ታሕሳስ ፳፮ ቀን ፳፻፰ ዓ/ም
ለእንግዶች ማረፊያ ስፍራ ያልነበረሽ
የተናቅሽ መንደር፣ የከብቶች ግርግም፣ የእረኞች ማደርያ ታናሽቱ ከተማ ቤተልሔም ሆይ ክርስቶስ ባንቺ ተወልዷልና ደስ ይበልሽ፡፡
ውርደት ንቀትሽ ቀርቶ፤ ታናሽነትሽ ተረስቶ ታላቅ አደባባይ የክብር ዙፋን ሆነሽ ተገኝተሸል፡፡
ቤተልሔም ብሂል ቤተ ህብስት እንዲል
የዘላዓለም ምግብ የሕይወት እንጀራ፣ እውነተኛ የሕይወት መጠጥ የተወለደብሽ እውነትም የእንጀራ ቤት ነሽ፡፡ አርባ ዓመት ሙሉ እስራኤልን
መና ከሰማይ አውርዶ ውሃ ከዓለት አፍልቆ በሲና በረሃ የመገበ ጌታ አምላክ እርሱ ራሱ ህብስተ መና ስቴ ሕይወት ሆኖ ከድንግል እናቱ
ባንቺ ተወለደ፡፡
ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም አምላክ
ባንቺ ተወልዶ ቢያይ ተፈሥሒ ኦ ቤተልሔም ሀገሮሙ ለነቢያት እስመ በኀቤኪ ተወልደ ክርስቶስ ዳግማይ አዳም ከመ ያግብኦ ለአዳም ቀዳሚ
ብእሲ እምድር ውስተ ገነት ይስዐር ፍትሐ ሞት (የነቢያት ሀገራቸው ቤተልሔም ሆይ ደስ ይበልሽ ሁለተኛው አዳም ክርስቶስ በአንቺ
ዘንድ ተወልዷልና፡፡ የቀድሞውን ሰው አዳምን ከምድር /ሲኦል/ ወደ ገነት ይመልሰው ዘንድ የሞት ፍርድም ያጠፋለት ዘንድ) ብሎ ባንቺ
የተደረገውን አደነቀ፡፡
ቤተልሔም ሆይ አንቺ ዛሬ የታላቁ
ንጉሥ የክርስቶስ ከተማ ነሽ፡፡ በምድር ላይ ቀድሞ ባንቺ ነግሧልና ደስታሽ ብዙ ነው፡፡ የቀድሞ አዳምን ከውርደት ወደ ቀድሞ ክብሩ፣
ከባርነት ወደ ቀደመ ጌትነቱ (የፍጡራን አክሊል)፣ ከሲኦል ወደ ቀድሞ ስፍራው ወደ ገነት፣ ከሞት ወደ ሕይወት (ከገሀነም እሳት
ወደ መንግሥተ ሰማያት)፣ ከጠላትነት ወደ አምላክ ልጅነት፣ ከደካማ ሰውነት ወደ ተመኘው አምላክነት (ምሥጢረ ሥጋዌ) በክብር ይመልሰው
ዘንድ ዳግማይ አዳም (ሁለተኛው አዳም) ክርስቶስ ባንቺ ተወለደ፡፡
ለክርስቶስ ልደት የአዳም በደል
ምክንያት እንደሆነ ቅዱስ ጰውሎስ እንደሚከተለው ያብራራዋል፡፡ ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት ባንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ፣ በኃጢአትም
ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤ ሕግ እስከ መጣ ድረስ ኃጢአት በዓለም ነበርና፣ ነገር ግን ሕግ
በሌለበት ጊዜ ኃጢአት አይቆጠርም፣ ነገር ግን በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ
ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው ለእርሱ አምሳሉ ነውና፡፡ ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን እንደዚያው አይደለም፤ ባንድ
