Thursday, February 4, 2016

ከመላእክት ጋር አንድ አድርገን

አቤቱ የእያንዳንዱን ልመናውን አሰብ፤ አቤቱ እያንዳንዱን ከእናቱ ማኅፀን ጀምረህ አስብ፤ በቀናች ሃይማኖት የሚኖሩትን ብዙ አሕዛብ አስብ፤ ሴቶቻቸውን ጠብቅ፤ ጎልማሶቻቸውን አቅና፤ ሽማግሎቻቸውን አጽና፤
በመከራ የተቀጠቀጡትን አድን፤ በስደት የተበተኑትን ሰብስብ፤ መንገድ ከሚሄዱት ጋርም በረድኤት ሂድ፤ በመከራም የሚጨነቁትን አድን፤ በጸብ በክርክር በጽኑ አገዛዝ ያሉትን በረድኤትህ አስባቸው። አቤቱ ዓለምን የያዝህ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ሆይ በረድኤት አስበን።
እውነት ነው አቤቱ ፈጣሪያችን ባልቴትዋን የምትረዳ፤ አባት እናት የሌለውን የደሃውን ልጅ ከመከራ የምታድን፤ ለታመሙት ባለ መድኃኒት፤ መንገድ ለሚሔዱት ወደብ ጸጥታ አንተ ነህ፤ አንተ እግዚአብሔር ልመናውን አኗንዋሩን የቤቱን አሳብ መርምረህ ታውቃለህና፤ አቤቱ ይህችን አገር ሌሎችንም አገሮች ባንተ ሃይማኖት ጸንተው የሚኖሩባቸውን አድን፤ ቅዱሳንን ከመናወጥ ከረኃብ ከሌላም ወገን ከሚመጣባቸው ወራሪ አድን፤ ያማረ የተወደደ ብርሃን ዕውቀትን ግለጽልን፤ መጠራጠርን ከቤተ ክርስቲያንህ አርቅ፤ የምስጋናህ ብርሃን ልጆች ከሚሆኑ ከመላእክት ጋር አንድ አድርገን፤ አንድ ልብ አንድ ቃል ሆነን አብን ወልድን መንፈስ ቅዱስንም እናመስግን ዘንድ ማመስገኑን ስጠን፤ ዛሬም መቼም መች ለዘለአለሙ አሜን።
ሥርዓተ ቅዳሴ የአርብ ሊጦን

No comments:

Post a Comment