Friday, March 25, 2016

በልቼ ባልጨርስ ጭሬ ልጨርስ



ዶሮ ናት፡፡ ባለቤቶቿና ጎረቤቶቿ ያሰጡትን ስጥ በልቼ ባልጨርስ ጭሬ ልጨርስ አለች፡፡ በልታ የማትጨርሰውን ስጥ መበተን፣ ትንሽ ተጠቅማ ብዙ ማጥፋት ወደደች፡፡
ቅዱስነታቸው ላይጠቅም ላይረባቸው ሀገርን በሚጎዳ የቤተ ክርስቲያንን ሕልውና በሚፈታተን፤ በሰውም ሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ ክብርና ሞገስ ላያገኙበት የቤተ ክርስቲያን ልጆችን በሚያስከፋ፣ ቅን አገልግሎታቸውን በሚያደናቅፍ አደገኛ ሥራ ተጠምደው ሳያቸው የዶሮዋ አባባል ትዝ አለኝ፡፡
 ቤተ ክስቲያን የምትገለገልበትን እግዚአብሔርም የሚከብርበትን በአበው ቤተ ክርስቲያን በፅኑዕ መሠረት ላይ የተመሠረተውን የአገልግሎት ማሕበር ለማፍረስ፣ ያለ ደመወዝ በፀጋ የሚያገለግሉትንና የሚገለገሉትን  አእላፍ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ለመበተን ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ የገዛ ልጆቻቸውን በጠላትነት ፈርጀው እስከ መጨረሻው ድረስ ለመታገልም ወስነዋል፡፡ አስከ ሞት ድረስ እታገላለሁ ብለዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋት አባት በደመ ክርስቶስ የተዋጁ ብርቅዬ ልጆቿን በትኖ ለነጣቂ ተኩላ ለመስጠት የሚታገላትን ሳይሆን የተበተኑትን ለመሰብሰብ፣ የጠፉትን ለመፈለግ ከእኩያት አጋንንት ጋር የሚታገል አባት ነው፡፡ እግዚአብሔር ለምን እንደሾመው፣ በማን ላይ እንደሾመው፣ ሥራውንና ተልእኮውን፣  ክብርና ስልጣኑን የሚያውቅ፤ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ክብርና ልዕልና ለመጠበቅ የሰማዕታትን ፅዋ የሚጨልጥ፣ በትረ ሙሴን መያዝ፣ መስቀለ ክርስቶስን መጨበጥ፣ ቅናተ ዮሐንስን መታጠቅና አስኩማ እንጦንስን መሸከም ብቻ ለአባትነት ክብር እንደማያበቃ የሚገነዘብ፣ ዓላማውን መረዳት፣ ሆኖ መገኘት፣ ሠርቶ ማሳየት የሚችል፣ መምህረ ፍቅር የሆነ አባት ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋት አባት ለሀገር ነፃነት፣ ለምእመናን አንድነት፣ ለቤተ ክርስቲያን ክብር ከጠላት ጋር የሚታገል እውነተኛ አባት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምትፈልገው ዙፋነ ክብሩን እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ በመስቀለ ክርስቶስ ላይ ቁልቁል የሚዘረጋ፣ እንደ ቶማስ በገዛ ቆዳው አሸዋ የሚሸከም (ስለ ቤተ ክርስቲያን መከራ ሥጋን መቀበል)፣ ከልጆቹ ጋር ሳይሆን እንደ አግናጢዎስ ከአናብስት (አላውያን) ጋር ስለ ልጆቹ የሚታገል፣ እንደ ዲዮስቆሮስ ለሀይማኖቱ ምስክርነት ጥርሱን የሚገብር፣ እንደ ተክልዬ እግር ሰጥቶ ክንፍ የሚቀበል፣ እንደ ገብረ መንሰፈስ ቅዱስ ድንጋ ነክሶ ለኢትዮጵያ የሚጸልይ፣ እንደ ሕፃን ሞዓ ከበሬ ጋር ተጠምዶ የሚያርስ፤ እንደ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ለሀገር ነፃነት፣ ለወገን ክብር፣ ለቤተ ክርስቲያን ሕልውና ጥይት ለብሶ በደም የሚያጌጥ አባት ነው፡፡
