በስመ
አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ዱ አምላክ አሜን
ኢየሩሳሌም ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ፡፡
በዲያቆን ዓለማየሁ ሀበቴ
(ክፍል ፩)
ኢየሩሳሌም ማለት ሀገረ ሰላም
ማለት ሲሆን ፤ በቅዱስ መጽሐፍ ከነዓን ፣ ምድረ ርስት ፣ የተስፋ ምድር ፣ ማርና ወተት የሚፈስባት ሀገር ፣ የዳዊት
ከተማ በመባል ትታወቃለች[1] ፡፡
ኢየሩሳሌም እግዚኣብሔር ለአብርሀምና ለዘሩ ርስት አድርጎ የሰጠው
የተስፋ ምድር ናት ፡፡ እግዚአብሔርም አብራምን አለው ፡- ከአገርህ ፣ ከዘመዶችህም ፣ ከአበትህም ቤት ፣ ተለይተህ
እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ ፡፡ ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ ፣ እባርክሃለሁ ፣ ስምህንም አከብረዋለሁ ፤ ለበረከትም ሁን ፤ የሚባርኩህንም
እባርካለሁ ፣ የሚረግሙህንም እረግማለሁ ፣ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ ፡፡ አብራምም እግዚአብሔር እንደ ነገረው ሄደ
፡፡ ከካራን ወጥቶም ወደ ከነዓን ምድር ገባ ፡፡ እግዚአብሔርም ለአብራም ተገለጠለትና ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ አለው ፡፡
ዘፍ. ፲፪ ፥ ፩- ፯ ፡፡
ኢየሩሳሌም ነብያተ እግዚአብሔር የኖሩባት መካነ ቅዱሳን ፣
ቅድስተ ቅዱሳን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተገኘችባት ሀገረ ሕይወት ፣ መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶሰ የተወለደባት ማዕከለ
ድኅነት ናት[2]
፡፡ ኢየሩሳሌም ልዑል እግዚአብሔር የሚመለክባት ፣ ታቦተ ጽዮን በክብር የኖረችባት ፣ ታላቁ የሰሎሞን ቤተ መቅደስ የታነፀባት ፣
ሕዝቧም ሕዝበ እግዚአብሔር ፤ ኅሩያነ እግዚአብሔር ተብለው የተጠሩባት ፣ ብሉይ ኪዳን ተወልዳ ፤ ነግሣ ወንጌልን የወለደችባት ፣
ሱባኤ የተቆጠረባት ፣ ትንቢት የተነገረባት ሀገረ ሀይማኖት ፣ በኋላም ክርስቶስ ተወልዶ ድኅነተ ዓለምን የፈፀመባት ማዕከለ ምድር
፣ መካነ ሕይወት ናት[3] ፡፡
መጋቤ ሓዲስ ፣ አብሳሬ ትስብእት ፣ ወሰባኬ ወንጌል ብርሃናዊ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል የዓለም መድኃኒት በኢየሩሳሌም መገኘቱን ለዓለም
ሁሉ ሲያበስር ፡- በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ ፡፡ እነሆም የጌታ መልአከ ወደ እነርሱ
ቀረበ ፤ የጌታ ክብርም በዙርያቸው አበራ ፣ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ ፡፡ መልአኩም እንዲህ አላቸው ፡- እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን
ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለኁና አትፍሩ ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት አርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና ፡፡
ይህም ምልክት ይሆንላችኋል ፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ ፡፡ ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ
፡፡ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ ፡፡ ሉቃ. ፪ ፥ ፰-
፲፬ ፡፡
ኢየሩሳሌም ፡- የሰላም ፣ የፍቅር ፣ የደስታ ከተማ ብትባልም
ሌላ ደግሞ በጎ ያልሆነ ገጽታ አላት[4]
፡፡ ኢየሩሳሌም የመዳን ቀኗን ያላወቀች ፤ ከበረከተ ድኅነቱ ማዕድ ያልተቋደሰች ፤ ከፍቅር ጽዋ ያልተጎነጨች ፤ ደስታዋን የገፋች
፤ ከሰላም ጉባኤ ያልዋለች ፤ የመድኃኒቷንም የሕይወት ጥሪ ያልሰማች ፤ ጌታ ያለቀሰላት አሳዛኝ ከተማ ናት ፡፡ ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም እንተ ትቀትሎሙ ለነቢያት ወእንተ ትዌግሮሙ ለሐዋርያት ለእለ ተፈነው ኀቤሃ ሚመጠነ ፈቀድኩ አስተጋብኦሙ ለውሉድኪ ከመ
እንተ ታስተጋብእ ዶርሆ አፍርኀቲሃ ታሕተ ክነፊሃ ወአበይክሙ ፡፡ ናሁ ይትኀደግ ለክሙ ቤትኪሙ በድወ ፡፡ አማን እብለክሙ ኢትሬእዩኒ እምይእዜ እስከ ሶበ ትብሉ ቡሩክ ዘይመጽእ
በስመ እግዚአብሔ ር ፡፡ ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ነቢያትን የምትገድል
ወደእርሷ የተላኩትንም የምትወግር፣ ዶሮ ጫቹቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድኩ!
