የሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት
ጥር ፳፱ ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ከብሔራዊ ቤተ
መዛግብት ወመዘክር ወደ ነባር ቦታው በክብር ሲመለስ ቅዱስ ፓትርያርኩ የክብር እንግዳ ሆነው በሥነ ሥርዓቱ ላይ መገኘታቸውን ከሪፖርተር
ጋዜጣ ረቡዕ እትም የካቲት ፪ ቀን ፳፻፰ ዓ/ም
ገጽ ፴ ላይ ስመለከት አግራሞት ፈጠረብኝ፡፡ ግራም ተጋባሁ፡፡
ጋዜጣው ሀውልቱ ከብሔራዊ ቤተ መዛግብት ወመዘክር ተነስቶ ወደ አራዳ
ቅ/ጊዮርጊስ ወይም ወደ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ አደባባይ ሲጓዝ የነበረውን ሥነ ሥርዓት እንደሚከተለው ይተርካል፡፡
“ሃውልቱ ከጊዜያዊው ማቆያ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም (ብሔራዊ ቤተ መዛግብት ወመዘክር ቢባል ቋንቋው ሀገርኛ ይሆናል) በዕለቱ ረፋድ
ላይ ተነስቶ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጎዳና በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ በኩል በታላቅ አጀብ በጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ሰልፈኞች፣
በካህናቱ ዝማሬና በሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን፣ በፌዴራል ፖሊስ ማርሽ ባንድ ታጅቦ ከጥንት መንበሩ ከደረሰ በኋላ አቡነ ጴጥሮስ ያኔ ሰማዕትነትን
በተቀበሉባት አምስት ሰዓት ተሩብ በመድረስ የማቆምና የመግለጡ ተግባር ተከናውኗል፡፡ በነቂስ የወጣውም ማሕበረሰብ ወንዱ በሆታ ሴቱ
በእልልታ ደስታውን ገልጿል” ይላል፡፡
ከዚህ በኋላ ጥቂት አናቅጽ ወረድ
ብለው ሲያነቡ ከእሰገራሚው አንቀጽ ጋር ይፋጠጣሉ፡፡ እንዲህ ያነቡታል፡- “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለሊቀ ጳጳሱ የማዕትነትን ክብር መስጠቷንና በንጉሠ
ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አማከይነት ሰማዕትነትን በተቀበሉበት ቦታ ለሀገርና ለነፃነት የከፈሉትን የሕይወት ዋጋ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በየትውልድ
ዘመኑ እንድያከብሩትና እንዲማሩበት የመታሰቢያ ሃውልት ማቆማቸውን ያስታወሱት የክብር እንግዳው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ለባቡር ምንገድ ሥራ ሲባል ከሶስት ዓመታት በፊት ከቦታው
ተነስቶ የነበረውን ሃውልት በክብርና በታላቅ ሥነ ሥርዓት መመለሱ መንግሥትን ያስመሰግናዋል ብለዋል”፡፡
ትልቁ ቅሌት እንግዲህ እዚህ ላይ
ነው፡፡ ለመሆኑ ጽና መስቀል የያዙ ካህናትና የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን በዝማሬና ስብሓተ እግዚአብሔር ባጀቡት የቤተ ክርስቲያን በዓል ላይ ያውም በታለቁ
ሰማዕት በዓል አከባበር ሥነ ሥርዓት ላይ ጋበዡ ማን ነው? ሰማዕቱንስ ቅዱስ ብላ የሰየመችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አይደለችንም? በዓሉስ የማን ነው? የቤተ ክርስቲያን በዓል አይደለምን? ቤተ ክርስቲያን ውድ ልጇን በደም
(በሰማዕትነት) በክብር እየሞሸረች አይደለም እንዴ? ታዲያ ደጋሹ ማን ነው? ቤተ መንግሥት ወይስ ቤተ ክህነት? በማን ድግስ ማንስ ይጋብዛል? ቅዱስ ፓትርያርካችን ግን በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት ታድመዋል፡፡
በዚህ ዓይነት የእግዚአብሔር ለቄሳር፣ የቄሳር ለእግዚአብሔር አልሆነም ትላላችሁ?
