዚአብሔር ተወሰነባት፡፡ “ለደም ከተማ ወዮላት! በሁለንተናዋ ሐሰትና ቅሚያ ሞልቶባታል ንጥቂያ ከእርስዋ አያልቅም፡፡ የአለንጋ ድምፅ፥ የመንኰራኵርም ድምፅ፥ የፈረሶችም ኮቴ፥ የፈጣን ሰረገላም ጩኸት ተሰምቶአል ፈረሰኛው ይጋልባል፥ ሰይፍም ይንቦገቦጋል፥ ጦርም ይብለጨለጫል የተገደሉትም ይበዛሉ፥ በድኖችም በክምር ይከመራሉ፥ ሬሳቸውም አይቈጠርም በሬሳቸውም ይሰናከላሉ። ስለ ተዋበችው ጋለሞታ ግልሙትና ብዛት ይህ ሆኖአል እርስዋም በመተትዋ እጅግ በለጠች፥ አሕዛብንም በግልሙትናዋ፥ ወገኖችንም በመተትዋ ሸጠች። እነሆ፥ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ ልብስሽን በፊትሽ እገልጣለሁ ኅፍረተ ሥጋሽንም ለአሕዛብ፥ ነውርሽንም ለመንግሥታት አሳያለሁ። ርኵሰትንም በላይሽ እጥላለሁ፥ እንቅሻማለሁ፥ ማላገጫም አደርግሻለሁ። የሚያይሽም ሁሉ ከአንቺ ሸሽቶ። ነነዌ ባድማ ሆናለች የሚያለቅስላትስ ማን ነው? የሚያጽናናትንስ ከወዴት እፈልጋለሁ? ይላል። ናሆ. ፫፥ ፩- ፯”፡፡
ልዑል እግዚአብሔር ኃጢአትን ቢጠላም በፍጡራን ጥፋት አይደሰትም፡፡ የሰው ጥፋት ያሳዝነዋል፡፡ ነነዌን ከተቃጣባት ጥፋት ይታደጋት ዘንድ ነቢዩ ዮናስን ወደ ነነዌ ላከው፡፡ “የእግዚአብሔርም ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ። ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ ክፉታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቶአልና በእርስዋ ላይ ስበክ። ዮናስ ፩፥ ፩- ፪”፡፡
የዋሁ ነቢይ ዮናስ የእግዚአብሔርን ምህረት፣ ቸርነትና ይቀር ባይነት ያውቃልና እኔ ነነዌ ትጠፋለች፣ በእሳትም ትጋያለች ብዬ በስተምራቸው እነርሱም ተፀፅተው ንስሓ ቢገቡ እግዚአብሔር በብዝኃ ምህረቱ ይቅር ብሎአቸው ነነዌ ሳትጠፋ ትቀራለች፡፡ እኔም ሀሰተኛ ነቢይ ተብዬ ዘለዓለም ሳፍር እኖራለሁ ብሎ በማሰብ እግዚአብሔር ደግሞ ወደ ነነዌ እንዳይልከው ከእግዚአብሔር ፊት ለመኮብለል (ለመሰወር) ወሰነ፡፡ ነቢዩ ዮናስ ነቢየ እግዚአብሔር ቢሆንም የእግዚአብሔር ዓላማ ገና አልገባውም፡፡ የእግዚአብሔር ማዳኑ ያሳፍረኛል፣ ይቅርታው ውሸታም ነቢይ ያስብለኛል አለ፡፡ ለእግዚአብሔር ከመታዘዝ ይልቅ ሽሽትን መረጠ፡፡ ሕይወትን ከመዳን ይልቅ ለክብሩ ተጨነቀ፣ ዝናው አሳሰበው፡፡
በዘማናችንም ሀብት ንብረት ሽተው፤ ዝናን ፈልገው፣ ክብርን ተመኝተው ከእግዚአብሔር ፊት፣ ከቤተ ክርስቲያን ጉያ የሚኮበልሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ የዛሬዎቹ ጳጳሳት፣ መነኮሳት፣ ካህናት፣ ሰባኪያነ ወንጌል፣ ዘማርያን፣ የሀገር አሰተዳዳሪዎች በአጠቃላይ መንፈሳውያንና ዓለማውያን የሕዝብ መሪዎች፣ እረኞችና አገልጋዮች ለሾመን ለእግዚአብሔር እንታዘዘላን? በተሰማራንበት መስክ ታማኝ አገልጋዮች ነን? በያለንበት ወንበር ላይ ለምን እንዳስቀመጠን የእግዚአብሄር ዓላማው ገብቶናል? በሰዎች መቃብር፣ በቤተ ክርስቲያን መገፋት፣ በሀገር ጥፋት ላይ ቆመን ኪሳችንን ከመሙላት፣ ያልተገባ ሀብትና ንብረት ከማጋበስ፣ ዝናን ከመናኘትና ክብርን ከመፈለግ ይልቅ ሕይወትን ለማድን፣ ፈጣሪን ለማገልገል፣ ለሀገር ልማት፤ ለወገን እድገትና ደህንነት መትጋት ይገባችኋል፡፡ ዝናውም ክብሩም ከዚህ በኋላ ይመጣል፡፡ ነቢዩ ዮናስ እግዚአብሔር አግኝቶ ዳግም ወደ ነነዌ እንዳይልከው እግዚአብሔር ወደ ሌለበት ወደ ተርሴስ ለመሄድ በመርከብ ተሳፈረ፡፡
 ነገር ግን እግዚአብሔር የሌለበት ቦታ፣ ከእርሱ የተደበቀ ስፍራ፣ እርሱ የማይገዛው ዓለም የለም፡፡ እግዚአብሔር ዮናስ የተሳፈረባትን መርከብ በታላቅ ማዕበል መታት፡፡ መንገደኞቹ ሁሉ ተጨነቁ፡፡ መርከቧም እንዳትሰጥም ክብደቷን ለመቀነስ ዕቃቸውን ሁሉ ወደ ባሕር ጣሉ፡፡ የዋሁ ዮናስ ግን ተኝቶ ነበር፡፡ የሰዎችን ጭንቅና መከራ አላየም፡፡ የመርከቡ አለቃ ከእንቅልፉ ቀስቅሶ ከመከራ እንድንድን ጸልይ አለው፡፡
ዛሬም የሰው ችግር የማይገባቸው፣ መከራው የማይታያቸው፣ ረሀብ እርዛቱ የማይታወቃቸው፣ ሀዘኑ የማይሰማቸው ጆሮ ዳባ ለብሰው ደሃ እየበደሉ ፍትሕ እያጓደሉ በግድ የለሽነት አልጋ በመርከቡ ችግር የውስጠኛ ክፍል የተኙ ጨካኞች፤ የኃጢአት እንቅልፍ ያንቀላፉ ደካሞች ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ እንቅልፋሞች የኃጢአት ድቅድቅ ጨለማ ነግቶ የሕይወት ብርሀን እንዲበራለቸው መርከቧ ሳትሰምጥ ነቅተው ወደ አምላክ መጮህ አለባቸው፡፡ “ስለዚህ፦ አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል ይላል። ኤፌ. ፭፥ ፲፬”፡፡

