ከዘምን ዘመን ተሸጋግረን ለዛሬዋ
ቀን የደረስነው ስለመልካምነታችን አይደለም ፡፡ ከሌላው በተሸለ ዕውቀታችንም አይደለም ፡፡ ይልቁንም ዕድሜ ሊነፈገን ቸርነት ሊነሳን
የሚገባን ምንም ዕውቀት የሌለን በተፈጥሮ የተሰጠንን ማስታወል በብዝሃ ኃጢአት ያጣን ደንቆሮዎች ነን ፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን
ግን በቸርነቱ ጤናን ሰጥቶ ዕድሜን አበድሮ እስከ ዛሬ ጠብቆናል ፡፡ ክብር ምስጋና ለእርሱ ይሁን ፡፡
ውድ ወገኖቼ፡- ከዘምን ዘመን መሸጋገር
አዲስ ዓመት ማክበር ብቻውን በቂ አይደለም ፡፡ የሕይወት ትርጉምም የለውም ፡፡ ከዘመን ዘመን ስንሸጋገር ከክፉ ሥራ ወደ መልካምና
በጎ ሥነምግባር መሻገር ወይም ከአንድ ትንሽ በጎ ሥራ ወደ ተሻለ ሀገርንና ወገንን ወደሚጠቅም መልካም ሥራ ማደግ ፣ በብዙ የጽድቅ
ሥራ በትሩፋት መበልጸግ ይገባል ፡፡ ከነበርንበት የኃጢአት አረንቋ ወደ ንሥሓ ሕይወት ፣ ከተኛንበት የኃጢአት እንቅልፍ መንቃት
ያስፈልጋል ፡፡
አዲስ ዓመት ስናከብር ልብሳችንና
ዕቅዳችን ብቻ ሳይሆን ሕይወታችንም መለወጥ መታደስ አለበት ፡፡ አሮጎውን ሰውነት አስወግደን አዲሱን ሰው መልበስ ይጠበቅብናል ፡፡
በአዲስ ዓመት አስተሳሰባችንን ፣ አኗኗራችንን ማደስ አለብን ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሕይወታችን በንሥሓ መለወጥና መታደስ አለበት
፡፡
ሰው በተፈጥሮ የፍጡራን ሁሉ ራስና
አክሊል ነው ፡፡ እግዚአብሔር በእጁ ሥራ ሁሉ ላይ ሾሞታልና ዓለምና በውስጧ ያለው ሁሉ በሰው ተፅዕኖ ስር ነው ፡፡ ይህም በመሆኑ
እግዚአብሔር ሰው ዓለምን እንዴት ማስተዳደር እንዳለበት በየዓመቱ ሠርቶ ያሰየዋል ፤ ያስተምረዋል ፡፡ ወርኃ ክረምቱን አሳልፎ በወርኃ
መስከረም ሰማይን በከዋክብት ሸልሞ ምድር በሥነ ጽጌያት (አበቦች) አስጊጦ አሽቆጥቁጦ ፍጡራን ሁሉ በደስታ ሲፈነድቁ ፣ ሰዎች በከዋክብት
ብርሃን በአበቦች መዓዛ ሲመሰጡ ፣ እንስሳት ዘራዊት በመስክ በዱር ሲቦርቁ ፣ አእዋፍና ቢራቢሮዎች አበባ መስለው በአበቦች መሃል
ሲበሩ ሲባረሩ ዓለም ለፍጡራን ሁሉ የማትሰለች የደስታ ምንጭ የፍደቃ ቦታ ሆና ሲያያት ሰው በዚህ ሁሉ ይደሰታል ፤ አእምሮው ይታደሳል
፡፡
በአዲስ ዓመት ራሳችን ታድሰን ዓለምን
ለማደስ ተፈጥሮን በቁጥጥራችን ስር ለማዋል ሳይሆን በሕገ ተፈጥሮ ስር ሆነን ተፈጥሮን ለመንከባከብ ማለም ፣ ማቀድና መሥራት አለብን
፡፡ እግዚአብሔር ዓለምን ውብ አድርጎ የሰጠን በእንክብካቤ ጠብቀን እንድንጠቀምባት ነው ፡፡ ሰው ውቢቷን ዓለም በጦርነት እያመሰ
፣ በእሳት እየጠበሳ ፣ በምሳር እየቆረጠ ውበት ልምላሜዋን ሊያጠፋ አይገባውም ፡፡
ተፈጥሮን መጠበቅና መንከባከብ ይገባናል
፡፡ ተፈጥሮ ከጠበቁአት ትጠብቃለች ፣ ከተንከባከቡአት ትንከባከባለች ፣ ከጠቁኣት ታጠቃለች ፣ ካራቆቱአት ታራቁታለች ፣ ከስራቡአት
ታስርባለች ፣ ካስጠሙአት ታስጠማለች ፣ ካደረቁአት ታደርቃለች ፡፡ ዓለም ዛሬ የኦዞን ንጣፍ ሳስቶብኝ ሙቃት በርትቶብኛል ፣ ድርቅ
አጥቅቶኛል ብላ የምትጨነቀው ተፈጥሮን መጠበቅ መንከባከብ አቅቶአት ነው ፡፡ በሰዎች ዘንድ አዲስ አስተሳሰብ ቀና አመለካከት ስለጠፋ
ነው ፡፡ ስለዚህ አዲሱን ዓመት ስናከብር ስለተፈጥሮ (ስለፍጡራን ሁሉ) ማሰብ ይገባናል ፡፡
ተፈጥሮን ስንጠብቅ ትልቁን ሥራችንን
እንዳንዘነጋም መጠንቀቅ ይገባል ፡፡ የተቸገረን መርዳት ፣ የተራበን ማጉረስ ፣ የታረዘን ማልበስ ፣ የተጠማን ማጠጣት ፣ ያዘነን
ማረጋጋት ፣ የታሰረን ማስፈታት ፣ የተመመን መጠየቅ የሕይወታችን ቅኝት ይሁን ፡፡ አዲስ ሰው አዲስ ሕይወት አዲስ አኗኗር ይለዋል
ይህ ነው ፡፡ ይህም ተፈጥሮአዊና ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው ፡፡
ውድ ወገኖቹ፡- የማያረጀውን ሀይማኖት
ለማደስ ከምንሯሯጥ የረጀ የፈጀ አስተሳሰባችንን በዕውቀት ፣ በሓጢአት ያረጀ ሕይወታችንን በንሥሓ ለማደስ እንሽቀዳደም ፡፡ ዘንድሮ
ከአምናው የተሸለ አስተሳሰብና አመለካከት አዲስ ሕይወት ይኑረን ፡፡ አዲስ ሕይወት መልካምነት ፣ ቅንነት ፣ ታማንነት ፣ ትህትና
፣ በጎነት ፣ ርህራሄ ፣ ለጋስነት ፣ ቸርነት ፣ ሰላማዊነት ፣ ብልፅግና ነው ፡፡
በአዲስ ሕይወት መኖር ማለት በሕይወት
መታደስና መለወጥ ነው ፡፡ ለሕይወት ለውጥና እድሳት የሚያስፈልገው ቀለምና ጌጣጌጥ ሳይሆን እውነተኛ ንሥሓ ነው ፡፡ ንሥሓ ከሰዎች
ጋር ለመታረቅ የተዘረጋች የእግዚአብሔር የምህረት እጅ ናት ፡፡ በአዲሱ ዓመት አዲስ ሰው ለመሆን ለሕይወት ለምህረት በተዘረጋችው
የእግዚአብሔር እጅ እንባረክ ፡፡
አዲሱ ዓመት ሠርተን የምናገኝበት
፣ ተምረን የምናውቅበት ፣ ወልደን የምንስምበት ፣ ዘርተን የምንቅምበት ፣ የሰላም ፣ የብልፅግና የነሥሓ ዘመን ይሁንልን ፡፡ አሜን
፡፡
No comments:
Post a Comment