ክፍል አንድ
የትምህርቱ ዓላማ ፡-ድካማችንን ተገንዝበን ከድካማችን ሁሉ ወደሚያሰርፈን አምላክ
እንድንቀርብ የንስሓ ጥሪን ማስተጋባት ነው፡፡
ሸክም የሚከብድ፣የሚያደክም፣የሚያሳስብ ከባድ ነገር ሲሆን፤የሸክም ምሥጢራዊ ትርጉሙ ደገሞ ሓጢአት፣መከራ፣በሽታ፣ችግር፣አደራ፣ሀላፊነትየመሳሰሉትን
ያመለክታል፡፡በዚህ ትምህርታችን የምንማረው ስለአንድ ከባድ ቁስ ሳይሆን በዚህ በሸክም ምሥጢራዊ ትርጉም ላይ ተመርኩዘን ጌታ ኢየሱስ
ክርስቶስ ያስተማረውን ትምህርት በአጭሩ እንመለከታለን፡፡
ጌታችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ተአምራት ተደርጎላቸው ንስሓ ያልገቡ ከተሞችን ከገሰፀ በኃላ ‹‹እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ
የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ›› ብሎ ዳግም የንስሓ ጥሪ አቀረበላቸው፡፡ ደካሞች ሁሉ ወደ እኔ ኑ አሳርፋችኋለሁ በማለት፡፡ ከላይ እንዳየነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንቢተ ነቢያትን፣ተስፋ አበውን፣ለመፈጸም በአጭር ቁመት፣በጠባብ ደረት ተወስኖ በለቢሰ ሥጋ፣ በኩነተ ሰብእ ወደ ዓለም በመጣበት ወቅት ለሁሉም ተአምር የሚያስፈልጋቸውን በገቢረ ተአምራት፣ምግበ ሥጋ የሚያስፈልጋቸውን በአበርክቶ ህብሥት፣ፈውስ የሚያስፈልጋቸውን ፈውሰ ሥጋ ፈውሰ ነፍስ በመስጠት ተገቢውን ትምህርት ያስተምራቸው ነበር፡፡በዚሁ መሠረት ብዙ ተአምራት የተደረገባቸው ከተሞች እንደነ ኮራዚ፣ቤተሳዳና ቅፍርናሆም የመሳሰሉትን ንስሓ ባለመግባታቸው ወዮልሽ ኮራዚ፣ወዮልሽ ቤተሳይዳ በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፣ማቅ ለብሰው አመድ ነስንሰው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሓ በገቡ ነበርና…አንቺም ቅፍርናሆም እስከ ሰማይ ክፍ ከፍ አልሽን?ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ፤በአንቺ የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን፣እስከ ዛሬ በኖረች ነበር በማለት ጠንከር ያለ የነቀፋና የግሳፄ ትምህርት አስተምሯቸዋል፡፡
ጌታችን
አመጣጡ በሰው ልጆች ላይ በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ፤በርደተ መቃብር ርደተ ገሀነም የተፈረደባቸውን የአዳምን ፀዊረ ሞት ለማቃለል ነውና‹‹እናንተ
ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ››በማለት የንስሓ ጥሪ አስተላለፈ፡፡
በዘመኑ
እስራኤላውያን የባርነት ቀንበር፣የፈሪሳውያን ትምክህታዊ ትምህርት፣የረበናተ አይሁድ ትብትብ (ሰው ሠራሽ ሕግ) ከባድ ሸክም ነበረባቸው፡፡በተለይም
ረበናተ ኦሪት ተራው ሕዝብ የሙሴን ሕግ እንዳይተላለፍ አጥር ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር ያላዘዘውን፤ሙሴም ያላስተማረውን ሰው ሠራሽ
ሕግ ከራሳቸው አፍልቀውና አመንጭተው ለመፈጸም እጅግ በጣም አስጨናቂ የሆኑ ከባድ የአቂበ ሕግ ሸክም ጭነውባቸው ነበር፡፡ይባስ ብለውም
ያልወለዱ መካኖችን እግዚአብሔር የጠላችሁ ሓጢአተኞች ናችሁ በማለት መብዓቸውን ለቤተ እግዚአብሔር እንዳያቀርቡ ሁሉ ይከልክሉአቸው
ነበር፡፡ነገር ግን እነሱ ራሳቸው ለሠሩአቸው ሕግጋት ተማኞች አልነበሩም፡፡ሕግ ያወጣሉ፣ያስተማራሉ፡፡እነሱ ግን ሕግጋትን አይተገብሩም፡፡በዚህ
እኩይ ተግባራቸው ጌታችን በማቴዎስ ወንጌል ፳፫÷፪-፬ ላይ እዲህ ብሎ ነቅፎአቸዋል፡-ፃፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል፡፡ስለዚህ
ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ፣ጠብቁትም፣ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደሥራቸው አታድርጉ፡፡ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው
በሰው ትከሻ ይጭናሉ፡፡እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም፡፡
ዛሬም
አንዳንድ የህዝብ መሪዎች መንፈሳውያኑም ሆኑ ዓለማውያኑ ሕግ ሲጥሱ፣ሥርዐት ሲያፋልሱ ይታያሉ፡፡እነርሱ ሕግ እያስተማሩ ሕገ ወጥ
ድርጊት ይፈጽማሉ፡፡ህዝቡን ግን ሕግ አክብር፣ሥርዐት ጠብቅ ብለው በወግ አጥባቂነት ሸክማቸው ያስጨንቁታል፡፡ይህ ፈሪሳዊነት ነው፡፡ሮሜ.፪÷፲፯-፳፬
ይቀጥላል፡፡
No comments:
Post a Comment