Sunday, March 29, 2015

ሸክማችሁ የከበደ ደካሞች ሁሉ ወደ እኔ ኑ፡፡ ማቴ.፲፩÷፳፰


                        ክፍል ሁለት
ከዚህ ሁሉ ባሻገር እሰድራኤላውያኑ ሌሎች ብዙ ማህበራዊና መንፈሳዊ የሆኑ ከባድ ሸክሞች ነበሩባቸው፡፡የሮማውያንን የቅኝ ግዛት ቀንበር አሽቀንጥረው ለመጣል የተደራጁ አደጋ ጣይ ብዙ የነፃ አውጪ ግንባሮች፤በአንጻሩ ደግሞ እንደ ፈሪሳውያን፣ሰዱቃውያን፣ኤሴውያን የመሳሰሉ ሃይማኖታዊ ካባ ለባሽ ቡድኖች ነበሩ፡፡
ከእነዚህ ቡድኖች ውስጥ በተለይም ጻፎችና ፈሪሳውያን እነርሱ በእጃቸው ስንኳ ሳይነኩ በሕዝቡ ላይ በጫኑአቸው ከባድ የአቂበ ሕግ ሸክም ጌታችን በማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ ፳፫ ላይ አጥብቆ ገስጾአቸዋል፡፡
ሕገ እግዚአብሔር እንዳይጥስ ለሕግ የሕግ አጥር ሥራ በሚለው መርሓቸው ተርታው ሕዝብ የሙሴን ሕግ እንዳይተላለፍ በማለት እግዚአብሔር ያላዘዘውን፤ሙሴም ያላስተማረውን ብዙ ሕግና ደንብ ሠርተው በነባሩ ሕግጋት ዙርያ በመተብተብ የማይገፋ የሕግ ሸክሞችን በሕዝብ ላይ ጭነው ሕዝቡን ያስጨንቁ ነበር፡፡
ጸፎችና ፈሪሳውያን ከእግዚአብሔር ይልቅ ሕግ አምላኪዎች ነበሩና የፍቅር ስጦታ የሆነውን ሕገ እግዚአብሔር ወደ ከባድ ሸክምነት ቀይረው፤ሕዝቡ ከፍቅረ እግዚአብሔር ተለይተው በሕግ ለሕግ ብቻ እንዲኖር አድርገዋል፡፡
ለምሳሌ ከአስርቱ ትእዛዛት አንዷ የሆነቸውና ሰንበትን አክብር የምትለውን የፍቅር ሕግ በሰላሳ ዘጠኝ ተጨማሪ ከባድና አስጨናቂ የሕግ አናቅጽ አጥረውታል፡፡እነዚህን ሕግጋት ተላልፎ የተገኘውን ሰው ያለ ርህራሄ በድንጋይ ወግረው ይገድሉታል፡፡
በአጠቃላይ ጸሓፎችና ፈሪሳውያን ለይስሙላ ብቻ ለሕግ የሚኖሩ ግብዞች፣ፍትህን የማያውቁ ምህረት የለሽ ጨካኞች ናቸው፡፡
በዚህ እኩይ ተግባራቸውና አስጨናቂ ሕጋቸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናንተ ግብዞች ወዮላችሁ በማለት ደጋግሞ ይወቅሳቸው ይገስጻቸውም ነበር፡፡
እናንተ ግብዞች ጸሓፎችና ፈሪሳውያን መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ ወዮላችሁ እናንተ አትገቡም፤የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ፡፡እናንተ ግብዞች ጸሓፎችና ፈሪሳውያን በጸሎት ርዝመት እያመከኛችሁ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ ወዮላችሁ፤ስለዚህ የባሰ ፍርድ ተቀበላላችሁ፡፡…እናንተ ግብዞች ጸሓፎችና ፈሪሳውያን ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አስራት ስለምታወጡ፣ፍርድንና ምህረትን ታማኝነትንም፣በሕግ ያለውን ዋናውን ነገር ስለምትተው ወዮላችሁ ሌላውን ሳትተው ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር፡፡…እናንተ ግብዞች ጸሓፎችና ፈሪሳውያን በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጠሩ ወዮላችሁ፡፡…እናንተ ግብዞች ጸሓፎችና ፈሪሳውያን በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን አትንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ ወዮላችሁ፡፡ማቴ.፳፫÷፲፫-፳፮፡፡
እነዚህ ሁሉ ሕዝቡን ያስጨነቁ እጅግ በጣም ከባድ ሸክሞች ነበሩ፡፡በዚህም ሕዝቡ ታውኳል፣ተጨንቋል፤ሸክሙ ከብዶት ከሸክሙ የሚያሰርፈውን ይፈልጋል፡፡በመሆኑም እረፍተ ሥጋ እረፍተ ነፍስ መንግሥተ ሰማያትን የሚሰጥ ሩህሩህ አምላካችን ሸክማችሁ የከበደ ደከሞች ሁሉ ወደ እኔ ኑ በአባታዊ ፍቅሩ ወደራሱ ጠራን፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ በሰው ልጆች ላይ ደዌ ሥጋ ደዌ ነፍስ፣ቀቢጸ ተስፋ፣ፃዕረ ሞት፣አምልኮ ጠኦት፤ከሁሉም በላይ ደግሞ በዘር የሚተላለፍ የሞት ዕደ ከባድ ሸክም ነበረባቸው፡፡ 

ይቀጥላል


No comments:

Post a Comment