አባት ማለት ያለወቀን የሚያስተምር፣ ለደከመው የሚጸለይ፣ ያጠፋውን የሚገሰጽ፣ የባዘነውን የሚፈለግ፣ የተበተኑትን የሚሰበሰብ፣ የተጣሉትን የሚያስታርቅ፣ ከተበደሉ ጋር ቆሞ ለፍትህ የሚሟገት፣ ለሰው ሁሉ አባታዊ ፍቅር ሰጥቶ በመልካም እረኝነት አባግአ ክርስቶስን የሚያሰማራ ነው፡፡
ከአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ጋር ወግኖ የቤተክርስቲያን ልጆችን መንቀፍ፣ መራገም፣ መኮነን፣ ማሳደድ፣ መበተን፣ ማጣለት፣ አሳልፎ ለፍርድ መስጠት፤ ቤተ ክርስቲያን ስትገፋ፣ ክብሯ ሲደፈር፣ ምእመናን ሲበተኑ፣ መርሓ ግብሮቿ ሲስተጓጎሉ፣ ቤተ ክርስቲያን የወንበዴዎች ዋሻ ሆና ሀብቷ ሲመዘበር፣ አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ፣ ገዳማት ሲደፈሩ፣ እናት ቤተ ክርስቲያን ጓዳዋ ሙሉ ሆኖ ሳለ የአብነት መምህራን ተርበው ሲሰደዱ፣ ካህናት የገጠር አብያትን ዘግተው ዳቦ ፍለጋ ወደ ከተማ ሲፈልሱ በቸልታ ማየት ጌታ በወንጌል እንደተናገረው ከመልካም እረኛ የማይጠበቅ ምንደኝነት ነው፡፡ የዮሐንስ ወንጌል ምእራፍ ፲ን ልብ ይለዋል፡፡    
መልካም እረኛ ስለበጎቹ ይገደዋል፡፡ ሥጋቸውን በልቶ ፀጉራቸውን ሸልቶ ለነጣቂ ተኩላ አሳልፎ አይሰጣቸውም፡፡ በለምለም መስክ (ሀይማኖት፣ ምግባር) አሰማርቶ በፍጹም ፍቅር ይጠብቃቸዋል፤ ይከባከባቸውማል፡፡ በታላቁ ሊቀ ኖሎት ክርስቶስ ግልገሎቼን አሰማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ በጎቼን አሰማራ ተብሏልና፡፡ ዮሐ. ፳፩፥ ፲፭- ፲፰፡፡
አባግዕ(በጎች) የተባሉ ምእመናን ናቸው፡፡ ሥጋቸውን በልቶ ፀጉራቸውን መሸለት ማለት በምእመናን መንፈሳዊ፣ ሥጋዊና ቁሳዊ ሀብት መጠቀም ማለት ነው፡፡
ቅዱስነታቸው የሚኖሩበት ውብ ሕንፃ የተሠራው፣ የሚቀመጡበት ምቹ ዙፋን፣ የሚሄዱባት ዘመናዊ መኪና፣ የሚተኙበት አልጋ፣ የሚጫሙት ጫማ፣ የሚለብሱት የክብር ልብስ፣ የሚጨብቱት የወርቅ መስቀል፣ የሚዙአት ቆንጆ በትረ ሙሴ፣ የሚደፉት አስኬማ፣ … የተገዙት፣ የሚበሉት፣ ሲታመሙ ውጭ ሀገር ሄደው የሚታከሙበት ገንዘብ እርሳቸው ከሚበትኑት ምእመናን ከደሃዋ መቀነት የተሰበሰበ ነው፡፡ እሱም ቢሆን በቤተ ክስርሰቲያ  በተሰገሰጉ ቅዱስነታቸውም በዝምታ ከሚመለከቱአቸው ሙዳይ ገልባጮች የተረፈ ነው፡፡
ታዲያ ይህ ድርጊታቸው ነቢየ እግዚአብሔር ሕዝቅኤል እንደተናገረው የበጎቹን ጮማ በልቶ ፀጉራቸውን ለብሶ በጎቹን ግን መበተን፣ ለተኩላ አሳልፎ መስጠት አይሆንም ወይ? በበጎቹ ባለቤት በእግዚአብሔር ዘንድስ አያስጠይቅም? ፍትህ ርትዕ የማያጓድለው የእረኞቹ አለቃ እግዚአብሔር ግን በጎቹን ረስተው ራሳቸውን የሚያሰማሩ እረኞችን እቀጣለሁ ይላል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ራሳቸውን ለሚያሰማሩ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች በጎችን ያሰማሩ ዘንድ አይገባቸውምን? ጮማውን ትበላላችሁ ጠጕሩንም ትለብሳላችሁ፥ የወፈሩትን ታርዳላችሁ በጎቹን ግን አታሰማሩም። የደከመውን አላጸናችሁትም የታመመውንም አላከማችሁትም የተሰበረውንም አልጠገናችሁትም የባዘነውንም አልመለሳችሁትም የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም በኃይልና በጭቈናም ገዛችኋቸው። እረኛንም በማጣት ተበተኑ፥ ለምድርም አራዊት ሁሉ መብል ሆኑ፥ ተበተኑም። በጎቼ በተራሮች ሁሉና በረዘሙ ኮረብቶች ሁሉ ላይ ተቅበዝብዘዋል፥ በጎቼም በምድር ፊት ሁሉ ላይ ተበትነዋል የሚሻም የሚፈልግም አልነበረም። ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና እረኛ ስለሌለ እረኞቼም በጎቼን ስላልፈለጉ እረኞችም ራሳቸውን እንጂ በጎቼን ስላላሰማሩ፥ በጎቼ ንጥቂያ ሆነዋልና፥ በጎቼም ለምድር አራዊት ሁሉ መብል ሆነዋልና ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በእረኞች ላይ ነኝ፥ በጎቼንም ከእጃቸው እፈልጋለሁ፥ በጎቼንም ከማሰማራት አስተዋቸዋለሁ። ከዚያም ወዲያ እረኞች ራሳቸውን አያሰማሩም በጎቼንም ከአፋቸው አድናለሁ፥ መብልም አይሆኑላቸውም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ እኔ ራሴ በጎቼን እሻለሁ እፈልግማለሁ። እረኛ በተበተኑት በጎች መካከል ባለ ጊዜ መንጋውን እንደሚፈልግ፥ እንዲሁ በጎቼን እፈልጋለሁ በደመናና በጨለማ ቀን ከተበተኑት ስፍራ ሁሉ አድናቸዋለሁ›› ሕዝ. ፴፬፥ ፩- ፲፪።
ቅዱስ ፓትርያርኩ እኮ ቅዱስ የተባሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለአለች ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያለቸው ደግሞ ምእመናን ስለአሉ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ደም የተመሠረተች ክርስቲያኖች እንድነት ናት፡፡ ክርስቲያኖች (ምእመናን) አልባሳተ ክርስቶስ ሕዋሳተ አካሉ ናቸው፡፡
እግዚአብሔር የመሠረተውን ለማፍረስ መጣር፣ ክርስቶስ በደሙ የሰበሰባትን ቅድስት ሕብረት (የምእመናን አንድነት) ለመበተን አይሁድ በእለተ አርብ እንዳደረጉት አልባሳቱን ለመግፈፍ ከእግዚአብሔር ጋር መታገል ወይም አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን ለመበተን ሲጣደፉ በዝምታ ማየት ከማን ወገን ያሰኝል?
እንግዲህ አባት ከሆኑ ክፋትና ተንኮልን እልከኝነትንም ለሴይጣንና ለሰራዊቱ ትተው ልጆችዎን ይምከሩ፣ ያስተምሩ፣ ይገስጹ፣ የተዛባውን ያስተካክሉ፣ የተጣመመውን ያቃኑ፤ የተጓደለውን ያሟሉ፣ መልካም እረኛ ከሆኑ ተኩላ ሳይበላው የተበተነውን መንጋ ይሰብስቡ፣ በአደራ የተቀበሉአትን ቤተ ክርስቲያን ይጠብቁ፡፡
የቤተ ክርስቲያን የበላይ መሪ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስም ልጆቹ ሲበተኑ፣ ቤተ ክርስቲያን ስትደፈር በዝምታ ማየት የለበትም፡፡ ብፁዓን አበቶች መክረው፣ ዘክረው የማስተካከያ እርምጃ ካልወሰዱ ውጤቱ መልካም አይሆንም፡፡ ዶሮዋ ጭራ ሳትጨርስ ዛሬ እሽ ከልተባለች ቁጭ ብለው የሰቀሉት ቆሞ ለማውረድ ከባድ ይሆናል፡፡ ‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ›› የሐዋ ፳፥ ፳፰።





    

No comments:

Post a Comment