Saturday, October 1, 2016

አንብር መስቀልየ ዲበ መስቀል (ክፍል ፪)፡፡

                                                             በዲ/ን ዓለማየሁ ሀብቴ
መስከረም ፳፩ ቀን ፳፻፱ ዓ/ም
ግማደ መስቀሉ ለብዙ ዘመናት በእስክድርያ በክብር ተቀምጦ እያለ የግብጽ እስላሞች ቁጥራቸው እየበዛ በመምጣቱ የኃይል የበላይት አግኝተው የእስክንድርያ ክርስቲያኖችን መከራ አብዝተውባቸው ማሰቃየት ጀመሩ፡፡ ይባስ ብለውም ሁለቱን ንዑዳን ክቡራን ጳጳሳት አባ ሚካኤልና አባ ገብርኤልን አስረው ያሰቃዩአቸው ጀመሩ፡፡ የእስክንድርያ ክርስቲያኖች በዘመኑ ኃያል ለነበረው የኢትዮጵያ ንጉሥ አፄ ዳዊት፡- ታላቁ ንጉሥ ሆይ እግዚአብሔር ኃይል እንዳበዘልህ እናውቃለን፡፡ በእኛ በእስክንድርያ በለን ክርስቲያኖች ላይ በዚህ በግብጽ ያሉ እስላሞች ስቃይ አጽንተውብናል፡፡ ኃይልህን አንስተህ እስላሞቹን አስታግስልን፡፡ ጳጳሳቱ አባ ሚካኤልና አባ ገብርኤልም አስረውብናል፡፡ እነርሱንም አስፈታልን ብለው መልእክት ላኩ፡፡