ይህችን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ አማርኛ የሚመስሉ የባዕድ ሀገር ስሞች ትክክለኛ የአማርኛ ትርጓሜዎች የሚል መልእክት በድሬ ትዩብ ላይ ማንበቤ ነው ፡፡
ኢትዮጵያውያ ሀገራችን በዓለም ካሉ ሀገራት ሁሉ የተለየ ከእርሷ የበቀለ የራሷ ብቻ የሆነ ሀገር በቀል ባህል ከነወጉ ፣ ቋንቋ ከነፊደሉ ፣ ቀመር ከነቁጥሩ ፣ ታሪክ ከነክብሩ ፣ ትምህርት
፣ ምርምርና ፍልስፍና ከነተጋባሩ ፣ ጥበብ ከነማዕረጉ ፣ አስተዳደር ከነስልቱ አስተባብራ የያዘች ምልዕት ሀገር ናት ፡፡ ከዚህም
ባሻገር ሀገራችን ኢትዮጵያውያ እግዚአብሔር የሚመለክባት የሀይማኖት ደሴት በቅዱሳን ጸሎት የምትጠበቅ ሀገረ እግዚአብሔር ናት
፡፡ ሕዝቧም በሀይማኖት ጸንቶ የሚኖር ሕዝበ እግዚአብሔር ነው ፡፡
ዛሬ ዛሬ ሁሉ እያለን ፣ ሞልቶ ተርፎን ሳለ ምንም እንደሌለን እንቅበዘበዛለን ፡፡
የራሳችንን ትተን የሌላ ፍለጋ ባሕር ማዶ እንሻገራለን ፡፡ ምን አዚም እንደተደረገብም ባለውቅም ሀብታሞች ሳለን ደሆች ፣ ኩሩዎች
ሳለን ወራዶች ፣ ፍቅር እያለን ዳተኞች ፣ አንድ ሆነን ሳለን የተለያየን ፣ ኩሩ ታሪክና ባህል እያለን እንደልነበረን ፣ ቋንቋ
እያለን እንደሌለን ሆነን በምዕራባውያን ቋንቋ፣ ፣ ባህልና በወግ ቅኝ ተገዝተናል
፡፡ ለምሳሌ እንድ በጣም የሚያሳዝነኝ ነገር ልንገራችሁ ፡፡ የዓለምን ዜና/ወሬ የምንመለከትበት ምስለ ድምጻችን ዜናውን በአማርኛ
ሲያስተላልፍ የራሱን ስም ግን የሚጽፈው በባዕድ ቋንቋ EBC ብሎ ነው ፡፡ ስንቱ ያገሬ ገበሬ ምንነቱ ይረዳ ይሆን ? ታዲያ የብብትን ትተን የቆጡን አልሆነብንም ትላላችሁ ? የሰው ወርቅ አያደምቅ አለች አያቴ !
ይህን ስል የአሞራና ቀበሮ ተሪክ ትዝ አለኝ ፡፡ አንድ አሞራ ሙዳ ሥጋ ይዞ ዛፍ
ላይ ሆኖ ሲበላ ቀበሮ ከመሬት ሆኖ ተመለከተና በጣም ጎመዠ ፡፡ ቀበሮው ብልህ ስለነበር እንደጎመዠ አልቀረም ፡፡ ያማረውን ሥጋ
ለመብላት ሥጋውን ከአሞራው አፍ የሚያስጥልበትን ዘዴ ቀየሰ ፡፡ ወደ ላይ ቀና ብሎ አቶ አሞራ በጣም ቆንጆ ነህ ከአእዋፍ ሁሉ
አንተ ታምራለህ ይለዋል ፡፡ አሞራው ደስ ብሎት በፈገግታ ቀበሮውን ወደ መሬት ሲመለከት ቀበሮው መልሶ ፡- ምን ዋጋ አለው
ውበትህ ተበላሽቷል ፤ የያስከው ሥጋ ውበትህን እንደልነበረ አድርጎተል አለው ፡፡ አሞራውም በጣም አዝኖ ታዲያ ምን ላድርግ አቶ
ቀበሮ ይለዋል ፡፡ ቀበሮውም ውበትህ እንዲፈካ የያስከውን ሥጋ ወደ መሬት ጣለው ውበት ተመልሶ ይደምቃል አለው ፡፡ አሞራው ውበት
እንዳይበላሽ ሥጋውን ወደ መሬት ሲጥል ቀበሮው ከመ ቅጽበት ሙዳ ሥጋውን አፈፍ አድርጎ መብላት ጀመረ ፡፡ አሞራው ቀበሮው
ሥጋውን እየዘነጠለ ሲጎርስ አይቶ ምራቁን እየዋጠ አቶ ቀበሮ ምሳይስ ? ሲለው ቀበሮው በል አንተ ውበትህን ብላ
አለው ፡፡ እኛም ወርቅ ሰጥተን ጠጠር እንዳንቀበል እንጠንቀቅ ፡፡
አማርኛ የሚመስሉ የባዕድ ሀገር ስሞች ትክክለኛ የአማርኛ ፍች
፩. ኮሌጅ------ መካነ ትምህርት
፪. ዩኒቨርስቲ------መካነ አምሮ
፫. ሌክቸር .......ትምህርተ ጉባኤ
፬. ሌክተቸረር.........መምህረ ጉባኤ
፭. ዲን ----- ሊቀ ጉባኤ
፮. ቢሮ........ መስሪያ ቤት
፯. ባንክ..... ቤተ ንዋይ
፰. ሲቪል ሰርቪስ...... ሰላማዊ አገልግሎት
፱. ከስተም ...... ኬላ
፲. ኮምፒተር...... መቀመሪያ
፲፩. ድግሪ..... ማዕረግ
፲፪. ሚኒስተር..... ምሉክ
፲፫. ማስ ሚዲያ..... ምህዋረ ዜና
፲፬. ፎቶ ግራፍ ..... ብራናዊ ስዕል
፲፭. ራዲዮ.... ንፈሰ ድምፅ
፲፮. ፖሊስ ...... የህግ ዘበኛ
፲፯. ኢንተርኔት.... የህዋ አውታር
፲፰. ሎሬት.... አምበል፣ ተሸላሚ የቅኔ
፲፱. ዶክተር ..... ሊቀ ሙህር
፳. ኢምባሲ ..... የእንደራሲ ፅ/ቤት
፳፩. ዲፕሎማት ..... የመንግስት መልክተኞች
፳፪. ኢኮኖሚክስ... ስነ ብዕል
፳፫. ሀዋላ...... ምህዋረ ንዋይ
፳፬. ሳሎን ..... እንግዳ መቀበያ
፳፭. ቱሪዝም..... ስነ ህዋፄ
፳፮. ስካን... ምክታብ
፳፯. ፕሬዝዳንት.... ሊቀ ሀገር/ ሙሴ
፳፰. ቴሌኮሚኒኬሽን.... ምህዋረ ቃል
፳፱. ቪዛ ..... የይለፍ ፍቃድ
፴. ፓስፖርት..... የኬላ ማለፊያ
No comments:
Post a Comment