መርከበኞቹ ይህ ክፉ መከራ በማን ምክንያት እንዳገኛቸው ለማወቅ እጣ ተጣጣሉ፡፡ እጣውም በዮናስ ላይ ወደቀ፡፡ ያን ጊዜ ዮናስን ሀገርህ ወዴት ነው? ከማን ወገን ነህ? ግብርህስ ምድን ነው? ለምንስ ይህን መከራ አመጣህብን? ብለው ጠየቁት፡፡ እርሱም ከእግዚአብሔር ፊት የሚሸሽ ዕብራዊ ነቢይ ነኝ፣ መከራው የመጣባችሁ በኔ ምክንያት ነው አላቸው፡፡ ከማዕበሉ እንድንድን ምን እናድርግ አሉት፡፡ ከማዕበሉ ተርፋችሁ በሕይወት ለመኖር ከፈለጋችሁ እኔን ወደ ባሕር ጣሉኝ ማዕበሉ ጸጥ ይልላችኋል አላቸው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ጥፋቱ ገባው፡፡ በደለኛ ነኝ ብሎ ሞትን በራሱ ላይ ፈረደ፡፡ ራሱን ረስቶ ለሌሎች ማሰብ ጀመረ፡፡ መርከበኞቹ ዮናስን ወደ ባሕር ለመጣል አልፈለጉም፡፡ እርሱ እንዳዘነላቸው አነርሱም አዘኑለት፡፡ እኛ ስንቱን ሰው በመከራ ባሕር ውስጥ ጥለን ይሆን? ሊያውም ንፁኃንን፡፡ እሱን ወደ ባሕሩ ከመጣል ይልቅ ቶሎ ቶሎ ቀዝፈው ወደ ወደቡ ለመድረስ ሞከሩ፡፡ ግን አልተሳካላቸውም፤ ማዕበሉ በረታባቸው፡፡ የንፁህን ሰው ደም በእጃችን አታድርግብን እያሉ በቁጣ ሳይሆን በጸሎት ነቢየ እግዚአብሔር ዮናስን ወደ ባሕር ጣሉት፡፡ ማዕበሉ ጸጥ አለላቸው፡፡ ዮናስ ፩፡፡

