ጥምቀት ‹‹አጥመቀ›› አጠመቀ ከሚለው
የግእዝ ግስ የወጣ ሳቢ ዘር ነው፡፡ ፍቺውም በገቢር መንከር፣ መድፈቅ፣ መዝፈቅ፤ በተገብሮ መነከር፣ መደፈቅ፣ መዘፈቅ፣ መላ አካልን
በውሃ ውስጥ ማስገባት ማለት ነው፡፡
ጥምቀት ከአዳም የወረስነውን ኃጢአትና
እኛም የፈጸምነውን በደል ሁሉ ደምስሳ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማሕጸነ ዮርዳኖስ እንደገና ከእግዚአብሔር የምንወለድባት የክርስትና
በር ናት፡፡ ኢየሱስም
መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊ*ያይ አይችልም አለው። ኒቆዲሞስም ሰው
ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው። ኢየሱስም መለሰ፥
እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።
ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው። ዮሐ. ፫፥፫-፮፡፡
የእግዚአብሔር ልጅነት፣ የቤተ ክርስቲያን
አበልነትና ሱታፌ መንፈስ ቅዱስን የምናገኘው በምሥጢረ ጥምቀት ነው፡፡ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን አሕዛብን ሁል አስተምራና አሳምና
በስመ ሥላሴ እንድታጠምቅ በአምላከዋ ታዛለች፡፡ እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥
ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ
ጋር ነኝ። ማቴ. ፳፰፥ ፲፱፡፡
ጥምቀት በብሉይ ኪዳን በብዙ ምሳሌ
ስትፈጸም ቆይታለች፡፡ ከነዚህም ውስጥ አምስቱን እንጠቅሳለን፡፡
፩. ማየ አይኅ ማየ ሥራዌ፡- አጥመቃ ለምድር በማየ አይህ እንዲል፡
ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ
የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቈየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም። ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት
ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፥ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፥ ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፥ ይህም
በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው፡፡ ፩ጴጥ. ፫፥ ፳፩፡፡
፪.
ማየ ኤርትራ፡- አጥመቆሙ ሙሴ በደመና ወበባሕር
እንዲል፡
ወንድሞች ሆይ፥ ይህን ታውቁ ዘንድ
እወዳለሁ። አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፤ ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር
ተጠመቁ፡፡ ፩ቆሮ.፲፥ ፪፡፡
፫. ማየ ኢያሪኮ፡- ወታጠምቃ እገሪሆሙ ለካህናት
እንዲል፡
እንደ መከር ወራት ሁሉ ዮርዳኖስ እጅግ ሞልቶ ነበርና ታቦት ተሸካሚዎቹ ወደ ዮርዳኖስ ሲደርሱ፥ ታቦቱንም
የተሸከሙት የካህናቱ እግሮች በውኃው ዳር ሲጠልቁ፥ ከላይ የሚወርደው ውኃ ቆመ፡፡ ኢያሱ. ፫፥ ፲፭፡፡
፬. ጥምቀተ አይሁድ፡
ኤልሳዕም። ሂድ፥ በዮርዳኖስም ሰባት ጊዜ ታጠብ ሥጋህም ይፈወሳል፥ አንተም ንጹሕ
ትሆናለህ ብሎ ወደ እርሱ መልእክተኛ ላከ። ፪ነገ. ፭፥ ፲፡፡
፭. ጥምቀተ ዮሐንስ መጥምቅ፡
ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር። ማቴ. ፫፥ ፮፡፡
አማናዊት ጥምቀት፡- ክርስቶስ ኢየሱስ በመስቀል ላይ
ሳለ በጦር ተወግቶ በፈሰሰው ማየ ገቦ የምንጠመቃት ጥምቀት ናት፡፡