ቅዱስ ፓትርያርኩ ማሕበረ ቅዱሳንን
ለማፍረስ ሲነሱ ክብረ ቤተ ክስርቲያንንም አብሮ ሊያፈርሱ አስበዋል እንዴ! ክብሯ፣ ወግ ሥርዓቷ ተዘነጋቸው እንዴ? ሰው በገዛ ቤቱ በገዛ ድግሱ ተጋባዥ
እንግዳ ሆኖ ሲገኝ ቅዱስነታቸው በዓለም የመጀመርያው ሰው ይመስሉኛል፡፡
ገድሎ ማዳን ነው እንዴ የያስከው
አትበሉኝና ቅዱስነታቸው በእንግድነት በታደሙት በዓል ላይ የሚያስመሰግን አንድ ትልቅ ሥራም ሠርተዋል፡፡ ገዜጣው እንዲህ ያስረዳል
“ቅዱስነታቸው አያይዘውም እንደ ሰማዕቱ
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በተመሳሳይ ሁኔታ በጎሬ ከተማ በ1929 ዓ/ም በፋሽስት ኢጣሊያን በግፍ የተገደሉት ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ሚካኤልም
ለሀገር ክብርና ለነፃነት የከፈሉትን የሕይወት ዋጋ ሁሉ እንዲዘክረውና እንዲማርበት በቅዱስ ሲኖዶስ አማካነት የተዘጋጀው ሃውልታቸው
ሰማዕትነትን በተቀበሉበት ቦታ በጎሬ ከተማ በክብር እንዲመለስና እንዲቆም ለሚመለከተውና ለኢትዮጰያውያን ሁሉ መልእክታተውን አስተላልፈዋል”፡፡
ይህ ከአንድ አባት የሚጠበቅ ታላቅ መልእክት ነው፡፡ ከአባቶቻችን የምንጠብቀውና
የምንፈልገው ትምህርትና ምክር እንዲህ ያለ ደግና መልካም ትእዛዝ፣ ምክር፣ መልእክትና መመርያ ነው፡፡ በዚህ ቃለ ሕይወት ያሰማልን፤
በሌላውም አባታዊ ቅን ልቡና ይስጥልን እንላለን፡፡
በዚሁ እግረ መንገዴን ስለቤተ ክርስቲያናችን
ወቅታዊ ጉዳይ ጠቅለል ያለ ነገር መናገር እፈልጋለሁ፡፡ እርግጥ ነው ቤተ ክርስቲያን ኑሮዋ በመስቀል ላይ ስለሆነ ዱሮም በአላውያን
ነገሥታት ስትገፋ ኖራለች፤ ዛሬም ትገፋለች፡፡ ሚዛኑ ይለያይ እንጂ ስደቷ አሁንም አላበቃም፡፡ ለጊዜው በጎ የሚመስሉ ጉዳታቸው የሚከፋ
ዛሬ ያልታዩን ነገ ከባድ ችግር የሚወልዱ ልናጤናቸው የሚገባ በርካታ ጉደዮች አሉ፡፡ ጥንታውያት አብያተ ክርስቲያናት፣ ልዩ ልዩ
የቤተ ክርስቲያን ቅርሶች፣ ንዋያተ ቅድሳት፣ በዓለተ ቤተ ክርስቲያን፣ … ወዘተ ከቤተ ክርስቲያን ይዞታነት ሾልከው ሊወጡ እየተቃረቡ
ነው፡፡ ዛሬ ቤተ ክስርቲያን ሁነኛ አባት፣ ምንደኛ ያልሆነ እውነተኛ እረኛ በማጠቷ ንዋያተ ቅድሳቷ ያለ ቤተ ክርስቲያን ፈቃድ በማይመለከታቸው
አከላት ለማይገባ አገልግሎት ይውላሉ፡፡ ተገቢው ክብር ሳይሰጠቸው እንደ ማንኛውም ተራ ሸቀጥ ሊያውም አማኝ በልሆነ ሰው በገበያ
ይሸጣሉ፡፡ ይህን ማስተካከልና ማረም የሁሉም ክርስቲያን ግዴታ ሲሆን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አበቶቻችን መሪ ተዋናይ ፊት አውራሪ
መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡
የዘመኑ አባቶቻችን አብዛኞዎቹ እግዚአብሔር ለምን እንደሾማቸው ሥራቸውንና ተልእኮአቸውን ቢገነዘቡ፣ በማን
ላይ እንደሾማቸው ክብርና ስልጣናቸውን ቢያስተውሉ፤ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ክብርና ልዕልና ለመጠበቅ የሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ
ወኔ በደማቸው ውስጥ ይኖር ነበር፡፡ በትረ ሙሴን መያዝ፣ መስቀለ ክርስቶስን መጨበጥ፣ ቅናተ ዮሐንስን መታጠቅና አስኩማ እንጦንስን
መሸከም ብቻ ለአባትነት ክብር አያበቃም፡፡ ዓላማውን መረዳት፣ ሆኖ መገኘት፣ ሠርቶ ማሳየት ይገባል፡፡ ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ የሰማዕትነት
ክብር ያገኙት ያማረ ሽቱ መዓዛ አርከፍክፎ ሣይሆን ገላቸውን በፋሽስት ኢጣሊያ የጥይት እሩምታ በደም ታጥበው ነው፡፡
የሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በረከት
ይደርብን፡፡
አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment