Friday, January 1, 2016

‹እግዜር እና ጴጥሮስ›› ይህችን ሰዓት ! (1)

ሰሞኑን ነው አሉ
ደጋግ ቅዱሳን በገነት ውስጥ ያሉ
በድንገት በእግዜር ድምጽ ‹‹ተነሱ!›› ተባሉ

ቅዱሳን ተነሱ እግዜር ተናገረ
በየሀገራቸው እየዘረዘረ….

‹‹
ምንም እናንተ አሁን -
በሥጋ አርፋችሁ በገነት ብትኖሩ
አውቃለሁኝና -
ሁል ጊዜ በመንፈስ እንደምትበሩ
ስለየአገራችሁ ወቅታዊ ሁኔታ
እስኪ ተናገሩ ‹‹ችግሩ›› እንዲፈታ !››
ብሎ እንደጨረሰ አምላክ ንግግሩን
‹‹
ችግር›› የሚለው ቃል አስታውሶት ችግሩን
ፊቱ ሀዘን ከቦት ቁጣው እንደጋለ
ቅዱሱ አርበኛ ጴጥሮስ ብድግ ! አለ፡፡

‹‹
ምነው ግን ፈጣሪ ሁሉን እያወቅኸው
የሀገሬን ነገር እንደዚህ ቸል አልኸው ?
ደግሞስ እኔ ላንተ ምኑን እንድነግርህ
ፈጣሪ ፍጡርህንትጠይቀኛለህ ?››

እግዜርም መለሰ
የጴጥሮስን ራስ በእጁ እየዳሰሰ
‹‹
ረጋ በል ጴጥሮስማወቁን አውቃለሁ
ግና ከአንተ አንደበት መስማትን እሻለሁ፡፡

ምነው ረሳኸው …?
አዳም በለሲቱን ተው እያልሁት በልቶ
በወደቀ ጊዜ ከጸጋው ተራቁቶ
አዳም ወዴት አለህ?› ብዬ የጠየቅሁት
ይመስልሃል ያኔ ቦታውን ያጣሁት?
መስማት ፈልጌ እንጅ ከእርሱ ከአንደበቱ
እንዲናዘዝልኝ ይቀር ዘንድ ኃጢአቱ፡፡

ምነው ረሳኸው …?
እድሜህን በሙሉ ያስተማርኸው ወንጌል
ካህናት ሕዝቡን ከኃጢአቱ ወንጀል
ይፈቱት ዘንድ ሥልጣን ለምን ሰጠኋቸው?
የማይድኑ ሆነው ነው እንዲያው ብምራቸው ?
ስለፈለግሁ እንጅ በጸጋ እንዲከብሩ
ባለሥልጣንሆነው እንዲፈቱ እንዲያስሩ፤
ለማጠየቅ እንጂ የእኔ የፍርድ ዋጋ
ተሰጥቶት በጸጋ
በሰው እጅ እንዳለ እንዳይዘነጋ፡፡

በመንፈስ ተፈጥሮህ -
የማወቅን ሥልጣን ላንተም ስለሰጠሁ
ያው እኔ ማውቀውን -
ከአንተ ከአንደበትህ ማዳመጥን መረጥሁ፡፡››

ቀዝቀዝ አለ ጴጥሮስ ከቁጣው በረደ
ዓይቶ ለመመስከር -
በመናፍስት ፍጥነት ወደእኛ ወረደ
እንደ ብርሃን ፈጥኖ እንደ መልአክ
ኢትዮያን ዳር ከዳር አያት ተዟዙሮ
ወዲያው ተመለሰ ፊቱን ዘን ቋጥሮ ::

ምክንያቱም -
ሀገሩን እንዳያት ልቡ ይበልጥ ደማ
ያው እንዳለች አለች -
በተለያዬ አጽናፍ በድህነት ቆማ

ምሥራቁ ድርቅ ነው ሰሜኑም ተርቧል
ሕዝቡ ሰላም ርቆት መንፈሱ ተዋክቧል
በዚህ ሁሉ መሐል… ‹አንዳንዱ ግን ጠግቧል፡፡

እናም ተመልሶ
ከእግዜር ፊት ቀረበ እንባ እያቀረረ
አንገቱን በሀፍረት እንዳቀረቀረ
‹‹
አየህልኝ አምላክ…›› መናገር ጀመረ
‹‹
አየህልኝ እግዜር !
የገዘትኋት ምድር
ፍጥረትህን በሚገድል አረመኔ ፋሽስት ቅኝ እንዳትገዛ
ከነፃነት ማግስት
በድህነቷ ላይ በጥላቻ መንፈስ የፍጥኝ ተይዛ
እግርህ የረገጠው አፈሯ እሾህና አሜከላ አብቅሎ
ጨለማዋ ገዝፎ የእምነት ልቧ ቂም በቀልን አዝሎ
ምነው ዛሬስ ባልሄድሁ !
ሕዝቦቿ እርስ በርስ
ሲከፋፈሉ አየሁ
ሲሰራረቁ አየሁ
ሲጠላሉም አየሁ
!
ባይኔ ነው ያየሁት ዓይኔን አምነዋለሁ
ይሄን ያሳየኸኝ ምን በድየሃለሁ ?

በሥጋዬም ሆነ አሁንም በነፍሴ እረፍት ስላጣሁኝ
በወላጅ እናትህ በማርያም በስሟ አምልሃለሁኝ ፡፡
ኢትዮጵያውያንን
በሥጋም በነፍስም እረፍት አሳጥተህ እንዲህ ከምትቀጣን

እንዳልነበርን ርገን ራስህ ለራስህ በሰጠኸው ሥልጣን ፡፡››

ሲለው እግዜርም ትንሽ ፈገግ ብሎ
ጥቂት ወደ ጴጥሮስ ራሱን አዘንብሎ
‹‹
አይ ሰው መሆን ደጉ
እየውልህ ጴጥሮስ አንተ ጀግናው ልጄ!
ይሄን ሁሉ ችግር -
በዝምታ ማየው መስሎህ ነው ወድጄ ?
በእግዜርነት ትዕግሥት !
በአምላክነት ምህረት ! እንጅ ተገድጄ ፡፡

በል አሁን ከቁጣህ ትንሽ ተረጋግተህ
ጓደኞችህንም በዚሁ አወያይተህ
ነገ እናወጋለን ከክፉ እስከ ደጉ
መለየት ግድ ነው -
አብሮ እንዳይቀጣ ተኩላውና በጉ !!!››

አለውና እግዜር በዚህ ተለያዩ
ሰላም ካሳደረን
እንሰማቸዋለን ነገ ሲወያዩ ፡፡
ሰላም እንድናድር ………. ‹‹ትጉና ጸልዩ !››

መላኩ አላምረው - መለኛ ሐሳቦች©)


(ከበድሬ ትዩብ የተወሰደ)







No comments:

Post a Comment