ሰው በደል ብዙዎች ሞተዋልና፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የሆነው ስጦታ ከዚያ ይልቅ ለብዙዎች
በዛ፡፡ … በአንዱ በደል ሞት በአንዱ በኩል ከነገሠ፣ ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ የሚቀበል በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ
በኩል በሕይወት ይነግሣሉ፡፡ ሮሜ. ፭፥፲፪ - ፲፯::
አንቺ ቤተልሔም ከተላላቆቹ የይሁዳ
ከተሞች አንቺ ትበልጫለሽ፡፡ እስራኤል ዘነፍስ ወስጋን በነፍስ በሥጋ፣ በመንፈስ በህሊና፣ በሕግ በአምልኮ የሚገዛ ታላቅ ንጉሥ ክርስቶስ
ባንቺ ተወልዶ ነግሶብሻል፡፡ ነቢዩ ሚኪያስ ከዘመን ጀርባ ሆኖ በመንፈስ ቅዱስ አይቶ ወአንቲኒ ቤተልሔም ምድረ ኤፍራታ ኢቲተሐቲ
እምነገሥተ ይሁዳ፡፡ እስመ አምኔኪ ይወጽእ ንጉሥ ዘይርዕዮሙ ለሕዝብየ እስራኤል (አንቺ ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ አንቺ
በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ተነሺ፡፡ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላዓለም የሆነ በእስራኤል ላይ ገዥ የሚሆን
ይወጣልኛል) በማለት ተምኔቱ ገልጾ ነበር፡፡
ቤተልሔም ሰማያዊ ንጉሥ ቢወለድባት
ዛሬ በታላቅ ደስታ ተሞሽራ ሰማይን መሰለች፡፡ የብርሀን ድንኳን ተተክሎባታል፡፡ ለሰማያዊው ንጉሥ ክብር የብርሀን ድንኳን ተዘርግቶባታል፡፡
የክብር አጎበር ተጥሎ የብርሀን መጋረጃዎች ተጋርደውባታል፡፡ የክብር ነጋሪት ተጎስሞባታል፡፡ ነገሥታት ደጅ ጠንተውባታል፤ ገብረውባታልም፡፡
ቤተልሔም ዛሬ የሰማይ ምትክ ሆነች፡፡
ሰው፣ መላእክትና እንስሳት ሲያገለግሉት የፈጣሪ ቸርነት የፍጡራን አንድነት ታይቶባታል፡፡ የአምላክ ዙፋን ተዘርግቶባት በዘበነ ኪሩብ
ሆኖ በአእላፍ መላእክት የሚመሰገን እርሱ አልፋና ኦሚጋ ዛሬ በቤተልሔም ሰውና መላእክት በአንድነት በቀድሞ ባልሆነ በአዲስ ምስጋና
አመሰገኑት፡፡ ደሃ ሀብታም ሳይባል የሰው ሁሉ እኩልነት ታይቶባታል፡፡ እረኞች ከነ መንጎቻቸው ነገሥታት ከነ ሰራዊቶቻቸው በአንድ
ላይ ከትመው የፍቅር ከተማ ሆናለች፡፡
ቤተልሔም የሐዲስ ኪዳን ቅዳሴ ቤት
ናት፡፡ የሐዲስ ኪዳን ቅዳሴ (ምስጋና) ዛሬ በቤተልሔም ተጀመረ፡፡ ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ
(ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፣ ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ) ብለው አረኞች (ሰዎች) ከመላእክት ጋር በአንድነት
በታለቅ ምስጋና አዲስ ሰማያዊ ዝማሬ ዘመሩ፡፡ ቀደሱ፡፡ ሉቃ. ፪፥ ፰ - ፲፭ን ይመልከቱ፡፡ ድሮስ አምላካችን እረኞችን መች ንቆ