አልወደዳችሁምም ፡፡ እነሆ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል ፡፡ እላችኋለሁና በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ
ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም ፡፡ ማቴ. ኧ፫ ፥ ፴፯ - ፴፱ ፡፡
ወገኖቼ እኛስ እንደ እስራኤላውያን ዐይን ያልታወረ እግዚአብሔርን
ማየት የሚችል ዐይነ ሕሊና አለን ? ከለንስ መሲሕን አይተነዋልን ? እግዚአብሔር ነኝ ብሎ በአምላክነቱ በእግዚአብሔር ስም የመጣውን ወደፊትም ለፍርድ የሚመጣውን ወልደ
አምላክ ወልደ ማርያም አምላክነቱን ተረድተን ተቀብለናል ? አንዳንዶቻችን ኢየሱስ ፍጡር ነው አማላጃችን ነው እንለዋለን ፤ ሌሎቻችን
ደግሞ በአንደበታችን ብቻ እናመልካለን ፡፡ የአምልኮት መልክ እንጂ ምግባር የለንም[5]
፡፡
ኢየሩሳሌም የሰላም ከተማ ፣ ቅድስት ሀገር ፣ ሀገረ እግዚአብሔር
፣ የአምልኮ ምድር ብትባልም በአንጻሩ ደግሞ ትንቢተ ነቢያት ፣ ተስፋ አበው ፣ የቤተ ክርስቲያን መሠረት ፣ የአሕዛብ ብርሀን በቤተ
ልሔም ዋሻ መወለዱን አምኖ መቀበል ተስኖአት ሊያድናት ለመጣው መሲሕ ክፉ ጠላት ሆና ምንም እንኳን ሞቱ በፈቃዱ ቢሆንም በመስቀል
ላይ ሰቅላ መድኃኒቷን ገደለችው[6] ፡፡
እናንተ አንገተ ደንዳኖች ልባችሁና ጆሮአችሁ ያልተገረዘ እናንተ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ ፤ አባቶቻችሁ እንደ ተቃወሙት
እናንተ ደግሞ ፡፡ ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው ? የጻድቁንም መምጣት አስቀድሞ የተናገሩት ገደሉአቸው ፤ በመላእክት
ሥርዐት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ፣ ገደላችሁትም ፡፡ የሐዋ. ፯፥ ፶- ፶፫
፡፡ ረበናቷም እንደጠበቁት ከቤተ መንግሥት ሳይሆን እነርሱ ከናቁት ቤተሰብ መገኘቱ ፤ ይልቁንም ሁሉ የእርሱ ሆኖ ሳለ በቤተ መንግሥት
በሐር የተጨመጨመ ፣ በወርቅ የተለበጠ ምንጣፍ ይነጠፍልኝ ሳይል እንደ ተራ ምስኪን በእንስሳት ግርግም በመወለዱ መሲሕን መቀበሉ
ሞኝነት መሰላቸው ፡፡ የተቆጠረው ሱባኤ ገና እንዳልደረሰ ፣ ትንቢተ ነቢያት ተስፋ አበው እንዳለተፈፀመና ተስፋ እስራኤል መሲሕ
ገና እንዳልመጣ አበክረው በማስተማር ለዘመናት ቢጠባበቁትም ተምኔታቸውን
ማግኘት አልቻሉም ፡፡ ረበናተ እስራኤል ከክርስትናው ጋር ያላቸው ክፉ ታሪክ እንደ እሬት እየመረራቸው ፣ እንደ እግር ውስጥ እሳት
በቁጭት እየለበለባቸው ተስፋ ያደረጉበት መሲሕያቸው ባለመምጣቱ በቀቢፀ ተስፋ ወድቀው ሊቀ ሐመር እንደሌላት መርከብ በግራ መጋባት
የሐሳብ ማዕበል ይዋልላሉ ፡፡ ተስፋቸው ከመሟጠጡ የተነሳ መሲሕ መቼ ይመጣል ? ተብለው ሲጠየቁ ከአሁን በኋላ በእስራኤል እንኳን
ክርስቶስ መልካም ሰው አይወለድም በማለት መዘባበት መጀመራቸው ይነገራል ፡፡ የሚበጃቸው ግን ባለፈው አሳፋሪ ታሪክ እየተሸማቀቁ
መኖር ሳይሆን በመስቀል ላይ ሰቅለው የገደሉትን ክርስቶስ ኢየሱስን አምኖ በመቀበል ንስሓ ገብቶ ዘላለማዊ ሕይወት ማግኘትና ክፉዉን
ታሪክ ወደ በጎ መቀየር ነው[7] ፡፡
ይቀጥላል …
No comments:
Post a Comment