አማናዊት ጥምቀት ባሕርይዋና ዓላማዋ
እንድ ሲሆን በብዙ ወገን ትፈጸማለች፡፡
ሀ. በውሃና በመንፈስ
ለ. በመንፈስ ቅዱስና በእሳት
ሐ. በደም (ደመ ሰማዕት)
መ. በአንብዐ ንስሓ
ጥምቀተ ክርስቶስ፡- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለ
ዘርዓ ብእሲ በግብረ መንፈስ ቅዱስ በሕቱም ድንግልና ተወልዶ በሰላሰ ዓመቱ በፈለገ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ልጅነት የምናገኝበት
ማሕያዊት የምትሆን ጥምቀት በውሃ ተጠመቀ፡፡ በሳላሳ ክረምት በዮርዳኖስ ተጠምቀ እንዲል፡፡ ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ
ወደ ዮርዳኖስ መጣ። ዮሐንስ ግን እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ብሎ ይከለክለው ነበር። ኢየሱስም
መልሶ፦ አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው። ያን ጊዜ ፈቀደለት። ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው
ከውኃ ወጣ። ማቴ. ፫፥ ፲፫- ፲፭፡፡
መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እኔ
በአንተ ልጠመቅ ይገባኛል እንጂ አንተን እንዴት አጠምቀሃለሁ? ቢለው ጌታው ሕግን ሁሉ ልንፈጽም ይገባል አለው፡፡ እንኪያስ ሌላውን
በአንተ ስም አጠምቃለሁ፡፡ አንተን በማን ስም ላጥምቅህ? ስመ አብ ብከ ወስመ ወልድ ለሊከ ወስመ መንፈስ ቅዱስ ህልው ውስቴትከ በስመ መኑ አጠምቅ ኪያከ አለው፡፡
ጌታም፡- ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሀን ተሣሃለነ፡፡ አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሲመቱ ለመልከ ጼዴቅ ብለህ አጥምቀኝ አለው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመጠመቅ ወደ ዉሃው ሲገባ ዮርዳኖስ ወደ ኋላ ሸሸች፡፡ በሕርኒ
ርእየት ወጎየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ እንዲል፡፡
መዝ.፻፲፫፥ ፫- ፯ ባሕር አየች ሸሸችም፥ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ።
ተራሮች እንደ ኮርማዎች፥ ኮረብቶችም እንደ ጠቦቶች ዘለሉ።
አንቺ ባሕር የሸሸሽ፥ አንቺም ዮርዳኖስ ወደ ኋላሽ የተመለስሽ፥ምን ሆናችኋል?
እናንተም ተራሮች፥ እንደ ኮርማዎች፥ ኮረብቶችስ፥ እንደ ጠቦቶች ለምን ዘለላችሁ?
ከያዕቆብ አምላክ ፊት፥ ከጌታ ፊት
ምድር ተናወጠች፡፡
ጌታም በሰውነቱ ተጋግሮ
በአምላክነቱ አጽንቶአቸዋል፡፡ ዮሐንስም፡- ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሀን ተሣሃለነ እግዚኦ፡፡ አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሲመቱ ለመልከ
ጼዴቅ እያለ አጥምቆታል፡፡ ከውሃውም ሲወጣ ሰማያት ተከፈቱ፡፡ መንፈስ ቅዱስም በአምሳለ ርግብ ጸዓዳ ወርዶ በራሱ ላይ አረፈበት፡፡
የበሕርይ አባቱም አብ በደመና ሆኖ ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ሎቱ ስምዕዎ (የምወደው የበሕርይ ልጄ ይህ ነው እሱን ስሙት)
ብሎ የባሕርይ ልጅነቱን መስክሮለታል፡፡ እነሆም፥ ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ
አየ፤ እነሆም፥ ድምፅ ከሰማያት መጥቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ። ማቴ. ፫፥ ፲፮- ፲፯፡፡
ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም
ተጠምቀ በማይ ከመይትቀደስ ማይ በማለት ጥምቀት ክርስቶስን
ሰብኳል፡፡ ልጅነት የምናገኝበትን ውሃ ለመቀደስ በዉሃ ተጠመቀ አለ፡፡ ዉሃ ለሥጋዊ ሕይወት ልምላሜ ብቻ ሳይሆን የዘለዓለማዊ ሕይወትም
መገኛ እንዲሆን በልደተ ዓለም በውሃ ላይ ሰፍፎ የነበረውን የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ ውሃው ለመመለስ ጌታችን በውሃ ተጠመቀ፡፡
የእግዚአብሔርም
መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር። ዘፍ. ፩፥ ፪፡፡ ይህ መንፈስ የሕይወት መንፈስ ነው፡፡ በውሃ ላይ ያለ የእግዚአብሔር መንፈስ፡፡ ይህ ሕይወት
ዳግም ታደሰ፡፡ ውሃው ተቀደሰ፡፡
በጥምቀተ ክርስቶስ ያገኘናቸው ጸጋዎች፡-
ሀ. ዓለም ከእድፉ ከጉድፉ ታጠበ፡፡
·
ሕዝ. ፴፮፥ ፳፭ ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ፥ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ።
ለ. የሰው ልጅ አጥቶት የነበረውን
የእግዚአብሔር
ልጅነት ዳግም ተጎናጸፈ፡፡
·
ቲቶ. ፫፥ ፬- ፭ ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና
ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ
ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፡፡
ሐ. ውሃ ተቀደሰ፡ የሕይወት ምንጭም
ሆነ፡፡
·
ተጠምቀ በማይ ከመይትቀደስ ማይ፡- በዘመነ
ኖኅ ለፍጡራን መጥፍያ ሆኖ የነበረው ውሃ የሕይወት መገኛ ሆነ፡፡ ውሃ ለጥፋት ብቻ ሳይሆን ለምህረትም የተፈጠረ መሆኑን መሆኑ ተረዳ፡
ታወቀ፡፡
መ. ደሃ በለጸጋ ተስተካከለ፡፡
·
ለሁሉም በውሃ ልጅነት ተሰጠው፡፡
ሠ. ምሥጢረ ሥላሴ ተገለጠ፡፡
·
የሥላሴ አንድነትና ሶስትነት በጎላ በተረዳ ታወቀ፡፡ ወልድ በተለየ አካሉ በማዕከላ ዮርዳኖስ ቆሞ
ሲጠመቅ፣ አብ በደመና ሆኖ ሲናገር፣ መንፈስ ቅዱስም በአምሳለ ርግብ ጸዓዳ ሲወርድ ምሥጢረ ሥላሴ ታወቀ፡ ተብራራ፡፡
ረ. ፀጋ እግዚአብሔርና በረከት
ለዓለም ታደለ፡፡
·
ዮሐ. ፩፥ ፲፮- ፲፯ እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ
ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ።
·
ኤፌ. ፩፥ ፫ በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ
አምላክና አባት ይባረክ።
ሰ. ኃያል አምላክ ትሕትናን አስተማረን፡፡
·
በባርያው እጅ ተጠምቆ ትሕትናን አስተማረ፡፡ በዚሁ መሠረት ታቦታቱ ከክብር መንበራቸው ተነስተው ወደ
ጥምቀተ በሕር ይሄዳሉ፡፡
ሸ. እዳ በደላችን ተሸረ፡ ተደመሰሰልን፡፡
·
ወሰጠጠ መጽሐፈ ዕዳሆሙ ለአዳም ወለሔዋን እንዲል፡፡ ዲያብሎስ በአዳምና በሔዋን የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ
ስመ ግብርናት ጽፋችሁ ብትሰጡኝ ስቃይ/አገዛዝ አቀልላችኋለሁ አላቸው፡፡ አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ ብለው ጽፈው
ሰጡት፡፡ በሁለት እብነ ሩካም ቀርጾ አንዱን በዮርዳኖስ አንዱን በሲአል ቀብሮታል፡፡ በዮርዳኖስ የጠለውን ጌታ ሲጠመቅ እንደ ሰውነቱ
ረግጦ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ አጥፍቶልናል፡፡ በሲኦል የጠለውንም በእለተ እርብ በአከለ ነፍስ ውርዶ ደምስሶልናል፡፡
·
ቆላ. ፪፥ ፲፬ በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው።
እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
No comments:
Post a Comment