ያውቃል? ወላጅ አባቱ የዘነጋውን የበግ
እረኛ ትንሹን ዳዊትን አምላክ አከበረው እንጂ መች ናቀው? እንደ ልቤ የሆነ ዳዊትን አገኘሁ ብሎ ታላቅ ንጉሥ አደረገው፡፡ ዛሬም
መንጋቸውን ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ የተናቁ እረኞች ብርሀነ ልደቱን እንዲያዩ ለክብር መረጣቸው፡፡
በቤተልሔም ሰውና መላእክት በአንድነት
ዘመሩ፡፡ በሰውና በእግዚአብሔር፣ በሰውና በመላእክት፣ በነፍስና በሥጋ፣ በሰማይና በምድር መካከል የነበረው ጠላትነት ቀረ፡፡ ሰላም
ወረደ፣ ፍቅር አንድነት ሆነ፣ እርቅ ተፈጸመ፡፡
በቤተልሔም ሰው የመላእክትን ዝማሬ
ዘመረ፡፡ ከመላእክት ማሕበር አንድነት ተደመረ፡፡ ከፈጣሪው ታርቆ ሰማያዊ ሕይወትን ጀመረ፡፡ ኪዳነ አዳም፣ ተስፋ አበው፣ ትንቢተ
ነቢያት፣ ሱባኤ ካህናት ተፈጸመ፡፡ የአሕዛብ ተስፋ፣ የቅዱሳን አክሊል፣ የቤተ ክርስቲያን መሠረት መድኅን ዓለም ክርስቶስ በቤተልሔም
ዋሻ ተወለደ፡፡ ለካህናት ሹመት፣ ለነገሥታት ስልጣን፤ የሚሰጥ ለቅዱሳን የብርሀን አክሊል የሚያጎናጽፍ ብርሀን ልብሱ የሆነ እርሱ
ታለቁ ንጉሥ በጨርቅ ተጠቅልሎ በከብቶች በረት ተኛ፡፡ በጎል ሰከበ በአጽርቅት ተጠብለለ እንዲል፡፡ እልፍኙን እሳት ማገሩን ውሃ
ያደረገ፡- እሳት ጽርሑ ማየ ጠፈሩ፣ ደመና መንኮራኮሩ፣ ተብሎ የሚመሰገን መድኅን ዓለም ክርስቶስ እንደ ምስኪን ደሃ በተናቀ ቦታ በከብቶች በረት ተወለደ፡፡
እንስሳቱም ትንፋሻቸውን ገበሩለት፡፡ በግርግም ተኝቶ ከነገሥታት እጅ መንሻ ተቀበለ፡፡ ፍጡራንን የሚመግብ እርሱ ከእናቱ ጡት ሲለምን
እንደ ሕጻነት አለቀሰ፡፡ ሰብአ ሰገል (ጠቢባን ነገሥታት) ከሩቅ ምስራቅ ኮከብ እየመራ ቤተልሔም አደረሳቸው፡፡ ነገሥታቱ ተደስተው
ወርቅ፣ እጣን፣ ከርቤ እጅ መንሻ አቀረቡለት፡፡ የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ የዓረብና የሳባ ነገሥታት እጅ መንሻን ያቀርባሉ፡፡
ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል። አሕዛብም ሁሉ ይገዙለታል። እንዲል መዝሙረ ዳዊት ፸፪፥ ፲ - ፲፩፡፡ ወርቁን ለመንግሥቱ፣ እጣኑን
ለክህነቱ፣ ከርቤውን ማሕያዊት ለምትሆን ሞቱ አቀረቡለት፡፡ እርሱም ለዓለም ቤዛ ሊሆን ወዶ፣ ፈቅዶ ተቀበላቸው፡፡
የአዳም ልጆች ሆይ ዛሬ በቤተልሔም
መድኀኒት ተወልዶልናልና ኑ ከእረኞች ጋር እንዘምር፡፡ ኑ ከነገሥታቱ ጋር የምስጋና እጅ መንሻ እናቅርብ፡፡ ልደተ ክርስቶስ
ልደታችን ነውና ኑ ከቅዱሳን መላእክት ጋር ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ ብለን ስለሰላማችን ለእግዚአብሔር
ክብር በሐዲስ ዜማ እንዘምር፡፡
መልካም በዓለ ልደት ይሁንልን፡፡
አሜን!
No comments:
Post a Comment