ዓለምንና በዓለም ያሉትን የሚገዛ ፍጡራን ሁሉ የሚታዘዙት አምላክ እግዚአብሔር ዮናስን እንዲውጥ ዓሣ አንበሪውን አዘዘው፡፡ አንበሪውም ዮናስን ከመርከቧ ወደ በሕር ሲወረውሩት ተቀብሎ ዋጠው፡፡ ዮናስም በዓሣ አንበሪው ሆድ ውስጥ ሶስት መዓልት ወሌለት አደረ፡፡ እግዚአብሔር አዞታልና ዓሣው ዮናስን አልጎዳውም፡፡ ነቢዩም በአንበሪው ሆድ ውስጥ ሆኖ እንዲህ ጸለየ፡- በመከራዬ ሳለሁ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ እርሱም ሰማኝ በሲኦልም ሆድ ውስጥ ሆኜ ጮኽሁ፥ ቃሌንም አዳመጥህ። ወደ ጥልቁ ወደ ባሕሩ ውስጥ ጣልኸኝ፥ ፈሳሾችም በዙሪያዬ ነበሩ ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ አለፉ። እኔም። ከዓይንህ ፊት ተጣልሁ ነገር ግን ወደ ቅዱስ መቅደስህ ደግሞ እመለከታለሁ አልሁ። ውኆችም እስከ ነፍሴ ድረስ ከበቡኝ ጥልቁ ባሕር በዙሪያዬ ነበረ የባሕሩ ሣር በራሴ ተጠምጥሞ ነበር። ወደ ተራሮች መሠረት ወረድሁ በምድርና በመወርወሪያዎችዋ ለዘላለም ተዘጋሁ አንተ ግን፥ አቤቱ አምላኬ፥ ሕይወቴን ከጕድጓዱ አወጣህ። ዮና. ፪፥ ፪- ፯፡፡

ወደ እግዚአብሔር መሸሽ እንጂ ከእርሱ ሸሽቶ ማምለጥ፣ ከፊቱም ኮብልሎ ከመካራ መዳን አይቻልም፡፡ እርሱ በመከራ ጊዜ መሸሸጊያ፣ በችግር ሰዓት መጠጊያ፣ በምቾትም ጊዜ ሰላማችን ነው፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት በመዝሙር ፩፻፴፰፥ ፯- ፲፪ ላይ አይቴኑ አሐውር እመንፈስከ፤ ወአይቴኑ እጎይ እምቅድመ ገጽከ፡፡ እመኒ ዐረጉ ውስተ ሰማይ ህየኒ አንተ፤ ወእመኒ ወረድኩ ውስተ ቀላይ ህየኒ ሀሎከ፡፡ ወእመኒ ነሣርኩ ክንፈ ከመ ንስር፤ ወሠረርኩ እስከ መሕለቅተ ባሕር፣ ህየኒ እዴከ ትመርሐኒ፤ ወታነብረኒ የማንከ፡፡ ወእቤ ጽልመትኑ እንጋ ኬደኒ ወሌሊትኒ ብሩህ ውስተ ትስፍህትየ፡፡ እስመ ጽልመትኒ ኢጸልም በሀቤከ፤ ወሌሊትኒ ብሩህ ከመ መዐልት፤ በአምጣነ ጥልመታ ከማሁ ብርሀነ ‹‹ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ አለህ። ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ። እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች። በውኑ ጨለማ ትሸፍነኛለች ብል፥ ሌሊት በዙሪያዬ ብርሃን ትሆናለች ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና፥ ሌሊትም እንደ ቀን ታበራለችና እንደ ጨለማዋ እንዲሁ ብርሃንዋ ነው›› ብሎ ዘምሯል።
 https://scontent-mxp1-1.xx.fbcdn.net/hphotos-xpl1/v/t1.0-9/12717556_756859621080764_5456513885435778854_n.jpg?oh=836827bebad68c9daf879de38fe592b3&oe=575AC3D1
ከሶሰት ቀንና ሶስት ሌሊት በኋላ ዓሣ አንበሪው ነቢዩ ዮናስን ወስዶ በአንጻረ ነነዌ እንዲተፋው እግዚአብሔር አዘዘው፡፡ አንበሪውም በታዘዘው መሠረት ነቢዩን ወደ የብስ ተፋው፡፡ ይህም ምሳሌ ነው፡፡ ዮናስ የክርስቶስ፣ ከርሰ ዓሣ የመቃብር፣ ሶስት ቀን ሶስት ሌሊት ጌታ በከርሰ መቃብር ውሎ ያደረበት መዓልት ወሌለት፣ ጽንፈ ነነዌ የትንሳኤ ምሳሌ ነው፡፡
  
ይቆየን፡፡

No comments:

Post a Comment